የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎችን ከተጨማሪ ጉዳት ለመታደግ

ወጣት እሸቱ ዘውዱ፣ እህቱ በደረሰባት አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ምክንያት ከሰሜን ወሎ አምባሰል ወረዳ መጥቶ አዲስ አበባ እየኖረ ነው፡፡ ስለ እህቱ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ሲያወራ፣ «በ2003 ዓ.ም እኛን፣ እናትና አባቷን ለማገዝ ብላ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ታላቅ እህታችን አዲስ አበባ መጣች፡፡ ከዚያም በአንድ ጫማ ፋብሪካ ተቀጥራ እየሠራች መኖር ጀምራ ነበር፡፡ እናትና አባቶቻችን የሸመገሉ ስለሆኑ ቤተሰብ ውስጥ ችግር ስለነበር በምታገኛት ገቢ ከቤት ኪራይና ከራሷ የእለት ወጪ የምትተርፋትን ገንዘብ ትንሽም ብትሆን ትልክልን ነበር፤…»፤ እንባ ነበር ያቋረጠው፤ «እንዲህ እየኖረች እያለች በሦስተኛው ዓመት ግን የቤተሰባችንን ህይወት የሚያጨልም መከራ ደረሰብን፤…» ድጋሚ ለቅሶ አቋረጠው፡፡

