የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለውሃ መቆራረጥ ተጠያቂ ተደረገ

 

ለኃይል አቅርቦት ከዓመት በፊት 21 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በከተማዋ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የውሃ አገልግሎት መቆራረጥ ችግር ለመፍታት «ለውሃ መገኛ ጉድጓዶችና ማሰራጫ ጣቢያዎች ብቻ ሀይል የሚሰጥ መስመር እንዲዘረጋ ከአንድ ዓመት በፊት የ21 ሚሊዮን ብር ክፍያ ቢፈጸምም አገልግሎቱ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመቅረቡ ተደጋጋሚ የሆነ የውሃ ስርጭት መቆራረጥ ሊያጋጥም ችሏል» ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተጠያቂ አደረገ፡፡

ባለስልጣኑ ትናንት ለዝግጅት ክፍሉ ባደረሰው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት ዓመታት በውሃ አቅርቦቱ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ቢታይም ከውሃ ምርትና ስርጭት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ በሚያጋጥም የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ምክንያት ትልቅ ተግዳሮት ተፈጥሯል፡፡ ችግሩን ለማቃለልም 80 ጀነሬተሮችን ቢተክልም መፍታት አልተቻለም፡፡

ከአቃቂ ከርሰ ምድር በቀን ከሚመረተው 230ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ተጠቃሚ የሆኑ የመሃል አዲስ አበባ፣ ምዕራብ አዲስ አበባ እና ደቡብ አዲስ አበባ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ለቀናት የሚቆይ የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ማጋጠሙ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም በለገዳዲ የግፊት ጣቢያዎችም ተመሳሳይ የኃይል መቆራረጥ በማጋጠሙ የምስራቅ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ለውሃ አቅርቦት እጥረት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከተማዋ የተከሰተውን የውሃ መቆራረጥ ችግር ህብረተሰቡ ላይ የፈጠረውን ጫና ተገንዝቦ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ ለተደጋጋሚውም ችግር ባለስልጣኑ ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያና ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም፡፡

 

ብሩክ በርሄ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።