ከዋጋ ግሽበቱ የሚዛን ቅሽበቱ Featured

 

ስንቶቻችን በከተማችን በሚገኙ መደብሮች ስንሸምት ሚዛኑን እንቆጣጠራለን? ምን ያህሎቻችንስ ስለሚዛን ማጭበርና ስለ ኪሎ ቅሸባ የተፈጸመብንን ለመከላከል ለእራሳችን ዘብ እንቆማለን?  ሁሉም ጥያቄዎች በአዕምሯችን ውስጥ የተለያየ መልስ ሊፈጥሩ ይችላሉ። አብዛኛው ህብረተሰብም ስጋም ሆነ የተለያየ ምግቦች ሲገዛ የሚዛን ጉድለት እንደሚደርስበት ቢያስብ ምን ያህል ኪሳራ ያስከትልብኛል የሚለውን ግን አጢኖ አይገዛም።

 በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሥጋ ዋጋ 160  እስከ 300 ብር ነው ብለን ብንወስደው፤  ከአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ አንድ መቶ ግራም የሚዛን ማጭበርበር ቢደርስብን በዝቅተኛው ስሌት አስራ ስድስት ብር እንደተወሰደብዎት ይቆጠራል። ተጨማሪ ሲገዙ ደግሞ ኪሳራውም በዚያው ልክ እያየለ ይሄዳል። ለአብነት ሥጋ ቤቶቹም በቀን ከአንድ በሬ ላይ ማለትም በግምት ሦስት መቶ ኪሎ ከሚመዝን ሥጋ ላይ በተመሳሳይ መጠን ቅሸባ ቢያደርጉ 30 ኪሎ ግራም ትርፍ ያጋብሳሉ። ይህም በገንዘብ ሲሰላ ህብረተሰቡ በቀን 4 ሺ 8 መቶ ብር  ሊውስዱበት  እንደሚችል ልብ ይሏል። ጉድለቱም ለሸማቹ «እበላ ብዬ ተበላሁ» እንደተባለው ይሆናል። ይህ አሃዝ በከፍተኛው ዋጋ  ካየነው ደግሞ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል  መገመት ይቻላል።

የኢፌዴሪ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ የተከናወነውን በሚዛን ላይ ያተኮረ የልኬት ዳሰሳ ጥናት ሰሞኑን ሲያቀርብ በሸቀጣሸቀጥ ሱቆች የተጋነነ የሚዛን ቅሸባ ባይታይም የሥጋ ቤቶች ሚዛን ግን ጉድለቱ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ይፋ አድርጓል።

የዳሰሳ ጥናቱ 75 ከግል እና ከሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ችርቻሮ መሸጫ ሱቆች፣ 21 የግል ሥጋ ቤቶች እንዲሁም 12 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሥጋ ቤቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በጥናቱ መሰረት  የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች የከፋ ችግር ባይታይባቸውም አነስተኛም ቢሆን የሚዛን መጓደል እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ሊስተካከል ይገባዋልም ተብሏል። የሚዛን የክብደት ልኬት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምልከታ ከተደረገባቸው 33 የግልና የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሥጋ ቤቶች ውስጥ 21ዱ ሥጋ ቤቶች ላይ በተለያየ መጠን የሥጋ ክብደት የልኬት ችግሮች ታይቷል። በሥጋ ቤቶቹም በአንድ ኪሎግራም እስከ 143 ግራም ጉድለት የሚያስከትሉ ሚዛኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንዳሉም ተመላክቷል።

