ከወርቃማው ህገ መንግሥት ጀርባ ያሉ ግጭቶች መንስኤና መፍትሄ Featured

የምክር ቤቱ አባላት ለውይይት በቀረበው እቅድ ላይ አስተያየትና ጥያቄ ሰንዝረዋል፤

 

ዜና ሐተታ

በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክ ራሲያዊ አንድነት፣ ህገ መንግሥት አስተምሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ለምክር ቤቱ አባላት የ2010 .ም እቅዱን ለውይይት አቅርቧል። በዋናነት መነሻ ያደረገው የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ሲሆን፣ ሁኔታዎችንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ ነው። የምክር ቤቱ አባላትም ለውይይት በቀረበው እቅድ ላይ አስተያየታቸውንና ጥያቄያቸውን ሰንዝረው ከተወያዩ በኋላ እቅዱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

በርካቶቹ የምክር ቤቱ አባላት ሲያነሱ የነበረው ጥያቄ የሚያጠነጥነው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ባለው ግጭት ዙሪያ ነው። ለግጭቱ መንስኤ ናቸው ብለው የሚያምኑትም የህገ መንግስቱ በተገቢው መንገድ በህዝቡ ውስጥ ያለመስረጹን ነው። ከህገ መንግስት አስተምሮና ስርፀት አንጻር ኮሚቴው እስካሁን ከሰራቸው ተግባራት መካከል ህገ መንግሥት አሳትሞ በማሰራጨት በኩል የተሻለ የተጓዘ ቢመስልም ስርፀት ላይ ግን እንቅስቃሴዎች የተዳከሙ ስለመሆናቸው ነው የሚያመለክቱት። የህገ መንግሥት ስርፀት ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ሊያመክን የሚችል በመሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶት አለመሰራቱን ይናገራሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው ግጭት ህዝብን እያንገላታና ከቀዬውም እያፈናቀለው ከመሆኑም በላይ ለቀጣይ ትውልድም ጭምር ቅራኔን እያስቀመጠ እንዳይሄድ ቀድሞ በመከላከሉ በኩል የተጠናከረ ሥራ መሰራት እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት ያስረዳሉ። በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም ምን ያህል ትውልዱን አንጿል? ምን ያህልስ ቀርጾታል? የሚለው ጉዳይ ታይቶ ለውጥ ከሌለ እንደገና ሊቃኝ ይገባዋልም ይላሉ። የህጉን መሰረት ዜጋው ገና ከጅምሩ የሚረዳ ከሆነ አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች ይወገዳሉ የሚልም እምነት አላቸው።

እንደ ምክር ቤቱ አባላት አባባል፤ በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው እየታየ ያለ ግጭት ሲያጋጥም የእሳት ማጥፋት ሥራ መስራቱ አያዋጣም። ግጭቶቹ ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ በመከላከሉ በኩል በጣም ድክመት ይታያል። ግጭቶቹ በአብዛኛው ሊከሰቱ የሚችሉት በፀረ ሰላም ኃይሎች እንደመሆናቸው ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጡ በኩል አልተሰራም። በተለያዩ ኃይሎች ግፊት በሚፈጠሩ ግጭቶችም አርሶና አርብቶ አደሩ በመቸገር ላይ ከመሆኑም በተጨማሪ ልማትንም በማደናቀፍ ላይ ነውና ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ያሻዋል።

በህገ መንግሥቱ ላይ እየተካሄደ ያለውን ጥሰት በተመለከተ ኮሚቴው ምን እያደረገ ነው ? ሲሉም ይጠይቃሉ። ግጭቶቹ መቃለል ሲገባቸው እለት እለት እየበረከቱ የመምጣታቸው ጉዳይ ድክመት ሆኖ ይታያልና ለዚህ መፍትሄ ለማበጀት ምን ያህልስ ርቀት መጓዝ ተችሏል? በማለትም ጥያቄያቸውን ያክላሉ። በኦሮሚያ ክልል እና በሱማሌ ክልል እየታየ ያለውን የቅርቡን ክስተት ለአብነትም ይጠቅሳሉ። በዚህ ዓይነት አካሄድም ወርቃማ የሆነው ህገ መንግስት ፈተና ውስጥ መግባቱ እንደማያጠራጥር ነው የሚያመለክቱት።

የምክር ቤቱ አባላት፣ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ያልተማረ እንደመሆኑ የህገ መንግስት ግንዛቤን ከማስጨበጥ አኳያ እንዴት ሊሰራ ታስቧል ሲሉ ይጠይቃሉ። በአሁኑ ወቅት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ደግሞ መንስኤያቸው የመልካም አስተዳደር እጦት ወይስ የስልጣን ፍላጎት የፈጠረው ሽኩቻ ነው የሚለውን በመለየት እውነታውን ማሳወቅም የተገባ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ግጭትን በመፍታቱ በኩል እንከን የሌለበት ህገ መንግስት ጎን ለጎን የየብሄረሰቡ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትም ቢካተት በማለት አስተያየት የሰጡ አባላት አልታጡም።

