ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድርና የኢትዮጵያ ተደራዳሪነት Featured

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ አገራትን ድምፅ በማሰማትና በማስተባበር በዓለም መድረኮች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተች ትገኛለች። ከድርድሩ በተጓዳኝም የድርድሩ አካል የሆነውን የአረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ቀድማ በመተግበር አርአያ መሆን ችላለች።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ አገሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ድርድር በማስተባበርና በመምራት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ንቁ ተሳታፊ የምታደርግ አገር ናት። በተናጠልም ብቻ ሳይሆን በጋራ እየሠራች ትገኛለች።

በቅርቡ ጀርመን ቦን በተካሄደው የኮፕ 23 የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያሉ 47 አገራትን እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አገራት ቡድንን በሊቀመንበርነት መርታ የመሪነት ሚናዋን ተወጥታለች። በተጨማሪም የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድንም አባል ተሳታፊ ናት ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን አስተዋፅኦ የሚገልጹት።

ዶክተር ገመዶ፤ «ለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረገው የማጣጣሚያ ድጋፍ አስገዳጅነት፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ድጋፍ፣ ያደጉት አገራት የሙቀት አማቂ ጋዞችን የማስተካከያ ዕቅድ ማስገባት፣ የፓሪስ ስምምነት የማስፈጸሚያ ህጎች በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት፣ ግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥ እራሱን ችሎ የመወያያ አጀንዳ መሆንና ሌሎች አጀንዳዎች ኢትዮጵያ በድርድሩ በሊቀመንበርነትና በአባልነት የምትሳተፍባቸው ቡድኖች የያዙት የጋራ አቋም ነው። እነዚህ አጀንዳዎችም በተደረገው ብርቱ ጥረት ተቀባይነት አግኝተዋል» ሲሉም ነው የገለጹት።

በድርድር ላይ የአደጉት አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ 90 ሚሊዮን ዶላር፤ እንዲሁም ለአየር ንብረት ተጋላጭ ለሆኑ ታዳጊ አገራት 100 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ይሄም የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሩ ውጤት ማሳያ መሆኑን ዶክተር ገመዶ ያመለክታሉ።

በድርድሩ ከምታደርገው ንቁ ተሳትፎ በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልትን ነድፋ በመተግበር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ አስገኝቶላታል ይላሉ ሚኒስትሩ።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ፈንድ አስተባባሪ አቶ ዘርይሁን ጌቱም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በ20 ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ከአገር ውስጥ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከሁለትዮሽ ትብብርና ከሌሎች ምንጮች 150 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ይፋ ማድረጓን አቶ ዘሪሁን ይገልጻሉ። እንደ አገር በተደረገው ድርድርና ጥረትም በሁለትዮሽ ትብብር ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ያደረጉትን ድጋፍ ሳያካትት 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

እንደ አቶ ዘርይሁን ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በዕቅዷ ውስጥ በማስገባት መተግበር የጀመረች ሲሆን፤ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታዎች፣ የገጠሩ ህብረተሰብ የአርባ ቀን ነፃ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች ሥራዎችና የአረንጓዴ ልማትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑና ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኙና አርአያ የሆኑ ተግባራት ናቸው።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረትና የህብረተሰብ ጉዳዮች ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አማኑኤል ዘነበ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዜጎቿንና እንስሳቷን በመገበር ዋጋ ከፍላለች። ባላደረሰችው ችግር ዋጋ እያስከፈላት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም በአገር ውስጥ የአረንጓዴ ልማትን፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ችግሯን ለመቅረፍ እየሠራች መሆኑን ያብራራሉ። ይህም ዓለም አቀፍ እውቅና ሳይቀር ማስገኘት የቻለ ፍሬ አፍርቷል ነው የሚሉት።

የፎረም ፎር ኢንቫይሮሜንት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ገብሩ በበኩላቸው፤ ባለፉት 21 ዓመታት አገራት በተደረገው ድርድር በዓለም ታሪክ ትልቁና ታሪካዊ የሆነው የፓሪስ ስምምነት ተፈርሟል ይሉና፤ ይህንን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው የግንባር ቀደም ተደራዳሪነትና የጀመረችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥራ በዓለም በምሳሌነት የሚጠቀስ አድርጎታል ሲሉ የአገሪቷን አበርክቶ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ መሳተፍ የጀመረችው በታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ዘመን ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጉዳዩ ዙሪያ መሪ ተደራዳሪ በመሆን ጉዳዩን አብይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ችላለች፤ አፍሪካን ወክላ ዓለም አቀፍ ድርድሮችን አድርጋለች፤ በቀደሙት ዓመታትም በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

አቶ ዮናስም ሆኑ ዶክተር አማኑኤል፤ በቀጣይ ድርድሩ ብክለት በፈጠሩ የበለጸጉ አገራት እና ብክልት ሳያደርሱ ተጠቂ በሆኑ ታዳጊ አገራት መካከል የሚደረግ በመሆኑ ፈታኝ ነው ይሉና፤ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ጠንካራ ድርድር ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ። በድርድሩ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የሚሠሩ ሥራዎች መሬት ላይ የወረዱና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተመዝነው በመረጃ የተያዙ ማድረግ፣ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ማሰልጠን፣ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፣ የሚሠራውን ሥራ በትክክል ማስተዋወቅ እንደሚገባ ያነሳሉ። እአአ እስከ 2020 ተግባራዊ ከሚደረገው የፓሪስ ስምምነት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ድርድር አሁንም የጎላ ሚና መጫወት፣ የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር እና በአገር ውስጥ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ይላሉ።

በአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪው አቶ ቢኒያም ያዕቆብ፤ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር የሚተባበሩ አገራትን በማስተባበር፣ የተደራዳሪዎችን አቅም ማጎልበት፣ ድርድሩን ከብሄራዊ እቅድ ጋር ማጣጣም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በተግባር በተደራዳሪዎችና በድጋፍ ሰጪ አገራት ላይ የሚገለጽ ተጽዕኖ ለማሳደር ትሠራለች፤ እንደ አገርም ከድርድሩ የምታገኘው ጥቅም መጨመሩ አይቀርም ብለዋል።

ሚኒስትሩና ምሁራኑ፤ እስከአሁን በተካሄደው ድርድሩ የተገኙ ውጤቶች መልካም ቢሆኑም በቀጣይ በጠንካራ ትብብር መሥራት ይገባል የሚለውን ይጠቅሱና፤ ይህ ተግባሯ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ እስከአሁን ካገኘችው የገንዘብ ድጋፍ በላይ በቀጣይ እንደምታገኝ ትንበያቸውን ያስቀምጣሉ። እንደ አገርም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፤ አገሪቱ የምትፈልገውን ድጋፍና ውጤት ማግኘት እንደምትችል እምነት አላቸው።

 

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።