ግብርናው ለወጣቱ የፈጠረው የሥራ ዕድል አነስተኛ ነው ተባለ

 

በግብርናው ዘርፍ ለወጣቱ የተፈጠረው የሥራ ዕድል አነስተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ በ2009/10 የምርት ዘመን የአምስት ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ማዳበሪያ ሥርጭት ማድረጉ ለመኸር ምርቱ ውጤታማነት እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴሩ የ2009/10 ምርት ዘመን ሥራዎች አፈጻጸም አስመልክቶ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሃ እንዳሉት፤ ግብርናው እስካሁን ባለው ሁኔታ በሜካናይዜሽን፣ በችግኝ ማፍላት፣ በዘር ማባዛት፣ አንዳንድ ክልሎች ባለሃብቶች ያልተጠ ቀሙባቸውን መሬቶች ለወጣቱ በማስተላለፍ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ አበረታች ቢሆንም፤ ዘርፉ ለወጣቱ መፍጠር ከሚገባው የሥራ ዕድል አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየቱ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡

ሚኒስቴሩ አክለው በቀጣይ የተሻለ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በመስራት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፤ ወጣቱን አደራጅቶ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመስኖ እንዲያለማና ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርጉ አሰራሮችን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፤ በ2009/10 ምርት ዘመን የአምስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ስርጭት ተደርጓል። የማዳበሪያ ዋጋው ከአምናው ከ300 እስከ 350 ብር በኩንታል የቀነሰ ሲሆን፤ ለመኸር ምርቱ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከማዳበሪያው ባሻገር አርሶ አደሩ በግብዓት አጠቃቀም ላይ ስልጠናዎችን መውሰዱ፣ ሰብሎችን በክላስተር በማደራጀት መዝራት መቻሉና የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም መደረጉ 50 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንዲገኝ ይረዳል፡፡

 

ዑመር እንድሪስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።