የአርሶ አደሮቹ የኮምባይነር ፍላጎትና አቅርቦት

 

ዜና ሐተታ

በአካባቢው በአብዛኛው የደረሱ ሰብሎች ምርታቸው ተንዠርግጎ ይታያል፡፡ ከእነዚህም መካከል ስንዴና ጤፍ ሰብሎች አልፎ አልፎ ደግሞ የኑግ፣ በቆሎና ጥራጥሬ ሰፊውን ማሳ ሸፍነውታል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ታጭደው የተከመሩ ሲሆን፣ በመወቃት ላይ ያሉትን ማስተዋል ችለናል፡፡

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ የጥጃ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አለሙ መኮንን አንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለውን የስንዴ ምርታቸውን አሳጭደው ለማስወቃት ኮምባይነር ሲጠባበቁ ነበር ያገኘናቸው፡፡ በያዙት ወረፋ መሰረት ተራው የደረሳቸው አርሶ አደር 15 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ኮምባይነር አጭዶና ወቅቶ ምርቱንና ገለባውን ለይቶ 26 ኩንታል ስንዴ መሬት ላይ ባነጠፉት ማዳበሪያ ላይ ዘርግፎላቸው ወደ ሌላ ተራኛ ሲሄድ ተመልክተናል፡፡

አርሶ አደሩን ገና ምርቱን በኮምባይነር ገና ሳያሳጭዱና ሳያስወቁ አግኝተናቸው ነበርና ከማሳቸው ምን ያህል ምርት እንደሚያገኙ በጠየቅናቸው ጊዜ 24 ኩንታል ብለው የገመቱ ቢሆንም ለመላ ምታቸው ትክክልኛ ቁጥር ለማስቀመጥ ሩብ ደቂቃ ያልፈጀበት ኮምባይነር ግን ወዲያውኑ ትክክለኛውን ቁጥር አስቀምጦላቸዋል። አርሶ አደሩ ዓምና ለአንድ ሄክታር በተጠጋው ማሳቸው ላይ ጤፍ ዘርተው ስምንት ኩንታል ማግኘታቸውን ያወሳሉ፡፡

አርሶ አደር አለሙ ሦስት ሄክታር መሬት ሲኖራቸው በዘንደሮ የምርት ዘመን ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ አምርተዋል፡፡ ዘንድሮ ሰብላቸውን በረዶ ስለመታው የምርት ቅናሽ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ፡፡ ለእነዚህ ሰብሎች ሁሉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መጠቀማቸውን የሚያስታውሱት አርሶ አደሩ፣ በኮምባይነር በማሳጨዳቸውና በማስወቃታቸውም ድካም ከመቀነሳቸውም በተጨማሪ ለምርት አሰባሳብ የሚደርጉትን ድግስ እንዳስቀረላቸው ያመለክታሉ። ጊዜንም መቆጠብ የቻሉ ሲሆን፣ የምርት ብክነት እንዳያጋጥምም ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። አጭዶ ለወቃላቸው ኮምባይነር በኩንታል 90 ብር ከፍለዋል፡፡ ስምንት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ የሚናገሩት አርሶ አደር አለሙ ምርታማነታቸው እየጨመረ ቢመጣም የገበያ ችግርና የማዳበሪያ ዋጋ በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን ነው የተናገሩት። በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት የማዳበሪያ ዋጋ ቢቀንስላቸውና ምርታቸውንም በጥሩ ዋጋ መሸጥ የሚችሉበት አማራጭ ቢፈጠር መልካም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አርሶ አደር አዝመራው አባተ ሁለት ሄክታር መሬት አላቸው፡፡ ሌላ ሁለት ሄክታር መሬት ደግሞ ተከራይተው ያርሳሉ፡፡ እርሳቸውም ልክ እንደ አርሶ አደር አለሙ ሁሉ አንድ ሄክታር የስንዴ ሰብላቸውን በኮምባይነር ከፍለው አሳጭደው ያስወቁ ሲሆን፣ ከዚህም 43 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ኮምባይነር ባለመገኘቱ ቀደም ሲል ግማሽ ሄክታር ማሳ የስንዴ ሰብል በሰው ኃይል አሳጭደውና ወቅተው ምርቱን ወደ ጎተራ ያስገቡ ሲሆን፣ አንዱን ሄክታር የስንዴ ማሳ በኮባይነር ለማሳጨድና ለማስወቃት እየተጠባበቁ ነው፡፡ ከዚህም 46 ኩንታል ስንዴ አገኛለሁ የሚል ግምት አላቸው፡፡ ጎተራ ካስገቡት ምርት በቅርቡ አምስት ኩንታል ስንዴ ወደ ገበያ በማውጣት ኩንታሉን 900 ብር ሂሳብ የሸጡ መሆኑን የነገሩን ቢሆንም፤ ከአሁን በኋላ ሁሉም አርሶ አደር ምርቱን እያስገባ በመሆኑ የእህል ዋጋ በጣም ይቀንሳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸውልናል፡፡ ዓምና የገበያ ችግር በማጋጠሙ በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን አስታውሰዋል።

እንደ አርሶ አደር አዝመራው ገለጻ፤ የሰብል ምርታማነት በመኖሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ መጥቷል፡፡ 20 ሺ ብር ባንክ አስቀምጠዋል፡፡ አንዱን ልጃቸውን የግል የጤና ኮሌጅ እየከፈሉ በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ የበጋውንም ወቅት መስኖ በማልመት ተጠቃሚ ለመሆን ዕቅድ ይዘዋል። በዚህም የቡና ዘር በመስኖ በማልማት ችግኞቹን ለአካባቢው አርሶ አደር ለማከፋፈል አስበዋል፡፡

