አዳዲሶቹ የመስሪያ ቦታዎች ሥራ ፈጣሪዎችን ይሻሉ Featured

የጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ከተደራጁ ወጣቶች ተደጋግሞ የሚነሳው ቅሬታ የመስሪያ ቦታ ጉዳይ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ የተለያዩ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመስሪያ ቦታ ችግር ግን ፈታኝ እንደሆነባቸውም ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመ ለከታቸው አካላት ደግሞ አዳዲስ እየተሠሩ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ 422 ሼዶችን አስገንብቶ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ሼዶቹም ለተለያዩ አይነት ሥራዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሼዶች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል አካባቢ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጀሞ መድሃኒለም፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና ዘጠኝ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ቂሊንጦ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰሚት ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች የተገነቡ ናቸው፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉዕሽ ተክለመድህን እንደሚሉት፤ በሳንባ ነቀርሳ ሆስፒታል አጠገብ ያለው የመስሪያ ቦታ በዋናነት የሚያገለግለው ለደረቅ ምግቦች ዝግጅት ነው፡፡ ይህም እንዲሆን የተደረገው በወጣቶች ፍላጎትና ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
የመስሪያ ቦታው በውስጡ 25 ሼዶችን የያዘ ሲሆን፤200 ወጣቶችን በኢንተርፕራይዝ አደራጅ ቷል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ሲሆኑ በውስጣቸው ግን ብዙ ወጣቶችን ቀጥረው የሚያሠሩ ናቸው፡፡ ለ600መቶ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የመስሪያ ቦታው አሁን ሥራ ስላልጀመረ እንጂ ሲጀምር ሌሎች ሥራዎችንም እንደሚሠራ ነው አቶ ጉዕሽ የተናገሩት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ መብራት ብቻ ነው የቀረው፡፡ መብራት እንዲገባም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ተልኮ በመጠበቅ ላይ ነው ያለው፡፡
ጀሞ አካባቢ በተገነባው የመስሪያ ቦታ ደግሞ 28 ሼዶች ይገኛሉ፡፡ አንዱ ሼድ ብቻ 50 ሰዎች ይይዛል፡፡ በውስጡ የሚሠሩትም የባልትና ውጤት ምርቶች፣ የእንጨትና ብረታብረት ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይም ሥራ እንዳይጀመር ፈተና የሆነው መብራት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ እንደሚሉት፤ ቢሮው በተለይም በዘንድሮው ዓመት ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም ለ61 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውም በኮንስትራክሽን ዘርፍና በኮብልስቶን ንጣፍ ነው፡፡ እስከአሁንም 18 ሺ ወጣቶች ሠልጥነዋል፡፡ በብረታብረትና እንጨት፣ አልባሳትና ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉት የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችም ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡ አሁን ላይ ተገንብተው የተጠናቀቁት የመስሪያ ቦታዎችም እነዚህን ሥራዎች ታሳቢ ተደርጎ የተሠሩ ናቸው፡፡
በቀጣይም ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተጠና ነው፡፡ ይህም ለ113 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ሥራዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ይሠራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተገንብተው የተጠናቀቁት ሼዶች ብቻ ለ10 ሺ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
‹‹የመስሪያ ቦታ መገንባት ብቻውን የሥራ ዕድል መፍጠር አይደለም›› የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ ከራሳቸው ከወጣቶችም ሆነ ከሥራ አመራሮች ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ነው የሚያሳስቡት፡፡ በተለይም በሥራ ፈጠራ ግንዛቤ ላይ አሁንም ክፍተት ይታያል፡፡ ይህ የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተት ካልተሞላ፣ ሥራ አመራሩም በቁርጠኝነት ካልሠራ የመስሪያ ቦታ ብቻውን የሥራ ዕድል አይፈጥርም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቶ ድሪባ ኩማ አሁን ከተጠናቀቁት በተጨማሪ 760 የመስሪያ ቦታዎችም እየተገነቡ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይሁንና ተገንብተው የተጠናቀቁትም መብራት የማስገባትና የመስሪያ ማሽኖችን መትከል ይቀራል፡፡ በተጨማሪም 300 በህገ ወጥ የተያዙ ሼዶችም እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ከ12 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ታስቧል፡፡
የሚገነቡ ሼዶች በኢንዱስትሪ ክላስተር እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡ «ትላልቅ ኢንዱስትሪ የሚሠራባቸው ይሆናሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ክላስተር ሲሠሩ እርስበርስ የመተጋገዝ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አንዱ ኢንዱስትሪ ለሌላው ኢንዱስትሪ ምርት ማቅረብ ይችላል።» መስሪያ ቦታዎቹ በክላስር መሆናቸው እንደ መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ለመጠቀም አመቺ መሆኑን አስረድተው፤ ይህ ዓይነት አሠራር በሌላው ዓለምም የተለመደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የተገነቡት ሼዶች ለወጣቶች የሚሰጡት በዕጣ እንደሆነ ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡ ብዙ የተደራጁ ወጣቶች ስላሉ እንደተደራጁበት ቅደም ተከተል በሂደት በዕጣ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም አሠራሩን ከአድሎ የፀዳ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሲተላለፉም ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር የሚከተል ይሆናል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች የሚያመርቷቸውን ምርቶች ማስተዋወቅ እንደሚያ
ስፍልግ ነው ከንቲባው ያሳሰቡት፡፡ ለዚህም መንግሥት ምቹ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።