የባንኮች ተደራሽነት በቅርንጫፍና በቴክኖሎጂ መካከል Featured

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች አገልግሎት እየተስፋፋና እያደገ ቢመጣም ከአገሪቷ ሕዝብ ቁጥርና ከኢኮኖሚው እድገት አንጻር ተደራሽነቱ ዝቅተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ለተደራሽነቱ መጨመር ቅርንጫፎችን ማስፋፋት ተገቢ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ቴክኖሎጂ ትክክለኛው መፍትሄ እንደሆነ የሚገልጹ አልታጡም፡፡

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በኢትዮጵያ የባንኮች ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር አራት ሺህ 227 የባንክ ቅርጫፎችና 10 ሺህ 481 የወኪል ባንኮች፣ ሁለት ሺህ 743 ኤቲኤም ማሽኖች እና ስምንት ሺህ 895 የክፍያ መፈጸሚያ ነቁጦች (ፖስ ማሽን) ብቻ ነው ያለው፤ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ካሉ አገሮች አንጻር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የሚያብራሩት፡፡

እንደ አቶ ተክለወልድ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ባንኮችን ጨምሮ በመደበኛ ፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሆኑ ጎልማሶች ብዛት 22 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በአንጻሩ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት 34 በመቶ ደርሷል፡፡ ለዚህ ልዩነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በዋናነት 35 በመቶ ያህሉ የባንኮች ቅርጫፎች በከተሞች ላይ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የገጠሩን ኅብረተሰብ የባንክ ተጠቃሚ አላደረገውም፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የባንክ አገልግሎት መስጠቱም በኤሌክትሪክና በተንቀሳቃሽ ስልክ ኔትወርክ ጥራት ማነስ ምክንያት ገና በጅምር ላይ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የኢኮኖሚ መምህርና የአንበሳ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢው ፕሮፌስር ጣሰው ወልደሀና በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያሉ ንግድ ባንኮች ጠንካራም ደካማም ጎን አላቸው ይላሉ፡፡ አጀማመራቸው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ባለፉት 15 ዓመታት ቁጥራቸው መጨመሩ፣ ከሌሎች አክሲዮን ኩባንያዎች ጋር ሲነጻጸሩ ትርፋማ መሆናቸው፣ ብዙም ሙስና የማይታይባቸውና የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ጥንካሬያቸው መሆኑን ይጠቅሱና፤ ተደራሽነታቸው ግን ውስን ነው ይላሉ፡፡

ቅርጫፎችንም ሆነ አገልግሎታቸውን በደንብ አላስፋፉም፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውም ውስን በመሆኑ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንክ አገልግሎትን ምን ያህሉ በምን ያህል ጥራት ይሰጣሉ የሚለውም ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በዚህ ምክንያትም በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ተጠቃሚው ቁጥር በጣም አነስተኛ ሆኗል ሲሉም ነው ፕሮፌሰሩ ያብራሩት፡፡

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በኢትዮጵያ ያለውን የባንክ ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በኬንያ 60 በመቶ የአገሪቷ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) የሚንቀሳቀሰው በሞባይል ባንኪንግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን እዚህ ደረጃ ላይ ገና አልደረሰችም፡፡ በእርግጥ ከመንግሥት ባንኮች ውጭ በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት መስፋፋት የጀመረው ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ቢሆንም፤ አሁን ያለው የባንክ ቅርጫፍ ብዛት 100 ሚሊዮን ሕዝብ ለሚኖርባትና በአፍሪካ አራተኛውን ትልቅ ኢኮኖሚ ላስመዘገበች አገር የሚመጥን እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡

መንግሥት ይህንን የባንኮችን ተደራሽነት ለማሳደግ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አጽድቆ ማውጣቱን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ይናገራሉ። በዚህ ስትራቴጂ መሠረትም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የፋይናንስ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር፣ የባንክ ቅርጫፎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና በቴክኖሎጂ የታገዙ የባንክ አገልግሎቶችን በስፋት ለመስጠት ዕቅድ መያዙንና በ2012 .ም በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሚሆነውን ኅብረተሰብ ከ22 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማድረስ ግብ መቀመጡንም አቶ ደመቀ የገለጹት፡፡

