የአሸናፊነት መገለጫ Featured

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 64 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ህዝቡም ለግንባታው የሚያደርገው ድጋፍ ከነግለቱ ቀጥሏል፡፡ ግድቡም የአሸናፊነት አመለካከት እና የብሄራዊ መግባባት መገለጫ እየተባለ ነው፡፡ እነዚህን መገለጫዎች እንዴት ሊያተርፍ ቻለ ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም መምህርና ተመራማሪ ኮማንደር ዶክተር ዳንኤል ገብረእግዚአብሄር ግድቡ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ያለው እንዲሁም የዲፕሎማሲ ድል የተገኘበት መሆኑ በህዝቡ ዘንድ በልዩ ዓይን እንዲታይ አድርጎታል ይላሉ፡፡
ኮማንደር ዶክተር ዳንኤል ፤ግድቡን የአብሮነት መገለጫ እና የልማቱ ሁሉ አውራ ይሉታል፡፡ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ምንም ዓይነት የገንዘብ ብድርም ሆነ ድጋፍ እንዳይሰጥ የተዶለተውን ሴራ የተቋቋመ ፣ህዝቡ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ቢለያይም ግድቡ አገራዊ መግባባትን በመፍጠር አንድነቱን ይበልጥ እያጠናከረ እንዲመጣ ያስቻለ መሆኑንም ያብራራሉ፣እነዚህም ግድቡ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ እንዲኖረው ማድረጋቸውን ያብራራሉ፡፡
የተፋሰሱ አገሮች ጥያቄና የዓለም አቀፍ ተቋማትን ጫና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አካሄድ ማለዘብ እንዲሁም ከጥገኝነት ነጻ በመሆን በራስ አቅም መገንባት የተቻለበት መሆኑን በመጥቀስም ይህም ግድቡ በህዝቡ ዘንድ የከፍታ ማማ ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል ይላሉ፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ህዝብ በአንድ መንፈስና ዓላማ ተባብሮ ሙሉ ድጋፉን የሰጠለት ሥራ አለ ለማለት ይከብዳል ያሉት ተመራማሪው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በጥንካሬና በጥንቃቄ የያዘችው ስለሆነ ‹‹አትስሪ›› ብትባል እንኳ ቸል የማትለው ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና የውሃ ፖለቲካ ምሁሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ፤ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትነካ ሲፈጥሩ የኖሩት ደባ ከሽፎ ግንባታው መጀመሩም ሌላው ግድቡን የአሸናፊነት መገለጫ ያረገው ምክንያት ሲሉ ያብራራሉ ፡፡
ዶክተር ያዕቆብ እንደሚሉት፤ ግድቡ በህዝብ ድጋፍ መገንባቱ የብሄራዊ መግባባት መገለጫ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ የአገሪቱንና የህዝቧን የረጅም ጊዜ ፍላጎት ለማሟላት ወደ ግንባታ የተገባበት መሆኑን ያብራራሉ፡፡
በኮተቤ ሜትሮፖሊታያን ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ታምራት ኃይሌ የአገሪቱ ዜጎች የሚለያዩባ ቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የጋራ የሚያደርጓቸው እንዳሉም ጠቅሰው፣ የጋራ ከሚያደርጓቸው መካከል ዋናው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ግድቡ ከምንም በላይ ብሄራዊ ስሜት የተንጸባረቀበት መሆኑን በመጥቀስ የዶክተር ያዕቆብን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
በአባይ ወንዝ ላይ በሚካሄድ የግድብ ግንባታ ህዝቡ ኢትዮጵያና ሌሎች ብሎ የለየው ድንበር እንዳለና በዚህም ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት እንድታጠናቅቅ እንደሚፈልግ በመግለጽ የዶክተር ያዕቆብንና የዶከተር ዳንኤልን ሐሳብ የሚያጠናክሩት ዶክተር ታምራት፣ አገሪቱ በምትገነባው ሌሎች ግድቦች ላይ ግን እኛና እነሱ የሚል አመለካከት እንደማይንጸባረቅም ያመለክታሉ፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ገርባ አገሪቱ ካሏት ተፋሰሶች ውስጥ የአባይ ተፋሰስ ትልቁ የውሃ ሀብት ያለበትና ከ55 እስከ 60 በመቶ ያህል የአገሪቱ የውሃ ሀብት የሚገኝበት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ባሳየው ቁርጠኝነት መሰረት ድጋፉን ማጠናከሩን እና ሀገሪቱ ያደረገችውን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ጠቅሰው፣በዚህም ብሄራዊ መግባባትንና አገራዊ ትብብርን መፍጠር ተችሏል በማለት የምሁራኑን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
ህዝብ ባለው አቅም ተረባርቦ ፕሮጀክቱን እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዜጋው ከጉድለቱ እየለገሰ የሚሰራው እንዲህ ዓይነቱ የትብብር ሥራ ምናልባትም በአገራችን ከዚህ ቀደም ያልነበረ ፣በብዙ አገሮችም ላይኖር የሚችል ነው ይላሉ ፡፡