ሁሉንም ጠያቂዎችንና አስተያየት ሰጪዎችን የምክር ቤት አባላት ያስማማው ጉዳይ ቢኖር ወርቃማው ህገ መንግሥት ለግጭት መንስኤ ናቸው የተባሉትንም ችግሮች ሁሉ መፍታት እንደሚችል ነው። ይሁንና ዜጎች በህገ መንግሥቱ ላይ ያላቸው ግንዛቤ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ችግሮች በመፈጠር ላይ ይገኛሉና ህዝቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረጉ በኩል አፋጣኝ ሥራዎች ሊከናወኑ ይገባል ባይ ናቸው።

በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዙሪያ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑትና በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾሙት ካሳ ተክለብርሃንና የቋሚ ኮሚቴው ፀሐፊ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሄርን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል። አስተያየትና ጥያቄ እንዳቀረቡት የምክር ቤቱ አባላት ሁሉ እነርሱም ህገ መንግሥቱን ከማስረጽ አኳያ ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች አለመሰራታቸውን ይናገራሉ። እንደእነርሱ አገላለጽ፤ አሁን ያለው ትውልድ ወርቃማ የሆነ ህገ መንግሥት እንዳለ ከመናገርና ከማወቅ በስተጀርባ ምን ምን ይዘቶችን አካቷል ተብሎ ቢጠየቅ ምንም ምላሽ እንደሌለው መረዳት ተችሏል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ኢትዮጵያን ከመበታተንና ከእልቂት ያዳነ በመሆኑ የህዝቡ ህልውና ነው ሲሉ ያመለክታሉ። በመሆኑም በመተግበሩም ሆነ በማስተግበሩ በኩል የቋሚ ኮሚቴው የቤት ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የምክር ቤቱ አባላት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻዎችም ጭምር መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባው ነው የሚያሳስቡት። በአባላቱ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ወደ ውጭ የመግፋት ያህል መሆኑንም አመልክተው፤ ሁሉም ለተፈጻሚነቱ የበኩሉን ሊወጣ ግድ እንደሆነ ያስረዳሉ። የምክር ቤቱ አባላት ሁሉ የህዝብን ጥያቄ ታጥቀው የሰማዕታትን ተልዕኮ ደግሞ አንግበው መጓዝ እንዳለባቸው ነው የሚያሳስቡት።

በተለይ በበጀት ዓመቱ ከተያዙት እቅዶች መካከል አንዱ የህገ መንግስት አስተምህሮ ስትራቴጂ ሰነድ ጸድቆ ተግባር ላይ እንዲውል በማድረግ በኩል ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል። በሰነዱ ላይም የልህቀት ማዕከላት ተብለው የተለዩ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በስትራቴጂው አፈጻጸም ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱም ይጠበቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በየደረጃው ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል። 25 ሺ የህገ መንግስት ቅጂዎችም ታትመው እንደሚሰራጩ ተጠቁሟል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ቱት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አንድ አገር ወርቃማ የሆነ ህገ መንግሥት በማርቀቅ ማውጣት ብቻ በቂዋ አይደለም። የቱንም ያህል ህገ መንግሥቱ ምርጥ ቢሆንም ግንዛቤው በህዝቡ ዘንድ ካልሰረጸ ከበስተጀርባው ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው። ይህ እንዳይሆን አፈጻጸሙ ላይ የሁሉንም ትኩረት ይሻልና መረባረብ ግድ ይላል።

የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ ወይዘሮ ፍሬወይኒ እንደሚሉት፤ አሁን እየተከሰተ ላለው ግጭት መነሻው የህገ መንግሥት ስርፀት በአግባቡ ያለመካሄዱ ነው። ሰነዱ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ከወጣና መመሪያ ከተዘጋጀለት በኋላ ወደትግበራ ስለሚገባ ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት አላቸው። የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት አሰጣጥን በተመለከተም ካሪኩለሙ እንደገና እንዲሻሻል ሥራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ። ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉትንም የግጭት ካርታ ጥንክር ሥራ በአግባቡ ሊሰራ ይገባዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ካሳ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ተልዕኮው ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉትን ሥራዎች እንዲሰራ አይጠበቅበትም። አብዛኛዎቹ ሥራዎች በክልሎችና በአስፈጻሚ አካላት የሚከናወኑ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች መካከል ስምምነት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በመካከል ደግሞ ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል። ህግ የጣሰው አካል ወደህግ እንዲቀርብ ሥራ እየተሰራ ቢሆንም፣ ህገ መንግሥት ስርፀት ላይ አጥብቆ መስራት ግን ዘላቂ መፍትሄን የሚያመጣ መሆኑ አይካድም።

 

አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።