የመጤ ባህሎች «ሰ'ዶ ማሳደድ...» Featured

አንዳንዶች «እንቅፋት!» በሚል ስም ይጠሯቸዋል። ሰዎች ወደቤታቸው ሲያቀኑ በመንገዳቸው የሚያጋጥሟቸውን መሸታ ቤቶች። እነዚህ እንቅፋቶች ወደቤቱ ለመሄድ መንገድ ላይ ያለን ሰው ብቻ ሳይሆን ትውልድን ወደነገ የሚያደርገውን ጉዞ ሲያደናቅፉ ይስተዋላል። መዲናዪቱም በመጤ ባህሎች በመወረር እንዲህ ያለው እንቅፋት የበዛባት ከተማ ከሆነች ሰነባብታለች። ይህም በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የሌለ አልያም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የተከናነበ ያህል ስሜት እየፈጠረ ይገኛል።

በሌላ ወገን መጤ ባህልን ለመከላከልና የነበረውን በጎ ባህል ለማዳበር እንቀሳቀሳለሁ የሚል «ባለድርሻ» አካል አለሁ ሲል ይሰማል። ይህም ሆኖ ግን እነዚህ እንቅፋት የሚባሉ ጭፈራ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የራቁት ዳንስና ሺሻ ማስጨሻዎች፣ ጫት ማስቃሚያ እንዲሁም መሰል መጤ ባህል የሚጎበኛቸው ቤቶች ግዛታቸውን እያስፋፉ፤ አሠራራቸውም እየዘመነ ሄዷል። የንግድ ኃላፊዎችም በአንድ ጎን ለቤቶቹ ፈቃድ ሰጪዎች ራሳቸው ሆነው ይገኛሉ። «ሰ'ዶ ማሳደድ...» እንዲሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቢሮ ደረጃ ከተዋቀረ አስር ዓመታት እንደተቆጠሩ ያስታውሳሉ። መዋቅሩንም እስከወረዳ ድረስ አስፍቷል። «መዋቅሩ መዘርጋቱ ትልቅ እፎይታን ሰጥቶናል፤ ይህ የተደረገው ከባህል ጋር ተያያዥ የሆነ ሥራ መሥራት የሚቻለው ታች ያለው ህብረተሰብ ጋር በመሆኑ ነው» ይላሉ።
መዋቅሩ ከተዘረጋና ሥራ ከተጀመረ በኋላ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት፣ የገንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት፣ በመገናኛ ብዙኀን በኩል መረጃዎችን በማቀበል ጥሩ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ። ይሁን እንጅ በተለይ መጤ ባህልን በሚመለከት ካለው ስጋት አንጻር የተሠራው በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ችግሩን በመከላከል ረገድ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያስሄዳል የተባለለት ምክር ቤትም ከሦስት ዓመታት በፊት መቋቋሙን ይጠቁማሉ። ምክር ቤቱም በከተማ ደረጃ በከንቲባው የሚመራ ሆኖ ታች የክፍለ ከተማ እና የወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈትቤቶች ብቻቸውን ማምጣት ያልቻሉትን ለውጥ ከሌሎች ክፍሎች ጋር በጋራ ለማምጣት ያለመ ነው።
አቶ ወርቁ እንዳሉት፤ ይህ አሠራር «እኔን አይመለከተኝም» የሚል ክፍል እንዳይኖር ያግዛል። በዚህም አዲስ መዋቅር ከፖሊስ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ ሴቶችና ሕፃናት፣ ከትምህርት ቢሮ፣ መድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣንና ሌሎችም አካላት ጋር አብረን እንሠራለን ተባብለዋል። ይህም ሆኖ ግን ቅንጅቱ በራሱ ጅማሮ እንደሆነና ብዙ የሚጠበቅ ሥራ እንዳለ ይገልጻሉ።
የአልባሌ ቦታዎቹን ጉዳት በመከላከል ረገድ ቦሌ ክፍለከተማ በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች እንዳሉ የሚናገሩት ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ የባህል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት አፈወርቅ ናቸው። ችግሩን ለመከላከል በክፍለከተማው በሚገኙ 15 ወረዳዎች ለወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያና መሰብሰቢያ የስነጽሑፍ ምሽቶችን ማዘጋጀትና የኪነጥበብ ቡድኖች መፍጠርን እንደአማራጭ ተወስደዋል።
ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠትም በየወረዳው ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። መጠጥና ጭፈራ ቤቶች በብዛት የሚታዩባቸው አካባቢዎች እንደታወቁም ይጠቅሳሉ። «ልንቆጣጠረው ያልቻልነው ሰፊ ችግር አለ» የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በባርና ሬስቶራንት ወይም በማሳጅ ቤት ስም የሚከፈቱ ቤቶችን በሚመለከት፤ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት ወይም ፈቃድ ለማደስ በሚደረግ ቅኝት ቤቶቹ ከትምህርት ቤት ምን ያህል እንደሚርቁና የድምፅ ብክለት መኖር አለመኖሩን በዋናነት የሚታይ መሆኑን ይናገራሉ።
