የእንስሳት ቁጥር መጨመር እና የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ስጋት Featured

ዜና ትንታኔ

ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጨመር ምክንያት ከሆኑት መካከል የግብርና ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር ያላቸው አገራት ዘመናዊ የአረባብ ሥርዓት ካልተከተሉ ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ጉልህ ደርሻ ያበረክታሉ፡፡ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የእንስሳትን ቁጥር መቀነስ ወይስ ዘመናዊ አረባብ መከተል የሚሉት በአማራጭነት ይነሳሉ፡፡

በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር የማይበገር አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተገኝ፤ የእንስሳት ቁጥር መጨመር ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጨመር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የእንስሳት ቁጥር ሲጨምር ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ከፍተኛ ድርሻ ያለው በተለያየ መንገድ የሚያመነጩት የሜቴን ጋዝ ከፍ ስለሚል ነው፡፡

አቶ ጌታቸው ከእንስሳት ለሚመነጨው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ልማዳዊ የእርባታ ዘዴ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በ2000 .ም ኢትዮጵያ ያላት የግጦሽ መሬት ከ61 እስከ 65 ሚሊዮን ሄክታር እና ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋት ደግሞ 53 በመቶ ድርሻ እንደነበረው በማብራራት፤ አሁን ግን ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ሄክታር መቀነሱን ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ‹‹የአገሪቱ የእንስሳት አመጋገብ ልቅ ግጦሽ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ መሬቱ ይጎዳል፡፡ የግጦሽ መሬት በተጎዳ ቁጥር ካርበን ወደ አፈር ውስጥ እንዳይገባና ወደ አየር እንዲለቀቅ ምክንያት ይሆናል›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚናገሩት፤ ከእንስሳት የሚመነጨው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእንስሳት የአረባብ፣ የአመጋገብና የአያያዝ ጥራት ጋር ይያያዛል፡፡ ለአብነት ከብቶች በልቅ ግጦሽ ሲሰማሩ የሚለቀቀው አዛባ ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በየወቅቱ እየተከሰተ ያለው ድርቅ ደግሞ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠን ከግብርናው የእንስሳት ሃብት ድርሻ ከፍ ማለቱ የሚያመጣው ተጽዕኖ እንዳለ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀት በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ የሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠን የግብርናው ዘርፍ ጨምሮ ከሌሎቹ አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የልቀት መጠኑ አነስተኛ መሆኑ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ያለው ተጽዕኖም የዛኑ ያህል ዝቅተኛ ቢሆንም ለአየር ብክለት አስተዋጽዖ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የልቀት መጠን አነስተኛ ስለሆነ ልቀቱ በእጥፍ ቢጨምርም ቢቀንስም በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚኖረው ፋይዳ ትንሽ ነው የሚሆነው›› የሚሉት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ የልቀት መጠኑ ምንም ያህል ቢሆን ያለውንም ለመቀነስ ቢሰራ የቴክኖሎጂ ሥራውን ሊደግፍ የሚችል የገንዘብ እገዛ ለመጠየቅ እንደ ዕድል መጠቀም እንደሚያስችል ይገልጻሉ፡፡

ፕሮፌሰር ወልደአምላክ የኢትዮጵያ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ድርሻ ከዓለም አንጻር የሚወዳደር ከሆነ አሳሳቢ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ካለው ኢኮኖሚ አቅም አንጻር እንዲሁም ሌሎች አገራት በለቀቁት ጋዝ ምክንያት ከሚፈጠረው ጫና ጋር ማወዳደር ተገቢ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹የእንስሳት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በአጠቃላይ የሃብት አጠቃቀምን ውጤታማ ከማድረግ ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡

አቶ ጌታቸው ግን ከእንስሳት የሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ ኢትዮጵያን ያሳስባታል ባይ ናቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አገሪቱ ከሌሎች ሲተያይ አጠቃላይ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቷ አነስተኛ ቢሆንም ድርሻ እስካላት ድረስ መጠኑ ምንም ያህል ይሁን ዞሮ ዞሮ ተጎጂዎቹ ደሀ አገራት መሆናቸው እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው፣ ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቱም ከፍተኛ ድርሻ ባለውና በልቀቱም መልሶ የሚጎዳው ግብርናው መሆኑ ነው፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ለችግሩ መፍትሄ የእንስሳት ቁጥር መቀነስ ሳይሆን የእንስሳት ቁጥሩ ባለበት እንዲቀጥል በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በልቅ ግጦሽ ላይ የተመሰረተውን አመጋገብ በመቀየር የመኖ አቅርቦት መጠንና ጥራት ማሳደግ፣ ከእንስሳት የሚገኘው ተረፈ ምርት መቀነስና እንስሳትን በፍጥነት ለገበያ ማቅረብ መፍትሄዎች ናቸው፡፡

