አዲስ መላ ለአዲስ አበባ ጽዳት

ከህዳር 30 ጀምሮ በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ የፅዳት ዘመቻ ይካሄዳል፤

 

ዜና ሐተታ

ሰዎች ንጹህ አየር ለማግኘት ወይም ለመዝናናት ከቤት ወጣ ብለው በአረንጓዴ ተክሎች ወደ ተዋቡ ወንዞች ወደሚገኙበት አካባቢ ይሄዳሉ፡፡ ዳሩ ግን ይህ በአዲስ አበባ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ ወንዞቻችን እንኳን ከአጠገባቸው ቁጭ ብሎ ንጹህ አየር ሊሳብባቸው ቀርቶ አልፎ ለመሄድ እንኳን እየከለከሉ ነው፡፡ ወንዞች ብቻ አይደሉም፤ ከተማዋ በሁሉም ቦታዎች መጥፎ ሽታ እየወረራት ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ የማን ችግር ነው? ለማንም ግልጽ ነው፤ ችግሩን እያንዳንዱ ነዋሪ መጋራት አለበት፡፡ ቆሻሻን በየሜዳው መጣል የተለመደ ሆኗል፡፡ ማንም ቆሻሻ ሲጥል እንጂ ሲያጸዳ አይታይም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ‹‹ለነገሩ አንድ ዘዴ አስቤያለሁ›› እያለ ነው፡፡ እንደ ጽሕፈት ቤቱ ዓላማ ከፊታችን ቅዳሜ ኅዳር 30 ጀምሮ የእያንዳንዱ ወር የመጨረሻ ቅዳሜ የጽዳት ቀን ይሆናል፡፡ ይህ የአንድ ወይም ሁለት ጊዜ ዘመቻ አይደለም፡፡ ዓመቱን ሙሉ ይቀጥላል፤ የተያዘው ዓመት ሲያልቅ በሚቀጥለውም ዓመት በየወሩ መጨረሻ የዋለው ቅዳሜ ሁሉ እያንዳንዱ ነዋሪ አካባቢውን የሚያጸዳበት ነው፡፡

ይህን ዘመቻ ለማስጀመርም ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ህዳር 26 የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ፍቃደ ከበደ እንደሚሉት ይህ የጽዳት ጉዳይ ለባለድርሻ አካላት ብቻ የሚተው አይደለም፤ ከእያንዳንዱ ነዋሪ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለዚህም የከተማ ሥራ አስኪያጁ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም አለበት፡፡ ይህ የጤና ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ለጽዳት ጉዳይ ከእያንዳንዱ ሰራተኛ ትንሽ ትንሽ ገንዘብ ቢቆረጥ ብዙ ሚሊዮን ነው የሚሆነው፡፡

በየትኛውም ዘርፍ የተሰማራ ሁሉ ትኩረት እንዲሰጠው ከተደረገ ከተማዋ በአጭር ጊዜ ጽዱ እንደምትሆን ነው የሚናገሩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የበጎ አድራጎት አካላትን ማሰማራት፣ ከባለሀብቶችና ታዋቂ ሰዎች ጋር መሥራት የበለጠ አዋጭ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ቆሻሻን ያለአግባብ የሚጥሉ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ነው አቶ ፍቃደ የሚያሳስቡት፡፡ የከተማዋ የጽዳት ነገር እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ የቱንም ያህል ወጪና የሰው ኃይል ቢፈልግ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተለያዩ የዓለም አገራት እንግዶች የሚያዩት ስለሆነ የልማትና ዲፕሎማሲ ሥራዎችም እንቅፋት ነው፡፡ በየቦታው የሚታዩ ቆሻሻዎችን ይዞ በዓለም ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ የቁጥጥር ሥርዓት በየሰፈሩ ሊኖር ይገባል፡፡ የትኛው አካባቢ የበለጠ እንደሠራ ማበረታታትና የትኛው አካል እያቆሸሸ እንደሆነ በመለየት ተገቢውን ቅጣት ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህን ለመሥራት የሚያስችል አሰራር መኖር አለበት፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ደረጀ ሙላቱ እንደሚሉት፤ በተቋማት አካባቢ ውስጥ እንኳን የቆሻሻ አያያዝ ልምድ በጣም አናሳ ነው፡፡ ለእዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በመሥሪያ ቤቶችም ሆነ በመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ ክትትል ሊደረግ ይገባል፡፡ መቀጣት ያለበት ከሆነ ትምህርት ቤትም ይሁን፣ መኖሪያ ቤትም ይሁን መሥሪያ ቤት ሊቀጣ ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍሰሃ እንደሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ የግል ድርጅቶችና ማህበራት ጋር በመተባበር የከተማዋን ጽዳት ለመጠበቅ ለመሥራት አቅዷል፡፡ ለእዚህም የሚያስፈልገውን የሰው ኃይልና ገንዘብ መድቦ ይሠራል፡፡ ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አብረው ይሠራሉ፡፡ ይህ የአሁን የጋራ መድረክ የመጀመሪያ ቢሆንም በቀጣይ በሚደረጉት ውይይቶችም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ተቋማት ድረስ በመሄድም በጋራ ይሠራል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችን በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ቁጥጥር እንዲያደርጉ ይሠራል፡፡ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቢሠራም የታሰበውን ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ግን በህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ለእዚህም በተለያዩ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች ድረስ በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ ድረስ በተቀናጀ መልኩ እንዲሠራ ታስቧል፡፡ ለእዚህም በየደረጃው ውይይትና ክትትል ይደረጋል፡፡ ለእዚህ ጽዳት ዋነኛው የግንዛቤ ጉዳይ ስለሆነ መገናኛ ብዙኃንም የጉዳዩ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በዕለቱ እንደተናገሩት፤ የከተማዋ ቆሻሻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው የከተማ ነዋሪ ላይ የተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ውስን በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም ደረቅ ቆሻሻ ሀብት ሆኖ ሳለ ግንዛቤ ባለመኖሩ ግን ቆሻሻ ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ያለው ቆሻሻ ስሟንና ዕድገቷን የማይመጥን ሆኗል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ እስከ ወረዳ ድረስ በአዲስ አደረጃጀት ለመሥራት አስቧል፤ ለእዚህም የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ያደራጃል፡፡ ዘመናዊ ማሽነሪ ለመግዛትም እቅድ ይዟል፡፡ የመንገድ ዳርቻዎችን፣ ፓርኮችንና ወንዞችን አረንጓዴ ለማድረግ አስፈላጊው በጀት ተመድቧል፡፡

ምንም እንኳን እስካሁንም ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ስላልቻሉ ከዚህ በኋላ በየወሩ መጨረሻ የጽዳት ቀን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ወረዳም አደረጃጀቶች እንደተዘረጉ ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለፉት ስድስት ዓመታት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ ከ402 ሚሊዮን ብር በላይ ለጽዳት ሥራ፤ በተመሳሳይ ለአረንጓዴ ልማትና ውበት ደግሞ ከ139 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የጽዳት ዘመቻው ህዳር 30 ቀን የተለያዩ የፌዴራል የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚገኙበት በይፋ ይጀመራል፤ ከዚያ በየወሩ መጨረሻ ቅዳሜ የፅዳት ቀን ይሆናል፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።