የግንባታ ቦታዎች አደጋን ለመቀነስ የመግባቢያ ሰነድ ሊፈረም ነው

 

የሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅና የአካል ጉዳተኞች የህንፃ ተደራሽነት ለማጠናከር የሚስያችል የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር ሊፈራረም መሆኑን አስታወቀ፡፡

የሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት፤ የመግባቢያ ሰነዱ አገሪቱ በ2007 .ም ያወጣችውን ብሔራዊ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲ በአግባቡ ወደመሬት አውርዶ ለማስፈጸም የሚያስችል ይሆናል፡፡

የሙያ ደህንነትና ጤንነት መጠበቅ የሁሉም አካላት ኃላፊነት መሆኑን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በየዘርፉ ፖሊሲዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ እስኪቻል ድረስ የሚፈረመው መግባቢያ ሰነድ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እየተሰማራ የሚገኘውን የሰው ኃይል ለመታደግ የሚያስችል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዘርፉ ላይ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል፡፡

ከግንባታ ዘርፍ ባሻገር ከመንግስት ትኩረት ጋር በተያያዘ በአምራች ዘርፉ በተለይም በኢንዱስትሪ መንደሮች አካባቢ የሰራተኞች መብት ጥበቃ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ብሔራዊ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲ በ2007 .ም መውጣቱን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲውን ተፈፃሚ ለማድረግ ደንብና መመሪያዎች ቢዘጋጁለትም ከሰራተኞች የግንዛቤ ማነስና ከአሰሪዎች ቸልተኝነት ጋር በተያያዘ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ መስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በግንባታ ቦታዎች ከማስተዋል የጥንቃቄ ጉድለት ጋር በተያያዘ ለሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት እስከመሆን የደረሱ የተለያዩ አደጋዎች መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ በተያዘውም ዓመት ከቀናት በፊት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህንፃ መወጣጫ መናድ ምክንያት በ12 የግንባታ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ተከስቷል፡፡ በሌላም በኩል በየአካባቢው የሚገነቡ ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ አለመሆናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎቹን ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርጓቸው ይስተዋላል፡፡

 

ብሩክ በርሄ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።