ክልሉ ለበዓሉ ታዳሚዎች የቱሪስት መስህቦቹን ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን ገለጸ

 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት በነገው እለት የሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች ክልሉ ያለውን ባህልና የቱሪስት መስህብ ለማስተዋወቅ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ገለጸ፡፡

የአፋር ክልል 12ኛው ዙር የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ አወል ኢብራሂም ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡ እንግዶች ማረፊያን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች የተጠናቀቁ ሲሆን፤ ክልሉ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻውን በዓል እንደማዘጋጀቱ በርካታ ተሞክሮን መቀመር ችሏል። በክልሉ ያሉትን መስህቦች ለበዓሉ ታዳሚ ለማስተዋወቅ የበዓሉ መከበር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በክልሉም እምቅ የማዕድን ሀብት እንደመኖሩ ልማትን ማከናወን ለሚፈልግ አካል የክልሉ በር ሁሌም ክፍት ነው።

ማረፊያን በተመለከተ መስተንግዶው እየተከናወነ ያለው በሦስት ደረጃ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፤ የመጀመሪያው የተለያየ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ሲሆኑ፣ በሁለተኛነት የተዘጋጁት ደግሞ እያንዳንዳቸው ሦስት ሰዎችን መያዝ የሚችሉና ባህላዊ የአፋር ቤቶች ከአምስት መቶ በላይ ተዘጋጅተዋል። በሦስተኛነት የተሰናዳው የተለያዩ ተቋማት ናቸው።

አቶ መሀመድ፣ ከተጠሩትም በላይ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ መታሰቡን ጠቅሰው፤ ተገቢውን መስተንግዶ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በደብዳቤ ጥሪ የደረሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዓሉንም መታደም የፈለገ የመምጣት መብቱ የተጠበቀ በመሆኑም «እንኳን ደህና መጣችሁ» ለማለት ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል። የሰው ዘር መገኛ ክልል እንደመሆናቸው ሁሉም የሚመጡት ወደራሳቸው መንደር ነው ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል።

እርሳቸው እንደገለጹት፤ ከሰላሙና ከፀጥታው አኳያ ክልሉ ምንም ዓይነት ችግር የለበትም። በዓሉ የአፋር ክልል አስተናጋጅ ይሁን እንጂ አስተባባሪው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደመሆኑ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን በመወጣት ላይ በመሆናቸው ምንም ስጋት አይኖርም። ክልሉም ቢሆን የራሱን ዝግጅት አድርጓል። እንግዶቹን መጠበቅ የጀመሩት ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ሲሆን፣በዛሬው እለትም ሲምፖዚየም ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል ሚቲካ በበኩላቸው፤ «በዓሉን ስናከበር በህገ መንግሥቱ የተገኙትን ትሩፋቶችን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን የክልሉን ገጽታ ለማስተዋወቅና ያለውን እምቅ ሀብት ለአልሚዎች ለማሳየትም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ጭምር ነው። ክልሉ በርካታ የቱሪስ መስህቦችም ያሉት ሲሆን፣ ሉሲ የተገኘችበት ክልል መሆኑ ይታወቃል» ሲሉ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደገለጹት፤ ክልሉ ዝናብ አጠር ነው። በዚህም መሰረት በተደጋጋሚ ጊዜ ድርቅ ይጎበኘዋል። ይህን ችግር ለማቃለል ተብሎ ለእንስሳት መኖ የሚያመርተውን በዱብቲ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የግጦሽ ባንክ የሚመረትበትን ቦታ ለበዓሉ ታዳሚ ለማስጎብኘት እቅድ ተይዟል።

ህዳር 29 ቀን በየዓመቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሆኖ እንደሚከበር የሚታወቅ ሲሆን፣ ዘንድሮም «በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን» በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ በነገው እለት እንደሚከበር ይታወቃል።

 

አስቴር ኤልያስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።