የላላው የጀነቲክ ሀብት ዝውውር ለመጤ አረሞች መዛመት ምክንያት ሆኗል

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ባለው የላላ የጀነቲክ ሀብት ቁጥጥር ስራ በአገሪቱ ወራሪ መጤ አረሞች እንዲስፋፉ እያደረገ መሆኑ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስትቲዩት ገለጸ፡፡
በጀነቲክስ ሀብት ዝውውር ላይ የመከረ የባለድርሻዎች መድረክ ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸውም፤ በአገሪቱ ያለው ልል የጀነቲክ ሀብት ዝውውር ቁጥጥር ስራ የአገሪቱን ሀብት ከማሳጣቱ ባለፈ ወራሪ መጤ አረሞች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ በጀነቲክ ሀብትና አርክቦት የማህበረሰብ መብቶች ላይ የተለያዩ ኃላፊነቶች ቢሰጠውም ብቻውን ግን ዝውውሩን መቆጣጠር አይችልም። ስለሆነም ከሌሎች ጋር ሥራ ተከፋፍሎ እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ዝውውሩ በሚፈለገው ልክ ጠንካራ ስላልሆነ በርካታ ዝርያዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና አገሪቱ ውስጥ ያሉትን የብዝሀ ህይወት አደጋ እንዲጋረጥባቸው አድርጓል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ችግሩን ለመከላከል እንዲቻል ኢንስትቲዩቱ ባለሙያዎችን በየኬላዎቹ መድቦ እየሰራ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራው የሚከናወነው 24 ሰዓት ስለሆነ ሙሉ ፈረቃ ለማሰራት ባለመቻሉ በአልታሰቡ መንገዶች ዝርያዎች እንዲገቡና ችግር እንዲፈጥሩ ሆኗል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የጀነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አያናው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የጀነቲክ ሀብት ዝውውሩን ሙሉ ለሙሉ ህጋዊ ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሁን ላይ ሁሉም ጠቋሚ እንጂ ይህ ሥራ የእኔ ነው ብሎ መስራት ላይ ብዙም ጠንካራ አይደለም። ይህ ደግሞ እየተንሰራፋ ላለው ወራሪ መጤ ዝርያ ዋና መንስኤ ነው፡፡
የመጤ ወራሪ ዝርያዎች መንሰራፋት ምክንያቱ ያለማወቅ ብቻ ሳይሆን እያወቁም ያለመተግበርና ጉዳዩን በቸልታ መመልከት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ እያንዳንዱ ተቋም ከውጭ አገር የሚገቡ ዝርያዎችን በጥንቃቄ አይተውና ለምን አላማ ይዘውት እንደሚገቡ አውቀው መሆን እንዳለበትም ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ለገንዘብ ብለው በአገሪቱ እነዚህን ዝርያዎች የሚያስገቡ አካላት ካሉም ተግባሩ አገርን ከመሸጥ ስለማይተናነስ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የኢንስቲትዩቱ የህግ አማካሪ አቶ ፍቅረማርያም ግዮን በመድረኩ ላይ የህግ ጉዳዮችን አስመልክተው ጽሑፍ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የተለያዩ ተግባራትን እንዲያከናውን በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በተለያየ መልኩ የጀነቲክ ዝውውር ትኩረት እንዲያገኝ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ለውጦች እየታዩ ሲሆን፤ ለውጡ ግን የሚፈለገውን ያክል አይደለም፡፡ ስለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች አሁን ያለው ወራሪ መጤ ዝርያን በመከላከል ጎን ለጎን የጀነቲክ ዝውውሩ ላይ ጠንካራ ሥራ ለመስራት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
በመድረኩ ላይ ጥናት ያቀረቡት አቶ አማረ ሰይፉ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አረሞቹ በፍጥነት የሚዛመቱ ከመሆናቸው ባለፈ ሰዎች ከአረሙ ጋር ለረዥም ጊዜ በሚነካኩበት ወቅት የጤና ጉዳት ያስከትልባቸዋል፡፡ ነባር ዝርያዎችም እንዲጠፉ እያደረገ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች መወገድ የሚችሉት ሁሉም በተሰጠው ኃላፊነት መስራት ሲችልና የጀነቲክ ዝውውሩ ላይ የተጠናከረ ስራ ሲከናወን ነው፡፡

ጽጌሬዳ ጫንያለው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።