«ታህሳስ 27 ቀን 2006 ዓ.ም እህቴ እንደተለመደው ከሥራ ውላ ከጓደኞቿ ጋር ወደ ቤት እየተመለሰች እያለ ቦሌ ሰንሻይን አካባቢ መንገድ አቋርጣ ስትሻገር በፍጥነት እየበረረ የነበረ ሚኒ ባስ ገጫት…ገጭቶም አልተዋት ሰላሳ ስድስት ሜትር የሚሆን መንገድ ወደፊት ወስዶ ጣላት፤…ለስድስት ወር ህክምና እየተደረገላት ብትቆይም 75 በመቶ የሚሆነው ማዕከላዊ ነርቯ በመጎዳቱ እጅና እግሯ መንቀሳቀስ የማይችል መሆኗን ሐኪሙ ነገረን፡፡…እናትና አባቶቻችንም በዕድሜ የሸመገሉ አቅመ ደካማዎች በመሆናቸው ከእኔ ሌላ እህቴን የሚያግዛት ሰው ባለመኖሩም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤት ተከራይቼ የቀን ሥራ እየሠራሁ እርሷን እያገዝኩ እዚሁ እኖራለሁ» በማለት ነበር፤ ከብዙ በአጭሩ የህይወት ሰቀቀኑን የተረከልን፡፡ በመኪና አደጋ ክፉኛ የተጎዳችውን እህቱን ለማስታመም ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ እግሩ አዲስ አበባን ሲረግጥ ገና ከቤተሰብ ጉያ ያልወጣ ትንሽዬ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርም አጫውቶናል፡፡
ወጣት እሸቱ፣ በእህቱ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳትም በየጊዜው የፊዚዮ ቴራፒ እንድትከታተል በማድረግና የተለያዩ ምግቦችንና ፈሳሾችን እንድታገኝ በማድረግ በጊዜ ብዛት በራሱ ጊዜ ካልተሻላት በስተቀር ከዚህ በላይ በህክምና የሚፈታ አለመሆኑን ሆስፒታሉ እንደነገረው ይገልጻል፡፡ «ሆኖም ፖሊስ ባደረገልኝ ትብብር መኪናው ኢንሹራንስ አለው ተብሎ ኢንሹራንስ ድርጅቱ 26ሺህ ብር ሰጥቶኝ ብሩ እስኪያልቅ የተባለውን እንድከታተል ባደርግም አሁን ግን ብሩ ስላለቀብኝ እንኳን ለህክምና ሌላው ነገርም እየከበደኝ መጥቷል» ይላል፡፡ ጉዳት አድራሹ አሽከርካሪም ልጅቷን የገጫት ዜብራ ላይ ለመሆኑ በፖሊስ ተረጋግጦበት ታስሮ የነበረ ቢሆንም «አቅመ ደካማ ወላጆችን ጧሪ ነኝ» በሚል ይግባኝ በመጠየቁ የአንድ ዓመት እስራትና የአንድ ሺህ ብር ቅጣት ከፍሎ መለቀቁን ከፖሊስ መስማቱን ታዳጊው ይናገራል፡፡
በአገሪቱ እንዲህ ዓይነት ታሪክ ያላቸው የትራፊክ ተጎጂ ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በቅርቡ የትራፊክ አደጋ ተጎጂ ወገኖችን ቀን ለማሰብ ተዘጋጅቶ በነበረ አንድ መድረክ ላይ የታዘብነውም ይህንኑ ሁኔታ በግልጽ ያሳየ ነው፡፡ በዕለቱ ከላይ ታሪኩ የቀረበውን ታዳጊ እሸቱን ጨምሮ በርካታ የትራፊክ ተጎጂ ወገኖች ለጉዳታችን «ተመጣጣኝ ካሳና ፍትህ እያገኘን አይደለም» የሚል እሮሮ ሲያሰሙም ነበር፡፡ ለመሆኑ ይሄን ችግር ከመፍታት አኳያ ምን እየተሠራ ይሆን? ጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ምን ይላሉ?
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይስሃቅ አበራ፣ ችግሩን ለመፍታት በሁሉም ክልሎች እስከ ወረዳና የማህበረሰብ ፖሊስ አደረጃጀቶች ድረስ የግንዛቤ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በተሸከርካሪ አደጋ ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች የሚቀርብ ህክምናን በተመለከተም ተጎጂዎቹ አስቸኳይ ህክምና የሚያገኙበት መመሪያ ተቀርፆ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ የህክምና ተቋማት እንዲዳረሱ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለአስቸኳይ ህክምና የሚሆን 604 ሚሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ በየክልሎቹ ጤና ቢሮዎች አካውንት ከፍተው ማስቀመጣቸውን በመግለጽ፤ ገንዘቡን ግን የጠቀሙበትም ያልተጠቀሙበትም ክልሎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የሦስተኛ ወገን መድን በገቡ ተሽከርካሪዎች በሚደርሰው ጉዳት ለተጎጂዎች የሚከፈለው በመድን ድርጅቶች መሆኑን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲው ካሳ የሚከፍለው ሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ለሌላቸውና ገጭተው በሚያመልጡ ያልታወቁ አሽከርካሪዎች ጉዳት ለሚደርስባቸው ግለሰቦች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ገጭተው ባመለጡ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ህይወታቸውን ላጡ አስራ ሰባት ሰዎች ኤጀንሲው 500ሺ 941 ብር እንደከፈለ እና ይህም በአማካኝ ሲሰላ በሰው 29ሺ 996 ብር ካሳ መክፈሉን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በመከላከያ ሚኒስቴር ተሽከርካሪዎች የደረሰ የሞትና የአካል ጉዳት ባይኖርም፤ የሚኒስቴሩ ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳትም ኤጀንሲው ባለው ስምምነት መሰረት ካሳውን ተቀብሎ ክፍያውን ይፈጽማል፡፡ ተመላላሽ ህክምና ሲከታተል ለነበረ አንድ ግለሰብ ግን ካሳ ፈጽመዋል፡፡ በተመሳሳይ ባለፉት ስድስት ወራት የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ባላቸው ተሽከርካሪዎች ለደረሱ የሞትና የአካል ጉዳቶች በመድን ድርጅቶች አማካኝነት ካሳ ተፈጽሟል፡፡ ሆኖም ኤጀንሲው የሚከፍለውን አማካኝ የካሳ ክፍያ ከመድን ድርጅቶች ጋር በማነጻጸር የእነርሱ ኤጀንሲ የተሻለ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸው ካሳ ያላገኙና በየቤታቸው የተቀመጡ ዜጎች የሚነሳን ቅሬታ አስመልክተውም፤ “በእኛ በኩል እስካሁን ድረስ ጉዳት ደርሶበት የፖሊስና የህክምና ማስረጃ ይዞ መጥቶ የጠየቀን የለም፡፡ በቀጣይ የሚመጣ ካለም በአግባቡ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “መረጃ በሌለበት ሁኔታ ግን ካሳ መክፈል አንችልም” ይላሉ፡፡ ጉዳዩ ከፖሊስ ከደረሰ በኋላ ከካሳ ማነስ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎችም ለፖሊስና ለፍርድ ቤቶች ከካሳ አከፋፈል ጋር ያሉ አዋጆችንና መረጃዎችን በመስጠት ተጎጂዎች ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኙ ኤጀንሲው ተባብሮ እንደሚሰራም ያመለክታሉ፡፡
በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ለማ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በትራፊክ አደጋ የተጎዱ ወገኖች በተለይም የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት እየኖሩ ያሉት ከአካል ጉዳታቸው በላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ ተጎጅዎችም ጉዳታቸውን የሚመሰክርላቸው እማኝና መረጃ ከማጣትና ከመድን ድርጅቶች አካባቢ ከሚያጋጥሙ የአሰራር ክፍተቶች ጋር ተያይዞ ካሳ ሳያገኙ ረጅም ጊዜ የሚቆዩበት አጋጣሚ መኖሩንም መረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ለተጎጅዎቹ ተመጣጣኝ ካሳ፣ ጥፋተኛውም ዳግም ጉዳት እንዳያደርስ በሚያስችል ሁኔታ አስተማሪ የሆነ የቅጣት እርምጃ በማስተላለፍ ተጎጂ ወገኖች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ እንባቸውን ማበስና ከተጨማሪ አደጋ መታደግ ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም ባለስልጣኑ ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ያሳተፉ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን፤ ችግሩን ለመፍታትና ከዚህ በኋላ የተጎጂዎች ቁጥር እንዳይጨምር በኤች.አይ.ቪ ኤድስና በሌሎችም ዘርፎች እንደተደረገው በዋነኝነት ተጎጂዎች ራሳቸው የሚሳተፉበትንና ስለ ትራፊክ አደጋ አስከፊነት ለህብረተሰቡ ወጥተው የሚያስተምሩበት “የትራፊክ አደጋ ተጎጂ ወገኖች ማህበር” ለማቋቋም መግባባት ላይ ደርሷል፡፡

ዜና ሐተታ
ይበል ካሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።