አቶ ዘመዴነህ በበኩላቸው ቅርጫፎች መከፈት ተገቢ ቢሆንም ኢትዮጵያ በስፋቷ ትልቅ አገር ስለሆነች ቅርጫፎችን ከማስፋፋት ይልቅ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ለተደራሽነት አዋጭ ነው ይላሉ፡፡ ዛሬ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሞባይል ስላላቸው በሞባይል ባንክ መጠቀም ይመቻቸዋል፡፡ ስለሆነም በመጪዎቹ አምስትና ስድስት ዓመታት በቀላሉ ብዙ ሚሊዮን ሰዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከተፈለገ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ያለበት የባንክ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የባንክ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ላይ ነው ባይናቸው፡፡ የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የወኪል የባንክ አገልግሎቶች በመስጠት 70 እና 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቷን ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ይቻላልም ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰር ጣሰው ግን ቅርንጫፎችም ቴክኖሎጂውም መስፋፋት አለበት የሚል ሃሳብ ነው ያላቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉትም፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር በመሆኑ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንክ አገልግሎት የማግኘቱ ዕድልም ሆነ ዘመናዊ ስልኮችን የማግኘቱ ጉዳይ ውስን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቅርንጫፎችን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ለከተማው ኅብረተሰብ ደግሞ የኢንተርኔት፣ የሞባይል፣ የፖስና የወኪል ባንክ አገልግሎትን ማስፋፋት ይበጃል፡፡ ስለዚህ አንዱ ካንዱ የሚመረጥበት ነገር የለም፤ ሁለቱም ተያይዘው መሄድ አለባቸው፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት መስፋፋት የጀመረው የደርግ ሥርዓት ወድቆ የነፃ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላም በጣም በዝቀተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የባንኮች ቁጠባ መጠን የ29 ነጥብ ስምንት በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 568 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ500 ሺህ ብር ተገድቦ የነበረው የግለሰቦች የካፒታል መጠንም፤ በ23 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ በማደግ 560 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ 17 ትንንሽ ባንኮች አሉ፡፡ የባንክን ተደራሽነት ለማስፋፋትና ጠንካራ ባንኮች ለማድረግ 17 እንዲዋሀዱ በማድረግ ቢያንስ አራት ቢበዛ አምስት ባንኮች ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም ለደንበኞቻቸው ከፍተኛ ብድር፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል፤ ወጪም ይቀንሳል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁን ኢኮኖሚ በምታንቀሳቅሰው ደቡብ አፍሪካ አምስት ንግድ ባንኮች ነው ያላት፡፡ ካናዳና እንግሊዝም አራት ትልልቅ ባንኮች ነው ያላቸው፡፡ ናይጀሪያም 85 የነበሩት ባንኮችን በትዕዛዝ 14 እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም ከመንግሥት ባንኮች ውጪ ከአምስት ባንኮች በላይ አያስፈልጋትም፡፡

ፕሮፌሰር ጣሰው ግን በአንድ ሴክተር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና ለማደግ ውድድር ሊኖር ይገባል፡፡ የባንኮች ቁጥር ማነስ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ የባንኮች ቁጥር ማነስ ውድድር እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የባንክ ተጠቃሚን ማብዛት ነው እንጂ የባንኮችን ቁጥር መቀነስ ዘርፉ ላይ ጥንካሬ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ነው የገለጹት፡፡ ዛሬም ደረስ 50 እና 60 ባንኮች ያሏቸውእንደ ኬንያ ያሉ አገራት መኖራቸውንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ስለዚህ ይሄ መፍትሄ ጊዜውን የጠበቀ አይደለም ብለዋል፡፡

የባንክ ሴክተሩ ካልተስፋፋ በቁጠባ መልኩ ሀብት ለማሰባሰብ አስቸጋሪ ይሆናል የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ በየቦታው ቅርጫፎች መክፈትና በተለይ ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ የባንክ አገልግሎት መስጠት ከተቻለ ቁጠባው እየጨመረ ይሄዳል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ቴሌኮም 56 ሚሊዮን ደንበኞችን የሚያስተናግድበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ 100 ሚሊዮን ደንበኛ ለማስተናገድ ዕቅድ ይዟል፡፡ ይህንን ዕድል መጠቀም ከተቻለ 100 ሚሊዮን ሕዝብ የባንክ ሂሳብ ደብተር ይኖረዋል፤ አገራዊ ቁጠባውም ያድጋል ባይ ናቸው፡፡ ስለሆነም ቴክኖሎጂው እስኪስፋፋ ቅርንጫፎችን በስፋት መጠቀም፤ ቴክኖሎጂው በደረሰበት አካባቢ ደግሞ ቴክኖሎጂውን መጠቀም ከተቻለ አገራዊ የፋይናስ ተደራሽነቱን ማስፋፋት ይቻላል ብለዋል፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።