የንግድ ትርዒቶቹና ባዛሮቹ ትርፍና ኪሳራ Featured

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ የንግድ ትርዒቶቹ በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ፣የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅና በመሳሰሉት አገሪቱን ምን ያህል ተጠቃሚ አድርገዋል በሚለው ላይ ግን ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች የተለያየ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድ ትርዒትና የኩነት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ወይዘሮ ባዝግናወርቅ ወልደመድህን በንግድ ትርዒትና ባዛሮቹ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡የአገር ውስጥ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅም ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል ይላሉ፡፡

ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒትና ባዛር ማዘጋጀት የጀመረው በትንንሽ ኢንዱስትሪዎች መሆኑን በማስታወስም አሁን ከ200 የማያንሱ ትልልቅ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ የተሳታፊዎች እና የሚቀርቡት የቴክኖሎጂ ውጤቶችም መጨመራ ቸውን ይጠቁማሉ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሲኒየር ኦፊሰር አቶ አየለ ገላና ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ ምርትና አገልግሎት ከሚያስተዋ ውቅባቸው መንገዶች አንዱና የገበያው ሞተር ተብሎ የሚታመንበት የንግድ ትርዒት መሆኑን ይጠቅሳሉ። አብዛኛዎቹ የንግድ ትርዒቶች የወደፊት ደንበኞችን ለማግኘት እንዲሁም ስምምነቶችን ለመጨረስ የሚደረጉ እንጂ «የተወሰነ ነገር ሸጬ እጠቀማለሁ» የሚል እሳቤን ያነገቡ አይደሉም ይላሉ።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በኢንቨስትመንት የመሳተፍ እንዲሁም ባሉበት አገር ሆነው ምርት ለመላክ ቅርንጫፎችን የመክፈትና ወኪሎችን የማዘጋጀት ሥራም በብዛት መከናወኑን ፣ ከዚህም የውጭ ሀገር የንግድና ባዛር ተሳታፊዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የሚመሰርቱት የቢዝነስ ግንኙነት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይጠቅሳሉ።አዳዲስ ቴክኖሎጂዎቻቸው ለአገር ውስጥ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን ለጎብኚዎችም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ያብራራሉ ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና አብዛኞቹ የውጭ ባለሀብቶች በንግድ ትርዒቶቹ በመሳተፍ ሸጬ እጠቀማለሁ የሚል አላማ ያነገቡ አይደሉም በሚለው የአቶ አየለ ሃሳብ አይስማሙም ፡፡ከውጭ ባለሀብቶቹ አብዛኞቹ «እንደዚህ ዓይነት እቃ አለን፤ግዙን» የሚል መልዕክት ማስተላለፍ አንዱ አላማቸው መሆኑን ያመለክታሉ።

ባለሀብቶቹ ለመሰሎቻቸው ቴክኖሎጂና እውቀት አስተላልፈዋል አላስተላለፉም ብሎ ለመናገር ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ፤ይህ ሲባል ግን ምንም አልጠቀመንም ማለት አይደለም ፤‹‹የምናስበውን ያህል ተጠቅመ ንበታል ወይ የሚለው ግን ያነጋግራል›› ሲሉ ይገልጻሉ።

የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ የወይዘሮ ባዝግናወርቅን ሃሳብ በመጋራት እስከ አሁን በተካሄዱት የንግድ ትርዒቶች ምርቶቻቸውን ሲያዘጋጁ ፣ሲያከማቹ ፣ሲያጓጉዙ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ ፣ለምርቱ ጥራት የሚያደርጉት ጥንቃቄ በተሞክሮነት መወሰዱን ይጠቅሳሉ፡፡ በንግድ ትርዒትና ባዛሮቹ አማካይነት ይህንን ቴክኖሎጂ ቀስመን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል ለማለት የሚያስችል ጥናት እንደሌለ በመጥቀስ የኢኮኖሚ ባለሙያውን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

‹‹የውጭ ባለሀብቶች የሚመጡት ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ነው፤የእኛ አላማ ቴክኖሎጂዎቻቸውን መቅሰም፣ በአገር ውስጥ አቆይተን እዚሁ አምርተው ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡም ይሁን ወደ ውጭ እንዲልኩ ማስቻል ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ባዝግናወርቅ፣ በዚህ መንገድ መጥተው በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ያሸጋገሩ ባለሀብቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ይህ ወደፊትም በጥናት በተደገፈ ሁኔታ መቀጠል እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፡፡