ወይዘሮ የተመኝ ፀሐይ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የዛሬ ዓመት አንድ ሄክታር ማሳ በደቦ አሳጭደው 40 ኩንታል ስንዴ አግኝተዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በኮምባይነር አሳጭደውና አስወቅተው 47 ኩንታል ስንዴ ምርት ማፈስ ችለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ማሳጨዱና ማስወቃቱ የምርት ብክነት እንዲሁም ለሠራተኞች የሚወጣውን ወጪ ይቀንሳል። ሆኖም በኮምባይነር በቀላሉ ማግኝት ስለማይታሰብ መንግሥት የሚገኝበትን ሁኔታ ቢያመቻች መልካም ነው።

በምሥራቅ ጎጃሟ ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በስፋት ስንዴ፣በቆሎ፣ጤፍ፣ የጥራጥና ቅባት እህሎችም ይመረታሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ምርት ዘመን አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኝ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ በወረዳው 42725 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈኑ ከዚህም ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል የሚሉት የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳዘዘ ጓዴ ናቸው፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካትም ከእርሻ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍና የግብዓት አቅርቦት ሥራ መሠራቱን ነው የሚናገሩት፡፡

እንደ አቶ እንዳዘዘ ገለጻ፤ ምርቱም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የዘጠኝ ነጥብ ሦስት በመቶ ብልጫ ይኖረዋል፡፡ የምርት እድገቱ እንዲጠበቅ ከአደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ተግባር ተኮር ስልጠና ለአርሶ አደርሩ መሰጠቱ፣የግብዓት አጠቃቀም በመሻሻሉ፣አርሶ አደሩ በመስመር መዝራቱ፣ፀረ አረም መድህኒት በወቅቱ መጠቀም መቻሉ፣ የምርት አሰባሰቡ ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ በሰው ኃይል በእጅ ሲታጨድ፣ ሲሰበሰብ፣ ሲከመር፣ ሲወቃና ሲጓጓዝ የምርት ብክነት ይከሰት የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኮምባይነር ምርት መሰብሰቡ የሚባክነውን ምርት ከማዳን ባለፈ የአርሶ አደሩን ጉልበትና ምርቱን ለመሰብሰብ ለድግስ የሚያወጣውን ወጪ መቆጠብ ተችሏል፡፡

በቆሎ መፈልፈያ መሳሪያ፣ ትራክተርና ኮምባይነር ይቅረብልን የሚል ጥያቄ አርሶ አደሩ እንደሚያነሳ አውስተው፤ ጥያቄ በእነሱ አቅም ሊመለስ ስለማይችል ለክልልና ለፌዴራል መንግሥት ማሳወቃቸውን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜም 30 ኮምባይነሮች ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ ተጓጉዘው ወደ ወረዳው መጥተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቅርቦቱና የፈላጊው ቁጥር አሁንም ሊመጣጠንና የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማርካት አለመቻሉን ያመለክታሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የጎዛምን ዩኒየን የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር በ2010 .ም መጀመሪያ ላይ ሁለት ኮባይነሮችን ገዝቷል፡፡ መሳሪያው በቅርበት መኖሩ መውቂያና ማሳጨጃ ዋጋ ላይ ቅናሽ ይኖረዋል፡፡ ከሻሸመኔ የመጡት ኮምባይነሮች በአሁኑ ጊዜ በኩንታል 90 ብር የሚያስከፍሉት የዩኒየኑ ኮምባይነሮች በኮምባይነር ደግሞ በኩታል 70 ብር ነው የሚቀበሉት፡፡ የአቅርቦት ውስኑነቱን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጅምር እንቅስቃሴ ከክልሉ ጋር በመተባበር የሚፈታ ይሆናል፡፡

የምርት ቅናሽ አጋጥሞናል የሚሉ አርሶ አደሮች አሉና እንዴት ያዩታል ተብለው ለተጠየቁት ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ ይህ ባለበት ሁኔታ 55 በመቶ የሚሆነው የስንዴ ምርት በወረዳው ተሰብስቧል፡፡ ከዚህ አኳያ የወረዳው ጥቅል መረጃ ሲታይ የምርት ቅናሽ አያሳይም፡፡ ግን ከማሳ ማሳና ከአርሶ አደር አርሶ አደር የምርት ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ የአንዱ አርሶ አደር ምርት ስለቀነሰ የወረዳው ሊቀንስ አይችልም፡፡ በረዶ የመታባቸው አርሶ አደሮች እርግጥ ነው ሊቀንስባቸው ይችላል፡፡ የምርት ዕድገት ለማምጣት ከተፈለገ አንዱ በምርታማነቱ የተረጋገጠ ምርጥ ዘር አቅርቦትን ማሻሻል ግድ ይላል ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ መፍትሔው በዞን ደረጃ የግብርና የምርምር ማዕከል ቢኖር የአርሶ አደሩን ማሳ እንደ ሠርቶ ማሳያ በመጠቀም ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ ይቻላል። የምርጥ ዘርና የማደበሪያ አቅርቦቶች በወቅቱና በጊዜው በማቅረብ ጉዳይ ላይና የገበያ ትስስር ላይ ሊታሰብበት ይገባል። በተለይ ታኅ፣ጥርና የካቲት ወራት አርሶ አደሩ የማደበሪያ ዕዳ የሚመልስባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡ በእነዚህ ወራት የእህል ዋጋ መውረድ እንዳያጋጥም ከወዲሁ መንግሥት ሊያስብበት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ የመንገድ ችግርም ለገበያ ችግሩ የራሱ አስተዋጸኦ መኖሩን ጠቅስው ትኩረት ቢደረግበት የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

 

ጌትነት ምህረቴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።