ከጥልቅ ተሃድሶው ምን ይጠበቃል? Featured

ክፍት የስራ ማስታወቂያ ለመከታተል በርካታ ወጣቶች ከማይታጡበት አራት ኪሎ መታጠፊያ ላይ ካለ ደረጃ ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ወደሚያነብ ወጣት እግራችን አቀና፡፡ ለትምህርት ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናረው ወጣት ሞቱማ ነገሪ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩት ችግሮች ለመንግስት ብቻ ሊተዉ እንደማይገባቸው ይገልፃል፡፡ በአካባቢው የስራ ማስታወቂያ ለማንበብ መንገዱን ያጨናነቁትን ወጣቶች በመመልከትም በስራ ዕድል ፈጠራ ወጣቶች ላይ አሁንም ያልተለወጡ ኋላቀር አመለካከቶች መኖራውን ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል መንግስትም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊሰራቸው የሚገቡ በርካታ ተግባራት እንዳሉ የትምህርት ተደራሽነቱ ላይ እንጂ ቀጣይ የወጣቶቹ ዕጣ ፈንታ ላይ አለማተኮሩና ሊቀረፉ ያልቻሉት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ማሳያ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ 

እንደ ወጣት ሞቱማ ገለፃ፤ ከተጠቃሚነት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና ህገ መንግስት አፈፃፀሙ ላይ ያሉ ችግሮች ብሎም በክልሎች አንድነትን የመፈረካከስ ሀይል ያላቸው ብሄርተኝነቶች መንገስ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሰላምና አለመረጋጋት ችግሮች መንስዔ ሆነዋል፡፡ መንግስትም ራሱን እያየ እንደሆነ ቢገልፅም ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ ጥልቅ ተሃድሶው ከታይታ በዘለለ በተግባር ለውጥ የሚያመጣ ካልሆነ ችግሩን ከማቃለል ወደ ማባባስ ይመራዋል፡፡ ምሁራንም መንግስትን ከመተቸት ይልቅ ራሳቸው የመፍትሄ አካል ቢሆኑ በተመሳሳይ መንግስት ከተሞች ላይ ከሚታየው ለውጥ ባሻገር በክልሎች ያለውን የህግ አፈፃፀም መላላቶች በትኩረት ሊመለከት ይገባል፡፡ የአገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ፌደራሊዝም ስርዓቱ ለውጥን ማምጣት የሚችል በመሆኑ አንድነትን አጥብቆ በመያዝ ለጋራ አገራዊ ዕድገት ርብርብ መደረግ ይኖርበታል፡፡
የአዲስ አበባ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ እንደሚናሩት፤ በከተማዋ ያሉ ሴቶች ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም ተጠቃሚነት ላይ አሁንም ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በሚከናወነው ተግባር ውስጥ በሴቶቹ ላይ ያለ የስራ መረጣ ችግር እንዳለ ሆኖ ከመስሪያ ቦታ አቅርቦትና መሰል ድጋፎች ጋር ውስንነቶች አሉ፡፡ የሴቷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አደረጃጀቶችንም ከማሳተፍ ጋር ተያይዞ መንግስት የከፋ ችግር አይታይበትም፡፡ ይሁን እንጂ ማህበራቱን በሚያጠናክር መልኩ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ችግሮች ይታያሉ፡፡ መንግስት በአሁኑ ወቅት እያደረገ ባለው ተሃድሶና ማጥራትም በተለይ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ተቋማት ጋር ያለ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችግር ላይ ትኩረት መስጠት ያለበት ሲሆን የተወሰኑ ውሳኔዎችንም ለማስፈፀም በጋራ መሰራት አለበት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ግርማይ እንደሚሉት፤ የተደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ለችግሮቹ መፈጠር ዋነኛ ምክንያት በአገልግሎት ሰጪው ዘንድ ህዝብን በቅንነት የማገልገል አመለካከት ሙሉ በሙሉ አለመያዙ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ህዝባዊነቱን የሚሸረሽረውም በከተማዋ የገነገነው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚስተዋሉ የጥበትና የትምክህት አመለካከቶች ናቸው፡፡ እነዚህም አንድነትን የሚሸረሽሩ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለሁሉም ዜጋ እኩልና ተገቢነት ያለው አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎት ቆይቷል፡፡
በተሃድሶ መልካም አስተዳደር የማስፈን እንዲሁም የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን በሚመለከት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው በርካታ ችግሮች መለየታቸውን የቢሮ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ችግሮችን ለማቃለል በስፋት ቅሬታ የሚነሳባቸው ተቋማትን በመለየት ዕቅድ ታቅዶ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሃላፊው እንዳብራሩት የከተማ አስተዳደሩን የ2009 በጀት ዓመት አፈጻፀም መነሻ በማድረግ በተያዘው 2010 ዓ.ም ምን መሰራት እንዳለበት በሰፊው የሚዳስስ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ምንም እንኳን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሁሉም ጉዳይ ቢሆንም በርካታ ተገልጋይን የሚያስተናግዱት እንደ መሬት፣ ንግድና ጤና ያሉ ተቋማት ቁልፍ ሴክተሮች በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ተቋማት በተለዩት ከ3 ሺህ 600 በላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ኃላፊው አመላክተዋል፡፡
እንደ አቶ ይስሐቅ ገለፃ፤ ችግሩን ከአመራሩ በተጨማሪ ፈፃሚው አካል ይጋራዋል፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ በተዘጋጁ ሰባት የስልጠና ሰነዶች ዙሪያ ለ 95 ሺህ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከሰነዶቹ መካከል አንዱ በመልካም አስተዳደር ላይ በሚታዩ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን በዚህም የህዝብ አገልጋይነት አመለካከት በማስረፅ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የታሰበውን ለውጥ ማምጣት እንዲቻል ከሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ዘርፈ ብዙ ተግባራት ጎን ለጎን ተጠያቂነትን ማስፈን ላይም መሰራት እንዳለበት ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ መንግስት ችግሮችን መለየት ላይ የጎላ ክፍተት ባይታይበትም በዛው ልክ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ግን ሰፊ ውስንነቶች እንዳሉ በተለያዩ አካላት የሚነሱት አስተያየቶች ዕውነታነት አላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ስራቸውን በአግባቡ ያላከናወኑና ስርቆት ውስጥ የገቡ 109 አመራሮች እንዲሁም 1 ሺህ 500 ፈፃሚዎች ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የሚፈጠረው ችግርና ተጠያቂ የሚደረጉት አካላት ካለው የችግሩ ስፋት አንፃር ሲታይ በቂ ባለመሆኑ የሚሰራው ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው አክለውም፤ አስተዳደሩ በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በጥልቀት ገምግሞ ከላይ እስከ ታች ይህንን ሊፈታ የማይችል አካል ካለ እያተስተካከለ እንዲሁም የተጠያቂነት ስርዓትን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ይሰራል፡፡ በዚህም ህብረተሰቡን ለመካስና የሚያነሳቸውን ችግሮች በቀሪ ወራት ለማቃለል በልዩ አቅጣጫና ርብርብ ለመስራት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ስራውም ከዳር እንዲደርስ ህብረተሰቡ ችግሮችን ከማንሳት ጎን ለጎን ከመንግስት ጎን በመሆን የመፍትሄ አካል መሆንና የልማት አጋርነቱን በንቁ ተሳትፎና ትግል ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ፍዮሪ ተወልደ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።