ኮሚሽኑ ድንገተኛ አደጋ ከጠበቀው በላይ እንደሆነበት አስታወቀ

 

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሩብ ዓመት ከታሰበው በላይ አደጋዎች በመከሰታቸው የእቅዱን 240 በመቶ ማከናወኑን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ለተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት የሩብ ዓመት አፈጻጸማቸውንና የ2010 በጀት ዓመት እቅድ ባቀረቡበት ወቅት ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ሩብ ዓመት ከተጠበቀው በላይ አደጋዎች በመከሰታቸው ከተያዘው እቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል። የሚደርሱት ድንገተኛ አደጋዎችም መንግሥት በሚሰራቸው ልማቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

ኮሚሽነሩ፤ ባለፉት ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ለአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን በበረዶ ጉዳት መድረስ፣ በአፋር ክልል ለተፈጠረ ከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ለተከሰተው ችግር፣ በኦሮሚያና በሱማሌ የድንበር አዋሳኝ ለተፈጠረ ግጭት፣ ከአማራ ክልል ተፈናቅለው በትግራይ ክልል ለሚኖሩ፣ የአፋርና የጋምቤላ ክልል ተፈናቃዮች፣ የሳዑዲ ተመላሾችና በኦሮሚያ ክልል ለቡኖ በደሌ ወረዳ የልማት ተፈናቃዮች እርዳታ መደረጉን ገልጸዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እርዳታውን ፈጥኖ ከማድረስ፣ ፍትሃዊ ክፍፍል ከማድረግ፣ አንዳንድ ጊዜ እርዳታዎች ለተረጂዎች ሳይደርሱ መጥፋት፣ በተጨማሪም ሀብት ማሰባሰብንም በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለኮሚሽኑ ኃላፊዎች ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል።

ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ ፈጥኖ ከመድረስ አንጻር አደጋው የደረሰበት ክልል ከአቅሙ በላይ ሆኖበት «ድረሱልኝ» ሲል የተረጂዎች መረጃ እንደደረሰ ሩቅ ቦታ በ72 ሰዓት ውስጥ ቅርብ ሲሆን ደግሞ ከዛ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይደርሳል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እርዳታው በስፍራው ከደረሰ በኋላ በሚፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ለተጎጂዎች ቶሎ ማከፋፈሉ ላይ መጓተቶች እንደሚታዩ ገልጸዋል።

ፍትሃዊ ክፍፍል ከማድረግ አኳያ በዋናነት ክፍፍል የሚያደርጉት አደጋው የደረሰበት ክልልና ወረዳዎች ናቸው። ኮሚሽኑ በቦታው የማድረስና በትክክል መድረሱን ነው የሚያረጋግጠው። አሁን ግን የሚቆጣጠር ቡድን በመላክ በትክክል መድረሱን እንደሚያረጋግጥም አብራርተዋል።

ሀብትን በማሰባሰቡ በኩል ከባለፈው ዓመት የተሻለ የማሰባሰብ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ አገራት የከፋ አደጋዎች በመከሰታቸው ኢትዮጵያ ካላት የተሻለ እንቅስቃሴ ራሷን ትቻል የማለት አዝማሚያ መኖሩን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበር ክፍሌ፤ በቀጣይም በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር፣ ከግዥ እስከ ተጠቃሚው ባለው ሂደት ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።