የግጦሽ መሬት መንከባከብና የመኖ አቅርቦት ሥራ ላይ የባለሀብቶች ድርሻን ማሳደግ፣ ማንኛውንም የእንስሳት እርባታ ሥራን ከፍጆታ ወደ ቢዝነስ መቀየር፤ የእንስሳት ሃብት አስተዳደርን ከከባቢ አየር ጥበቃ ጋር ማያያዝ፣ ዘረፉን ታሳቢ ያደረጉ የምርምር ሥራዎች መስራት፣ የምርምር ማዕከላት ሰብል ላይ ብቻ ሳይሆን የእንስሳት ሃብት አስተዳደር አሰራርን ማሻሻል ላይም እንዲያተኩር በገንዘብ መደገፍ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ተቋማት የተያዘውን የበካይ ጋዝ ልቀት የመቀነስ እቅድ ለማሳካት በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ሚኒስቴር የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ባለሞያ አቶ አሳየ ከተማ፤ የሙቀት አማቂ ጋዝን በመልቀቅ ረገድ ከዓለም ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ድርሻ ዜሮ ነጥብ ዜሮ ሁለት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ግብርናው ደግሞ ለእዚህ 79 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

የግብርናው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ኢኮኖሚው በግብርናው ላይ በመመስረቱ የተፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አሳየ የግብርናውን ሥራ ሳይጎዳ ልቀቱን መቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡

‹‹የሙቀት አማቂ ጋዝ መቀነስ የግብርናውን ምርታማነት መቀነስ ማለት አይደለም›› በማለት የግብርና ምርት ማሳደጊያ መንገዶችን በመጠቀም ምርቱ እንዲጨምርና የጋዝ ልቀቱ ደግሞ መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ የተለምዶ የእንስሳት እርባታ አሰራሮችን መቀየር አንዱ መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም በሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ ከአንድ አገር ከሚጠበቀው በታች አነስተኛ ቢሆንም ትንሽ የሚባል እንዳልሆነ ወደ ፊት እየጨመረ እንደሚሄድ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡

‹‹አሁን ያለውን የልቀት መጠን ከወዲሁ ለመቀነስ ሳይሰራ እንደ ሌሎች አገራት የአየር ብክለት ጉዳት ካደረሰ በኋላ ለማስተካከል መሞከር ወጪው አቅም ይጠይቃል›› የሚሉት አቶ አሳየ፤ አንዱ አካል ምርትን ለመጨመር ሌላው ደግሞ አካባቢን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን የተናጥል ሥራ በማስቀረት እንዲሁም የሥራ ድግግሞሽን በመተው የሚወጣውንም ወጪ መቀነስ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ፋኦ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለዓለም የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ግብርና ሦስተኛውን ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል፡፡ እስያ፣ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ ድርሻ ደግሞ 81 በመቶ ነው፡፡ ከሦስቱ አህጉሮች ከግብርናው የሚመነጭ አማቂ ጋዝ መጠን ከ1990 እስከ 2010 .ም በ42 በመቶ ጨምሯል፡፡ በዓለም ያሉ እንስሳት የአማቂ የጋዝ ልቀት መጠን በየዓመቱ ሲሰላ ሰባት ነጥብ አንድ ጊጋ ቶን ካርበን ያህል ይሆናል፡፡ ለሥጋና ለወተት ምርት የሚረቡ የቀንድ ከብቶች ደግሞ 65 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ይህ ማለት ከአጠቃላይ አማቂ ጋዝ ልቀት 14 ነጥብ አምስት በመቶ ነው፡፡ መረጃው በእንስሳት ምክንያት የሚፈጠረው ልቀት በ28 በመቶ ከትራንስፖርት ዘርፉ ብልጫ እንዳለው ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ በ2002 .ም የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው ከእንስሳት የሚለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋዝ 65 ሚሊዮን ሜጋ ቶን ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴ ካልተተገበረ ከእንስሳት የሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠን በ2022 125 ሚሊዮን ሜጋ ቶን በላይ ይደርሳል፡፡ ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ባለሞያዎቹ እንደሚሉት ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከአሁኑ ለችግሩ መፍትሄ ካልተፈለገና የአማቂ ጋዝ ልቀት መጠኑን መቀነስ ካልተቻለ፣ የአካባቢ ብክለቱ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱ የግብርናው ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጠራል፡፡ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተው ድርቅ ጉዳቱ እንዲጨምር ተጽዕኖው በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ጤና፣ ኢኮኖሚ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል እንዳታሳካና፣ ያላትንም ተአማኒነት እንድታጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።