የጥልቅ ተሃድሶ እርምጃ ከየት ወዴት? Featured

ዜና ትንታኔ

ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ማድረጉ ይታወሳል። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮችና ፈፃሚዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው። ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በሚወሰዱ እርምጃዎችና በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ላይ ምሁራኑ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ካሳሁን እንደሚናገሩት፤ በአገሪቷ እየታዩ የሚገኙትን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ማድረጉ እና እርምጃዎች መቀጠላቸውን ይገልፃሉ። በሥልጣናቸው ያለአግባብ የተጠቀሙ እና ሥራቸውን ችላ ያሉት ላይ በተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች እንዲሁም በከተሞች ደረጃ እርምጃ መወሰዱ እየተገለጸ ይገኛል።

‹‹የህግ የበላይነት ላይ የመሸርሸር ክፍተት አለ›› የሚለውንም መንግሥት እየተቀበለው ነው። በመሆኑም እርምጃው መወሰዱ አግባብነት አለው። ነገር ግን የእርምጃው ቀጣይነት ሲታሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል። በተለይ የመንግሥትን እርምጃ ተከትሎ ከኃላፊነት የማንሳት፣ በቁጥጥር ስር የማዋል እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች ላይ ጥፋተኞችን በተጣራ ማስረጃ በማረጋገጥ ንጹሃን ዜጎች ያለአግባብ እንዳይጎዱ እንዲሁም ተጠያቂዎች እንዳያመልጡ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚያጠኑት አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ እንደሚገለጹት ደግሞ፤ ከጥልቅ ተሃድሶ እርምጃዎች በዘለለ የመንግሥት መዋቅራዊ አሰራር ሊጠና ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሰራሩ በራሱ ሙስና እና በሥልጣን ያለአግባብ መበልጸግን የሚደግፍ ተቋማዊ ይዘት አለው። ለአብነት የመንግሥት መዋቅር ተጠቅሞ ያለአግባብ በሥልጣኑ የሚጠቀም ፈጻሚ ተበራክቷል።

የችግሮቹ ምክንያት ሲቃኝ የተጠያቂነት ሥርዓት አለመጠናከሩን ያሳያል። የመንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ጀምሯል፤ ጥልቅ ተሃድሶ ግን ሰዎችን ማሰር ብቻ መሆን የለበትም። ሰዎችን የሚያስራቸውና የሚያስወግዳቸው የአሰራር ሥርዓት መኖር አለበት። በመሆኑም አስፈጻሚው አካል ተጠያቂ መሆኑን የሚያጠናክር ተቋማዊ አሰራር ማስፈን ያስፈልጋል።

ሰዎች በአሁኑ ወቅት እየተጠየቁ ነው የሚሉት አቶ ካህሳይ ለምን ይጠየቃሉ? ብሎ መናገር በእራሱ ወንጀል መሆኑን ይገልፃሉ። አጥፊዎች መጠየቅ አለባቸው ነገር ግን ተጠያቂዎቹ በአንድ ወቅት ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ በሚከናወን ሥራ ብቻ ላይ መጠየቅ የለባቸውም፡፡ አንድ ግምገማ ስለተደረገ ብቻ መፍትሄ ይመጣል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ያስረዳሉ።

እርምጃዎችን መውሰድ በጊዜያዊነት ያጠፉትን ለመቅጣት እና በቀጣይ ህዝብን የሚበድሉትን ለመከልከል ይረዳል። ነገር ግን የፖለቲካል አሰራር ሂደቱን ማስተካከል ካልተቻለ ሰዎችን መቀየር እና ጥቂቶችን መቅጣት ብቻ ትርጉም አይኖረውም ይላሉ። በመሆኑም የፖለቲካል ሥርዓቱ ኃላፊዎች በህዝብ የሚገመገሙ፤ በህዝብ የሚመረጡ እና የሚሻሩ እንዲሆኑ እስካላስቻለ ድረስ አሁን እየተሄደበት ያለው አሰራር ረጅም ርቀት እንደማያስ ጉዝ ይገልፃሉ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተሾመ እሸቱ፤ ችግር በፈጠሩ ኃላፊዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው የሚል የግል አስተያየት እንዳላቸው ይናገራሉ። መንግሥት የባለሥልጣናት ያለአግባብ የሥልጣን አተያይ ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል፤ ስጋታቸውን ያስቀመጡ አመራሮች መኖራቸውን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየገለጸ ይገኛል።

ችግሩን ለመቅረፍም ጥልቅ ተሃድሶ እንደሚያስፈ ልግ በማመን የተለያዩ እርምጃዎችን በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችን እና አመራሮችን በማንሳት በሌሎች አመራሮች እንዲተኩ ተደርገዋል። ለአብነት የግል ሥራ አፈጻጸማቸው የተለያየ ቢሆንም የሚኒስትሮች ካቢኔ በ2009 .ም እንደ አዲስ እንዲዋቀር መደረጉ የሚታወስ ነው።