ዶክተር ዳንኤል በተከዜም፣ በአዋሽም ሆነ በሌሎች ወንዞች ላይ እየተገነቡ ያሉ ግደቦች ላይ የጎረቤት አገሮችም ሆኑ የዓለምአቀፉ ህብረተሰብ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንደሌለ በመጥቀስ ህዳሴ ግድቡ ላይ ግን የእነዚህ ወገኖች ተጽዕኖ የበረታ እንደነበርና ይህም ህዝቡን ወደ አንድ እንዳመጣው ያብራራሉ፡፡
ወንዙ በጣም ትልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚጠይቀው እውቀትና ቴክኖሎጂ በጣም ከፍተኛ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፣ በተለያየ ጫና ሳቢያ ብድርም እንዳይገኝ ይደረግ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ በወቅቱም ቢሆን ግድቡ እንዲገደብ የህዝቡ ፍላጎት ከፍተኛና ስሜቱም ጠንካራ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡ መንግሥት ባለፉት 25 ዓመታት ግድቡን በራስ ወጪና በአገር ውስጥ የሰለጠነ የሰው ኃይልም ጭምር መገንባት እንደሚቻል ማሳየትና መስራት መጀመሩንም ይገልጻሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ውሃን 86 በመቶ የምታመነጭ አገር ብትሆንም፤ ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብቷ በሌሎች ኃይሎች ተደፍቆ ቆይቷል፡፡ ይህ መብቷ ግን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን መከበር ጀምሯል፡፡በአሁኑ ወቅትም የግንባታው 64 በመቶ ተጠናቅቋል፡፡
ታላቁ መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 2003 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ የሚያርፍበት ግድብ ነው፡፡ ህዝቡም ፊቱን በቁጭት ሲንገበገብ ቆይቷልና ግንባታው ይፋ ከተደረገ አንስቶ ድጋፉን በገንዘብ በእውቀትና በጉልበት እያደረገ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በግድቡ ሥራ ምንም የምትደብቀው ምስጢር የለም፤ በሯን ክፍት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለአፍታም ቢሆን ሥራ ፈትታ፣ ለሚነገረውም ወሬ ጆሮ ሰጥታ አታውቅም የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ዶክተር ያዕቆብ፣ የዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ጫና ተቋቁማ ግንባታውን እያካሄደች ትገኛለች ይላሉ፡፡ይህን እንቅስቃሴዋን የሚያስቆምም ሆነ የሚያስተጓጎል ኃይል አይኖርም፤ዜጎች ሙሉ እምነታቸውንና ድጋፋቸውን ሰጥተው የግድቡን መጠናቀቅ በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ለዓሳ እርባታ እና ለቱሪዝም መስህብ እንዲውል በማድረግ የውሃ ላይ ትራንስፖርት በመስጠትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደ/ማኖረው ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡
ዶክተር ታምራት ከህዳሴ ግድቡ ጀርባ ብሄራዊ መግባባቱ ስላለ ግንባታው ትኩረት አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ግድቡ ተጠናቆ ማየትን ይፈልጋል፤በህዳሴ ግድቡና በሌላው ልማት ላይ የሚነሱ ማናቸውንም ጉዳዮች ህዝቡ አንድ አድርጎ አይመለከትም፡፡ ግድቡ እያጓጓ በመምጣቱ ህዝቡን ከመቼውም ጊዜ በላይ አነቃቅቶታል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚያስገኘው ጥቅም በርካታ ነው የሚሉት አቶ ከበደ፣በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በአገሪቱ ትልቅ እንደመሆኑ ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር እንዲሁም የአገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የመሰለፍ ራእይ እንደሚያፋጥን ይጠቁማሉ፡፡ ለታዳሽ ኃይል ስትራቴጂው መሳካት የበኩሉን ሚና በመጫወትም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ይላሉ፡፡
ከህዳሴ ግድቡ ብዙ መማር ይቻላል የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ግድቡ በሌሎችም ልማት ሥራዎች የቱንም ያህል የፋይናንስ እጥረት ቢኖርም ህዝብና መንግሥት አንድ ላይ መስራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሳየቱን ይገልጻሉ፡፡
አቶ ከበደ ዋናው ጉዳይ ህዝብን በዚሁ ልክ ማንቀሳቀስ ከተቻለ የማይፈነቀል ድንጋይ አይኖርም በማለትም፣ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ልክ እንደ ህዳሴ ግድቡ ሁሉ በትኩረትና በተጠያቂነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይለግሳሉ፡፡

ዜና ትንታኔ
አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።