እንዲያም ሆኖ የተጠቀሱት ጉዳዮች በትክክል የተቃኙ ባይመስሉም የወጣቱ የህይወት መንገድ በአጓጉል ሱስ ተጠምዶ መባከኑን በሚያገናዝብ መልኩ የሚሠራ ሥራ በባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በኩል እንደሌለ ከአቶ ዳዊት ንግግር መረዳት ይቻላል። ቡድን መሪው ለዚህ ችግር ብለው የጠቀሱት ታች እስከወረዳ ድረስ በእኔነት ስሜት ሳይሆን ኃላፊነቱ ጥቅም ያስገኝ ይመስል «ሥልጣኑ ለእኔ ይሰጠኝ» ሽኩቻ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም አንዱ ያሸገውን የንግድ ቤት ሌላው በገዛ ሥልጣኑ ሲከፍት ማስተዋላቸውን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ሲቲና ሲራጅ በአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊት ናቸው። በክፍለከተማቸው መጤ ባህልን ለመከላከል አስወጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሯል። ይህም በየወረዳው በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ መሆኑንና የተቋቋመውም በያዝነው ዓመት መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ኮሚቴ በተለይ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስና ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጋር በመሆን ወደሥራ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት ላይ ነው።
«መጤ ባህልን የሚጋብዙ ንግድ ቤቶችን ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ራሳቸው ድርጅቶቹ አምነውበት እንዲዘጉና ወደሌላ ሥራ እንዲቀይሩ ምክክር ይደረጋል። ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር እንዲዘጉ የተደረጉ ቤቶችም አሉ።» በማለት አስታውሰው፤ በዋናነት ግን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚያስቀ ድሙም ጠቁመዋል።
በክፍለ ከተማው እንደሌሎቹ ሁሉ መጤ ባህልን ለመከላከል ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን የሚጠቅሱት የአቃቂ ክፍለከተማ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ወልደሚካኤል ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፈው ዓመት ከንግድና ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት ጋር በጋራ የተወሰዱ ዕርምጃዎች አሉ። በክፍለከተማው በተለይም ሳሪስና ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ ይህ ችግር ጎልቶ ይታያል። አስቀድሞ ከተወሰደው ዕርምጃ በላይ ሥራ የሚፈልግ በመሆኑ አሁንም እንደዚያው ባለ ሂደት ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
«ብዙ ሥራ ተሠርቷል ግን ወጣቱን ከመጤ ባህል ወረራ አድናችሁታል ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ገና ብዙ መሥራት አለብን ብለን ነው የገመገምነው» ሲሉም አቶ ዳዊት ይናገራሉ። ምንም እንኳን የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈትቤቶች በየወረዳው ከተዋቀሩ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ባይሆንም በአዲስነት ስሜት ብዙ ሥራዎችን መሥራት ስለሚቻል በዚህ ጉዳይ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል። በዓመት ጥቂት ቀናትን የሚከወኑ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች በየዕለቱ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ይቀነሳል ብሎ ማመን አይቻልም። እየሰደዱ መልሶ ማሳደድ ከዚህ እንዳይብስ ግን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ያስረዳሉ።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።