የውጭ ኩባንያ ምርትና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ሲመጣ ለሆቴል ኢግዚቢሽን ለሚታይበት ቦታ የሚያወጣው ገንዘብ ብሎም ለሥራው ሰዎችን እንደሚቀጥር የሚጠቅሱት ወይዘሮ ባዝግናወርቅ፣ ይህም ለአገሪቱ ትልቅ ትርፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ከሁሉም በላይ ግን እነሱን በመሳብ ባለሀብት ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ወደፊት ይህን መሰሉ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲበረታታ የማሳያ ቦታዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ግንኙነትን ማጥበቅና አሰራሮችን ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና የውጭ ባለሀብቶች ከንግድ ትርዒት አልፈው ወደ ኢንቨስትመንት የሚሄዱበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መረጃዎችን ግንኙነቶችንና የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ከእኛ ይጠበቃል ይላሉ። በዚህ መንገድ መጥተው ውጤታማ የሆኑትን በማሳየትም አገሪቱን ይበልጥ ተመራጭ ማድረግ እንደሚቻል ያመለክታሉ።

በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እንደነ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራት በዓመት በርካታ ኮንፈረንሶችን ለማዘጋጀት መስራት ይገባል፤ በተለይም የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በመዲናዋ ላይ መኖራቸውን እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመጠቀም ጉባዔዎችን በማዘጋጀት ለንግድ ትርዒት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል የሚሉት አቶ አየለ፣ የመዲናዋን ምቹ ሁኔታዎች ማስተዋወቅ ፣ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እንደምትመች ለዓለም የሚያሳይ ተቋም መመስረትም የቤት ሥራ መሆን እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።

አቶ አየለ የወይዘሮ ባዝግናወርቅን ሃሳብ በማጠናከር ከአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋነት ፣ ምቹና ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የማሳያ ቦታዎች ፣ እንደ ዋይ ፋይ የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ አማራጮች በስፋትና በሚፈለገው ፍጥነት አለመኖር ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤት ጋር እያስገነባ ያለው «አዲስ አፍሪካ የኮንቬንሽን ሴንተር» በፍጥነት ተጠናቅቆ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ ፣ማንኛውንም ኤግዚቢሽንና ባዛር ማስተናገድ የሚችል የሀገሪቱን ኮንፈረንስ ማእከል መገንባት ሊተኮርበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

የኢኮኖሚ ባለሙያውም ከመሰረተ ልማት ጋር በማያያዝ ወይዘሮ ባዝግናወርቅ እና አቶ አየለ የጠቀሱትን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ፣የቴሌኮም እና የውሃና የመሳሰሉትን መሰረተ ልማት ችግሮች መፍታት ይገባል፣መንግሥትም ባለሀብቶቹን መሳቡን አጠናክሮ መቀጠል ፣አላሰራ የሚሉ ቢሮክራሲያዊ አካሄዶችንም መቀነስ ይኖርበታል ይላሉ።

ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአንድ የንግድ ትርዒት ብቻ ከአፍሪካ፣ ከኤሲያ፣ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ በዓመት ከ 12 እስከ 18 የሚሆኑ አገራት ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። በዚህም ከ97 እስከ 110 የሚደርሱ የውጭ ድርጅቶች ይሳተፋሉ፡፡ከ97 እስከ 100 የሚደርሱ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም የሚሳተፉ ሲሆን፤ ይህም በአምስት ዓመት ሲሰላ ከውጭ ከ 485 በላይ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ደግሞ እስከ 415 ተሳታፊዎች ይገኛሉ። ባለፉት 5 ዓመታት የተዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችን ከ 35 ሺ በላይ ሰዎች ተጎብኝተዋል።

አቶ አየለ የመሰረተ ልማትና የመሳሰሉትን ችግሮች ባልፈታን ቁጥር አሁንም በቂ ባልሆነ ሁኔታ እየመጡ ያሉትን ባለሀብቶች እስከነአካቴው እናርቃቸዋለን የሚል ስጋት አላቸው፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ከመሰረተ ልማትና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙትን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ ጊዜው የውድድር በመሆኑ ባለሀብቶቹን እናሸሻለን፤ መፍታት ከተቻለ ግን ባለሀብቶቹ የማይመጡበት ምንም ምክንያት አይኖርም ይላሉ፡፡ወደ ሀገሪቱ ከመጡም በኋላ ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚበረታቱ እና ለብዙዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻሉ ያመለክታሉ።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።