ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ምርቶች 47 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል Featured

ወደውጭ ከሚላኩት ምርቶች መካከል የሞባይል ስልኮች ይጠቀሳሉ

 

2009 .ም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ንኡስ ዘርፍ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 47 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ።

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በ2009 በጀት ዓመት በዘርፉ 75 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ 47 ነጥብ 9 ዶላር ተገኝቷል። ከተገኘው ገቢ 90 በመቶ ድርሻ ያላቸው የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ምርት ውጤቶች ናቸው።

«በበጀት ዓመቱ በታቀደው መሰረት ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ አልተቻለም። ግብዓቶች ከውጭ ስለሚመጡ በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ጥሬ እቃ ለማግኘት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነበረብን» ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የዘርፉን ምርቶች ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ የመላክ ልምድና ተሞክሮ አለመኖሩን ገልፀዋል። እንዲሁም ገበያ አፈላልጎ መግባት ላይም ክፍተት በመታየቱ አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል። ኢንዱስትሪዎች ምርቶቹን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ የመወሰን ፍላጎት ማሳየታቸውም ሌላው ችግር እንደነበር አመልክተዋል።

በዘርፉ በእቅዱ መሰረት ገቢ ባይገኝም በየዓመቱ ዕድገት መኖሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በ2010 በጀት ዓመት ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 126 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ወራት ውስጥም በኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር እና በብረታብረትና ኢንጂነሪግ ምርቶች 287 ሺ ዶላር ለማግኘት እቅድ ተይዞ በሁለቱም ዘርፍ አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ወደ ውጭ መላኩን አስረድተዋል። ይህ ከ2008 .ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ 17 በመቶ ብልጫ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ፊጤ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ሞባይል ስልኮች፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን ኬብሎች እንዲሁም የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ምርቶችን ትልካለች። የምርቶቹ መዳረሻ አገራት ኬንያ፣ ቶጎ፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመንና ስዊድን ናቸው፡፡

ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዘርፉ በ2006 .ም በዋናነት ገቢ ምርቶችን ለመተካት አላማ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በወቅቱም ሦስት ሚሊዮን 189 ሺ ዶላር ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ተገኝቷል፡፡ በሂደት የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ከመተካት ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እየተሰራ ይገኛል፡፡

 

ዳንኤል በቀለ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።