ነገር ግን የእርምጃ ሂደቱ ፈጣን መሆን አለበት። አሁን ላይ በግልጽ ያለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያመለክተው፤ ህብረተሰቡ በመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት በከፍተኛ አሉታዊ በሆነ ስሜት ውስጥ ይገኛል። በተለይ ችግሮች በገዘፉበት ጊዜ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ፋይዳ የላቸውም ባይባሉም ህብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እርምጃዎቹ በቂ ናቸው ብሎ መናገር አይቻልም በማለት በተቻለ መጠን ከጊዜ ጋር መራመድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ብርሃኑ መፍትሄ የሚሉትን ሀሳብ ሲያብራሩ፤ በተቻለ መጠን የጥልቅ ተሃድሶው እርምጃዎች አሳማኝ፣ በተጠኑ እና በተደራጁ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ሆነው ቀጣይነት ባለው መልኩ መከናወን ይገባቸዋል። በተለያዩ ጉዳዮች በተካሄዱ ግምገማዎች ላይ ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ አካላትን በመውሰድ ብቻ ወደ እርምጃ ከመሄድ በፊት በጉዳዩ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም ከህብረተሰቡ የተጠናቀሩ መረጃዎች በአግባቡ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል። አሳማኝ እና የተጣራ መረጃ ለማግኘት በእርምጃዎቹ ሂደት ህዝቡን በየደረጃው ማሳተፍና የመፍትሄው አካል ማድረግ ይገባል።

መንግሥትም በበኩሉ በስሩ በሚገኙ መዋቅሮች አማካኝነት የተጣሩ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለዘላቂ መፍትሄዎች መንገድ መቀየስ አለበት። ለአብነት ፍርድ ቤቶች እና የህግ አስከባሪ ተቋማት እርምጃ እንዲወሰድባቸው በቀረቡ አካላት ላይም ሆነ በእለት ተዕለት አገልግሎታቸው ውስጥ ፈጣን ምላሽ እና በአጭር ጊዜያት ውስጥ አቤቱታዎችን የሚያደምጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ይህም የተጣሩ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ እርምጃዎችን ለማከናወን እንደሚረዳ ያስረዳሉ።

አቶ ተሾመ በበኩላቸው፤ መንግሥት ችግሮቹን ለማስተካከል በጥልቅ ተሃድሶ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በወቅቱ የሚፈጸም፣ ሰፊ መዳረሻዎች ያለውና ስር ነቀል ሊሆን እንደሚገባው ያስረዳሉ። በሁሉም ተቋሞች ውስጥ ያሉት ችግሮች መንስኤያቸው ላይ ውይይት በማድረግ እንደ ጉዳያቸው ክብደት የሚመጥነውን ተገቢ ጊዜ በመለየት መፈታት መቻል አለበት። ለስር ነቀል ለውጡም ከአዳራሽ ውስጥ ጥፋቶችን አውግዞ እንደሚወጣ ሁሉ ከስብሰባ ውጪ በተግባር ምን ለውጥ እየታየ ነው የሚለውን መገምገም አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃሉ።

እንደ አቶ ተሾመ ትንበያ ከሆነ፤ እርምጃው በርካቶችን ያማከለ ስር ነቀል ለውጥ ካልሆነ ግጭቶች የመበራከት እድላቸው ሰፊ ይሆናል። በችግሩም የአገሪቷ ልማቶች እንዲቆሙ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲፈራርሱ ያደርጋል። ችግሩም የበርካቶችን ህይወት መጥፋት ሊያስከትል የሚችል አደጋ በመሆኑ የእርምጃ ሂደቱ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዶክተር ብርሃኑ በበኩላቸው፤ አንዳንድ ጊዜ በጥድፊያ እና በዘመቻ መልክ የሚከናወኑ ሥራዎች ችግር ፈጣሪዎች ተለይተው እንዳይቀጡ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በአገሪቷ በሚታዩ ችግሮች ውስጥ እጃቸው የሌሉ ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚደረጉበት ሁኔታ እንዲፈጠር በር ይከፍታል ብለዋል።

የተጣራ መረጃ በሌለበት ሁኔታ እና አንድ ወገን ተነስቶ ሌላኛውን በግምገማ መልክ ተጠያቂ የሚያደርግበት አሰራርን ተመርኩዞ ወደ እርምጃ የሚሄድ ከሆነ ንጹሃን ላይ የሚያሳርፈው ጉዳት ይከፋል። በተጨማሪም በአግባቡ መጠየቅ የሚገባቸው አጥፊዎች እንዲያመልጡ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ማስረጃዎችን በጥናት ላይ የተመረኮዙ ማድረግ አስፈላጊ እና ወሳኝነቱ የጎላ ነው ብለዋል።

አቶ ካህሳይ ደግሞ፤ ሰዎች በመረጃ እና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ሊታሰሩ ይችላሉ። በአንጻሩ ባልተጣራ መረጃ ላይ ተመስርቶ ከታሰሩ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት ተጠያቂነት ይዘት ሊኖረው ይገባል። አሰራሩ ካልተስተካከለ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ በተባባሰ ሁኔታ ሊቀጥሉ ይችላሉ። የጠራ መረጃ እንዲኖር ህዝቡን የመፍትሄው አካል እና የሂደቱ አካል እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ይህ ካልተደረገ ግን በቀጣይ የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ችግሮችን ለማስተካከል ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል።

 

ጌትነት ተስፋማርያም

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።