ማትረፍ እየቻለ ለወጪ የዳረገው ዘርፍ Featured

ዜና ትንታኔ

ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሁኑ ወቅት በማርብልና ግራናይት ማምረቻ ድርጅቶች አማካኝነት የሀገር ውስጥ ፍላጎት 70 ከመቶ በታች እየሸፈነ ይገኛል፡፡ ፍላጎቱን ለመሙላት ከአንድ ነጥብ አምስት እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጭ ይገባሉ፡፡ የሀገር ውስጥ አቅምን ማሳደግ ላይ ካልተተኮረ ያለውን ሃብት አለመጠቀም ሀገሪቱን ዋጋ እንደሚያስከፍላት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮጵያ እብነበረድ ማምረቻ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ኃይለማሪያም፤ ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የተፈጥሮ ግራናይትና ማርብል ግብዓት እየተጠቀመች አለመሆኑ አላስፈላጊ ወጪ እያስወጣት ነው ይላሉ፡፡ የሚመሩት ተቋም እንደ ቀዳሚነቱ ያለውን ሃብት በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት ቢሰራም ዘመናዊ መሳሪያዎችን የመጠቀም አቅም መፍጠር ባለመቻሉ ስኬታማ ነው ለማለት እንደማያስደፍርም ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ እቅድ በዓመት እስከ 80 ሺ ካሬ ሜትር እብነበረድ ማምረት ቢሆንም እስካሁን ከፍተኛ የምርት መጠን ግን 69 ሺ ካሬ ሜትር ነው፡፡

አቶ ተሾም እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ ማርብልና ግራናይት ምርት ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ በመሆኑ ጥራቱ ከውጭ ከሚገባው እንደሚበልጥ ጥርጥር የለውም፤ የማምረት አቅምን ማሳደግ ከተቻለ ከውጭ ማስገባቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡

የሀገር ውስጥ ምርትን ለመጨመርና በዋጋቸው ተወዳዳሪ ለማድረግ ከውጭ የሚገባውን መጠን መቀነስ ያስፈልጋል። በምትኩ የሀገር ውስጥ አቅምን ማሳደግ እና ኢትዮጵያ ያላትን የማርብልና ግራናይት አቅም በትክክል መጠቀም እንድትችል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ማስቻል መፍትሄ ይሆናል፡፡

የግል የቴራዞ ማምረቻ ድርጅት ባለቤትና የኢትዮጵያ የእብነበረድና ቴራዞ አምራች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ ኪዳኔ፤ የግራናይትና ማርብል ምርት ለምን ከውጭ ማስገባት እንዳስፈለገ በትክክል ሊጠና እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡«የሀገር ውስጥ ማምረቻ ፋብሪካዎች ባልተጠናከሩበት ሁኔታ ከውጭ የሚገባው ምርት ይቁም ማለት አይቻልም» ሲሉ ይገልጻሉ፤ ጎን ለጎን ግን በአገሪቱ የሚገኙትንና ማምረቻዎች አቅም በማሳደግ ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ወጪ መቀነስና እንደሚያስፈልግ ነው የሚስረዱት። «ባለው በቂ ግብዓት በመጠቀም የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ሀገሪቱን ካላስፈላጊ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል›› ይላሉ፡፡

ተፈጥሯዊና ከፍተኛ ጥራት ያለው የሀገር ውስጥ ግራናይት ምርት በዋጋ በካሬ ሜትር 1200 ብር፤ ከውጭ የሚገባው ግን እስከ 2ሺ ብር እንደሆነ በማስረዳት የሀገር ውስጥ አቅምን ማሳደግ ቢቻል ለገበያውም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ማቅረብ እንደሚቻል ያመለክታሉ። እና የሀገር ውስጥ አቅምን በበቂ ማበረታቻ ማጠናከር ሳይቻል ፍላጎትን ለማሟላት ከውጭ ማስገባት እንደ መፍትሄ መወሰድ የለበትም ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ ብድር ለማግኘት ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን ለሚያመርቱና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ተመሳሳይ ስራ ሆኖ በብድር አቅርቦት በኩል የሚጠየቀው ወለድ 12 በመቶ ነው፤ ወደ ውጭ ለሚልኩ ግን 9 በመቶ ነው። በተጨማሪም ዘርፉን ለማጠናከር ያለው ድጋፍና ማበረታቻ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣውን ወጪ የሀገር ውስጥ አቅም ለማሳደግ ቢውል መልካም ነው፡፡ የብድር አቅርቦቱን አበረታች ማድረግና የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ማሳደግ ይገባል፡፡

በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሴራሚክና ተዛማጅ ኢንዱስትሪዎች ልማት ዳይሬክቶሬት መሪ ተመራማሪ አቶ ንጋት መላክ፤ አምራች ድርጅቶች እየጨመሩ ቢመጡም አሁንም ከፍተኛ የሆነ ምርት ከውጭ እየገባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሀገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ያለውን የገበያ ፍላጎት በሀገር ውስጥ አምራቾች መሸፈን ባለመቻሉ ነው ይላሉ፡፡

አቶ ንጋት እንደሚጠቁሙት፤ ያለውን የገበያ ፍላጎት ማሟላት ሳይቻል ጥሬ እቃ ወደ ጣልያንና ቻይና በርካሽ ዋጋ ይላካል፡፡ ነገር ግን በርካሽ ዋጋ የተላከው ጥሬ እቃ እሴት ተጨምሮበት ተመልሶ ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ ዋጋ ሲመጣ ደግሞ ይስተዋላል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት የዘርፉ የአዋጭነት ጥናቶች ተሰርተው እንደ አማራጭ የተቀመጡ አሉ፡፡ እነዚህን አሰራርና መረጃዎች ለባለሀብቱ የማድረስ ስራው አሁንም ብዙ እንደሚቀረው ይታመናል። ወደፊት ግን ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡

መንግስት ለማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ለዘርፉ በተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ይናገራሉ። ለአምራቾቹ የሰለጠነ ባለሙያ አስፈላጊ ከሆነ ከውጭ እንዲያስመጡ እድሉ እንደሚመቻችም ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ 70 በመቶ ያህል በሀገር ውስጥ ምርት እየተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፤ 30 በመቶ ያህሉ ብቻ ከውጭ በሚመጣው ምርት እየተሟላ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ የአምራች ፋብሪካዎች ቁጥርም ከ50 በላይ መድረሱንና ከእነርሱ መካከል 20 ያህሉ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው መለየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የተሰራ የማርብልና ግራናይት ፍላጎት ትንበያ ለመስራት ካሉት አማራጮች ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ሀገር ውስጥ የገባውና የተመረተውን ምርት መነሻ በማድረግ በየዓመቱ በተመዘገበው ዕድገት መሰረት ፍላጎቱ በአማካይ 5ነጥብ6 በመቶ እንደሚያድግ ያሳያል፡፡ ትንበያው እንደሚያመለክተው፤ በ2001 .ም የሀገር ውስጥ ፍጆታ 13 614 ሺ ቶን ሲሆን፣ በ2005 .ም ደግሞ ወደ 16 930 ሺ ቶን ከፍ ብሏል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚናገሩት፤ በዘርፉ ያለው ችግር ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራበትና መላ የማይፈለግ ከሆነ፣ እየጨመረ ከሚሄደው የገበያ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን አቅርቦት እንዳይኖር ያደርጋል፤ በተጨማሪም ሀገሪቱን አለአግባብ ለከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ይዳርጋታል፡፡ ማትረፍ የሚቻልበት እድል እያለ ተጨማሪ ወጪ መውጣቱም ይቀጥላል፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።