የሠራዊቱ ታላቅ የሰላም ጉዞ

የቴዎድሮስ አደባባይ ገና በጠዋቱ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት በተውጣጡ ሰልፈኞች ተከቧል፡፡ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም በአደባባዩ አብረው ተሰባስበዋል፡፡ በዚህ ቦታ በጋራ ያሰባሰባቸው ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ‹‹የህዳሴው ግድብ የሰላም ምንጭ ነው›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የሰላም ጉዞ ነው፡፡ 

ጉዞውን የሚመሩት የፌዴራል ፖሊስ ፈረሰኞች የህዳሴውን የሰላም ዋንጫ በማጀብ የቸርችል ጎዳናን ቁልቁል ሲወርዱ ፣የመከላከያ ማርሽ ቡድን አገራዊ ስሜትን የሚቀሰቀሱ ዜማዎችን እያሰማ ፈረሰኞቹን ተከትሏቸዋል፡፡
የመከላከያ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ሰልፈኞችን አስከትሎ ቀይ በለበሱ ፈረሰኞች የታጀበው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫ መስቀል አደባባይ ሲደርስ በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከፍተኛ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኦርኬስትራ የተለያዩ የፖሊስና የመከላከያ መዝሙሮችን ባስደመጠበት ወቅትም ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከጫፍ እስከ ጫፍ በማውለብለብ ለሥነ ሥርዓቱ ይበልጥ ድምቀት ሰጡት፡፡
ሠራዊቱ የሰላም ዘብ ሆኖ እንዲቀጥልና እስከአሁንም ለግድቡ ላበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫውን ለመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ አስረክቧል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ እንደሚገልጹት፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በህዝብ እየተገነባ ያለ ታላቅ ፕሮጀክት ሲሆን፣በዚህም የመንግሥት ሠራተኛው ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም እንቅስቃሴያቸው እውቅና ለመስጠት ‹‹የህዳሴ የሰላም ዋንጫ›› ተሰይሟል፡፡
የህዳሴ የሰላም ዋንጫን በተለይም ለመከላከያ ሠራዊቱ ለማስረከብ የተፈለገበት ዋነኛ ዓላማ ሌትና ቀን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በንቃት ለሚጠብቁ የሰላም ኃይሎች ጽሕፈት ቤቱ ያለውን ክብር ለመግለጽና እውቅና ለመቸር ፣ለህዳሴው ግድብ በቦንድ ግዢና በሌሎችም ድጋፎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና ለማቅረብ እንዲሁም ሠራዊቱ ለህዳሴው ግድብ የሰላም ዘብ መቆሙን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማነቃቃትም ሲባል ነው በማለት ወይዘሮ ሮማን አብራርተዋል፡፡
የሰላም ጉዞው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በመላው አገሪቷ የሚካሄድ ሲሆን፣መከላከያ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ እንቅስቃሴውን እየመራ ይቀጥልና በነሐሴ ወር የፖሊስ ቀን ሲከበር የመከላከያ ሚኒስቴር ለፌዴራል ፖሊስ የህዳሴውን የሰላም ዋንጫ ያስረክባል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እንደገለጹት፤ የፀጥታ ኃይሉ ህገመንግሥቱንና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ ድርሻው የጎላ ነው፡፡ ሰላም የልማት ምሶሶና የአገሪቱ ህዝቦች ህልውና እንደመሆኑ መጠን መላው የፀጥታ ኃይል ከመላው የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን የአገሪቷን ሰላምና ደህንነት እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ የአገሪቷን ፈጣን ልማት ባስተማማኝ ሁኔታ በማስቀጠል ብልጽግናዋን እውን ማድረግ የሚቻለው የብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የአገሪቷን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ሲቻል ነው፡፡
ይህንንም ተልዕኮ ባስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል፣ ህዝባዊ ባህርይ ያለው፣ህግ መንግሥታዊ እኩልነቱ የፀና፣ሞያዊ ሥነምግባሩ፣ሞራላዊና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅኑቱ የዳበረ የሰላም ኃይል መገንባት መቻሉን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ላለፉት ዓመታት ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች አገሪቷ ያቀደቻቸውን የልማት ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ መፈፀም እንዲችሉ ያደረገ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ተችሏል ይላሉ፡፡
የፀጥታ ኃይሎች ህዝቡ የሰላሙ ባለቤትና የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የህዝቡ ልዕልና ማሳያ የሆነውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሌት ተቀን በተጠንቀቅ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣በቀጣይም የግድቡን ደህንነት በንቃት የመጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ሠራዊቱ የአገሪቷን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ለልማቱ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከወር ደመወዝ ተቆራጭ በማድረግ በየዓመቱ ያልተቋረጠ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁንም በሰባተኛ ዙር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
የህዳሴውን ግድብ የሰላም ዋንጫ በመረከብም መላው የሰላም ኃይሎች በተሰማሩባቸው የአገሪቷ ክፍሎች ሁሉ በማዘዋወር በግድቡ ዙሪያ እስከአሁን የተደረገው ንቅናቄና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ተግባርን የበለጠ የሚያነሳሳ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዜና ሐተታ
አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።