በከተማዋ የሚገኙ ህገወጥ ሥጋ ቤቶች ቁጥር ከግምት ውስጥ ሲገባ  እና በቀን የሚሸጡት የሥጋ መጠን ከፍ ባለ ቁጥር ሸማቹ ህብረተሰብ ለከፍተኛ ብዝበዛ መጋለጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ጥናቱን ያቀረቡት በባለሥልጣኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ሞላ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በጥናቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ሥጋ ቤቶች መካከል የልኬት መሳሪያ ብቃት ማረጋገጫ በትክክል የተለጠፈባቸው 12ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ የመስፈሪያ መሳሪያቸው ብቃት አጠራጣሪ መሆኑ ለማጭበርበር  የተጋለጡ ናቸው። ሚዛኖቹም «አናሎግ» አሠራር ስለሚጠቀሙ በቀላሉ የመዛነፍ ችግር ሊፈጠርባቸው ይችላል። እንደ መፍትሔ በቀጣይ ጊዜያት ብቃታቸው የተረጋገጠ ላቸው «ዲጂታል» ሚዛኖችን መጠቀም በመተማመን ላይ ለተመሰረተ ግብይት ይረዳልና ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገቢ ንግድ ክትትል ባለሙያው አቶ ደመቀ ሰይፉ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሚዛን ማጭበርበር መኖሩ ህብረተሰቡ ምን ያህል እየተጎዳ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። በተለይ በአብዛኛው ሥጋ ቤቶች በኩል በጥቅም ላይ የሚውሉ «የአናሎግ» የልኬት መሳሪያዎች ለሸማቹ ፊት ለፊት እንዳይታዩ በጎን በኩል ይቀመጣሉ። የልኬት መጠን ጠቋሚዎቻቸው ትክክለኛ በሆነው የዜሮ ምልክት ላይ መነሳታቸውን ወይም ከሚፈለገው የክብደት መጠን ላይ ማረፋቸውን ሸማቹ በትክክል እንዳይመለከት የአቀማመጣቸው ሁኔታ አዳጋች ይሆናል።

ቢሮውም «ዲጂታል» ሚዛኖች ለንግዱ አስፈላጊ መሳሪያዎች መሆናቸውን በማመን ከአስመጪዎች ጋር ለመስማማት ሂደት ላይ እንደነበረ አቶ ደመቀ ያስረዳሉ። ነገር ግን በጨረታ ሂደት ከአስመጪዎቹ ጋር በነበረው ያልተሳካ ግንኙነት ምክንያት ሚዛኖቹን ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ተከታታይነት ያለው ቁጥጥርና ፍተሻ ማድረግ ያስፈልጋል። ህብረተሰቡም ስለጉዳዩ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት የሚዛን ቅሸባዎችን እንዲከታተል ሰፊ ውይይቶችን ማዘጋጀት እንደገባ ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ በሥጋ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ኤልያስ በድሉ ግን ጥናቱ የሁሉንም ነጋዴዎች ሁኔታ ያማከላ ላይሆን ይችላል የሚል ሃሳብ አላቸው። «አንዳንዶች ሚዛኑን አጋድለውና አዛንፈው በማስቀመጥ ሊሸውዱ ይችላሉ። አብዛኛዎቹ ግን ደንበኛ ለመሳብ ሲባል እንኳን እላፊ መርቀው የሚሸጡ ናቸው። በመሆኑም ሸማቹ ህብረተሰብ አታላዮቹን ለመከላከል ሥጋ ከገዛ በኋላ በሌላ ሚዛን በማስመዘን ከአጭበርባሪዎቹ ጋር ያለውን ደንበኝነት ማቋረጥ ይኖርበታል። ከትክክለኛ መዛኞች ጋር ደንበኝነቱን ሲያጠናክርም ሚዛን የሚቀሽቡትን ወደ ትክክለኛው አሠራር ማምጣት ይቻላል» በማለት ህብረተሰቡ ችግሩን ለመካላከል መፍትሔው በእጁ እንደሆነ ያስረዳሉ።

«በጉዳዩ ላይ የስነልክ ጉድለቶችን ተመልክቶ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ይገኛል» የሚሉት ደግሞ ከንግድ ሚኒስቴር ህግ ክፍል የመጡት ወይዘሮ ኤልሳ ስዩም ናቸው። በአሁኑ ወቅት ህጉ ተዘጋጅቶ ለተጨማሪ ውይይት እና ውሳኔ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ዝግጁ ሆኗል። የስነልክ አዋጁ በንግዱ ላይ የሚስተዋሉ የሚዛን ጉድለቶችንና ተያያዥ ችግሮችን በተመለከተ እርምጃ ለመውሰድ የህግ ድጋፍ ይፈጥራል።

ህብረተሰቡም የሚዛን ችግሩን ቢረዳም ምን ማድረግ እንዳለበት እንደማያውቅ የህግ ባለሙያዋ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ሃሳብ ከሆነ፤ ህጉ ጸደቆ ቢወጣም የንግድ ግብይቱ ላይ የሚዛን ጉድለቶችን ለመከላከል በዋናነት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል። መገናኛ ብዙሃን እና የተለያዩ የመንግሥት አካላት በጉዳዩ ላይ መድረኮችን ፈጥረው ሸማቹን ሊያስተምሩ ይገባል።

ዜና ሐተታ

ጌትነት ተስፋማርያም

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።