በቡና ዝርያ የባለቤትነት መብት ዙሪያ ሊሰራ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፡- ከቡና የወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአመዛኙ እሴት ያልተጨመረበት ምርት ስለምትልክ ከባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ “የቡና ተክል እድገትና ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር” በሚል ርዕስ በአገሪቱ የቡና ሀብት ዙሪያ ከዘርፉ ባለሙያዎችና ምሑራን ጋር ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጊቢ አዳራሽ የፓናል ውይይት አድርጓል፡፡ በወቅቱ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ በአመዛኙ ቡናን እሴት ሳትጨምር ወደ ውጪ እየላከች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለቤትነት መብት ልታጣ የምትችልበት አጋጣሚ የበዛ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩን ከማቃለል አኳያ የኢትዮጵያን የቡና ዝርያ በአግባቡ በመለየትና ተገቢውን ስራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡

የውይይት ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብቷ በሌሎች እጅ እንዲገባ ሆኗል፡፡ አሁንም በተመሳሳይ ቡናን በጥሬው ለውጭ ገበያ እያቀረበች ትገኛለች፡፡ ቡና ደግሞ በአመዛኙ እሴት ተጨምሮ ስለማይላክ፤ ከመጠጥነት ባለፈ ለመድሃኒትነት ቅመም እያዋሉት ይገኛል፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ ከባለቤትነት መብት አንጻርም የጤፍ እጣ ሊደርሰው ይችላል፡፡ ስለዚህ አገሪቱ ያላትን ሀብት እንዳታጣ የሚያስችሉ ከቡና ባለቤትነት መብት ጋር ተያያዥ የሆኑ ስራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጥናት ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው እንደተናገሩት፤ ከባለቤትነት መብት ጋር ተገቢውን እውቅና ለማግኘት መሰራት ያለበት አርሶ አደሩ ላይ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ቡና የሚጠጣ ሁሉ የባለቤትነት መብት (ፓተንት) ይኑረው እየተባለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የሆነውን ላለማስመዝገባቸው ዋስትና አይኖርም፡፡ ስለዚህ የባለቤትነት መብት ስራው በአግባቡ ከዳር እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ ዋናው ተግባር የፖሊሲ አውጪዎች ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የተጠናከረ ስራ ማከናወን እስኪቻል ቡናን እሴት ጨምሮ በመላክ ችግሩን ማቃለል ይቻላል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙት በቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና ሻይና ቅመማቅመም ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የቡና ባለቤትነትን በተመለከተ ለነገ መስጋት ብቻ ሳይሆን ዛሬም የኛ ነው ማለቱን ጀምረውታል፡፡ ለምሳሌ፣ ኮፊ አረቢካ የሚባለውን ቡና በስያሜው ብቻ የመኖች ባለቤት ነን እያሉ ነው፡፡ በሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳይ እየተደመጠ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ችግር የማቃለል ስራ የባለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ትኩረት መሆን አለበት፡፡ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትን ጨምሮም ሌሎች ባለድርሻዎችም በትኩረት እንዲሰሩ የሚያስገድድ ሲሆን፤ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮም እንዲሰራ ጅምሮች አሉ፡፡ ነገር ግን የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ መስራቱ ብቻውን በቂ ስለማይሆን ምሁራንም በጥናት ላይ የተመሰረተ የባለቤትነት መብት ማስጠበቂያ ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።