ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ Featured

 

ዘንድሮ አዳዲስ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታዎች አይጀመሩም

የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ

የታክስ ስርዓቱን የማዘመን ስራ ይሰራል

መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትግበራው ተጠናክሮ ይቀጥላል

የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመንን ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ትናንት በይፋ ከፍተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸውም፤ አዳዲስ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደማይጀመሩ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ፣ የታክስ ስርዓቱን የማዘመን ሥራ እንደሚሰራ፣ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትግበራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለማሟላት፤ በ2010 የተረጋጋ የውጭ ንግድን የሚያበረታታ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲን ለማስፈን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ዶክተር ሙላቱ ተናግረው የኤክስፖርት ምርትና ግብይት ላይ በማተኮር 80 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም እንስሳት ምርትን በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ የመጡትን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማዕከል በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት በፍጥነት እንዲያድግ ይደረጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተለይም በማዕድኑ ዘርፍ ወርቅን ጨምሮ ሌሎች ጌጣጌጦችን ንግድ ለማበረታታት በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም ነው የገለጹት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ መልክ ተጠናክሮ የተጀመረውን የታክስ ሪፎርም ሥራ በተለይም በትላልቆቹ ግብር ከፋዮች ላይ በማተኮር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የታክስ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ የሚያተኩርባቸውን የውዝፍ ዕዳ አሟጦ የመሰብሰብ፣ የታክስ ኦዲት ሥርዓቱን ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት በማድረግ የማዘመንና የስጋት የሥራ አመራርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የማድረግ ትግበራ እንደሚኖርም ነው ያብራሩት፡፡

በዘርፉ ያለውን የመረጃ ሥርዓት ለመቅረፍ ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ የመጠቀም፣ የታክስ አስተዳደር መስሪያ ቤቱን የውስጥ ድርጅታዊ ጤንነት የመጠበቅና የታክስ ሰብሳቢ ሙያተኞችን በመስሪያ ቤቱ የማቆየት ሥራ እና ውጤት ተኮር የሥራ አመራርን ለማስፈን ይሰራል ብለዋል ዶክተር ሙላቱ ፡፡

በኮንስትራክሽንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ሌሎች የታክስ እፎይታ ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ በህጉ መሰረት የማይከፍሉ ታክስ ከፋዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የህግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚሰራ፣ ያላግባብ የመጠቀም ዝንባሌና ተግባር እንዲሁም ሙስና የታክስ ከፋዩን ህብረተሰብ በስፋት በማሳተፍ ትግል እንደሚደረግበትና የአስተዳደር ሥርዓቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ለንግድና አገልግሎት ተብሎ የተገነቡ ህንጻዎች አካባቢ ከኪራይ ጋር በተያያዘ የሚካሄደውን ማጭበርበርና ታክስ ስወራ ህጋዊ መስመር የማስያዝ ሥራ እንደሚተገበርም ገልጸዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን መሙላትና የአገልግሎት አቅርቦት ጥራትን ማሳደግ የኢኮኖሚውን ፖሊሲ ተወዳዳሪነት ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ ነው ፡፡ በመሆኑም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እጅግ ግዙፍ ፋይናንስ ይጠይቃሉ ፡፡ በተያዘው ዓመትም የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ወደ ተሟላ ሥራ እንዲገባ የማድረግና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን ማስቀጠል ሥራ ይሰራል፡፡ አዳዲስ ግንባታዎችን ለማስጀመር የሚያስችል ፋይናንስ ማግኘት ባለመቻሉ ሁኔታው እስኪስተካከል ድረስ አዳዲስ ግንባታዎች አይጀመሩም፡፡

ዴሞክራሲን ልማትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት ዶክተር ሙላቱ፤ የሥርዓቱ አደጋ የሆኑትን ያለውድድርና አላግባብ የመጠቀም፣ የሙስና ዝንባሌና ተግባር ለመቆጣጠር በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ታውጆ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እንደተደረገ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የታክስ ሥርዓት፣ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር፣ ግዢና የኮንስትራክሽን አስተዳደር፣ የመሬት ልማትና አቅርቦት እንዲሁም የመሬት አስተዳደር ግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ አላግባብ የመጠቀምና ሙስና ጎልቶ ይታይባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓትና ፀረ-ኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የፍርድ ሥርዓት፣ የፖሊስ አገልግሎትና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችም ተመሳሳይ ችግር እንደነበረባቸው ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ ላይ የተጀመሩ የሪፎርም ሥርዓቶች በአንዳንድ ቦታዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸው፤ አብዛኛው ቦታዎች ላይ ግን በዝግጅት ላይ ከመሆናቸው አንፃር መጓተት እንደሚታይባቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍጥነትና ጥራታቸውን በመጨመር የተሟላ ትግበራ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸውን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ሥራም በጥናት ላይ ተመስርቶ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ በመላው ሀገሪቱ የሚካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ ነጻ፣ ፍትሃዊና በህዝቡ ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ባለፈው ዓመት የምርጫ ሥርዓቱን በተመለከተ ሊደረግ ለታሰበው ማሻሻያም ውይይት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ ለምክር ቤቱ ቀርቦ በ2012 .ም በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ ይተገበራል ብለዋል ዶክተር ሙላቱ፡፡

 

ዘላለም ግዛው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።