መከላከያ ሠራዊቱና ህዝቡ ምንና ምን ናቸው?

በጉልህ ተጽፎ በአዳራሹ መድረክ አካባቢ ለሁሉም እንዲታይ ተደርጎ የተሰቀለ አንድ ጽሁፍ ይታያል፡፡ በውስጡም ሦስት መሰረታዊ ገዳዮችን ይዟል፡፡ የመጀመሪያው ሠራዊቱ ህዝባዊ ባህሪውን እንዲያጎለብት የሚጠቁምም ነው፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ የሆነው የህገ መንግሥቱ ሥርዓት በሠራዊት የሚጠበቅ ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡ በመጨረሻም አገሪቱ እያካሄደች ላለው የህዳሴ ጉዞ ዋስትና ሆኖ ሠራዊቱ እንዲቆም ያስረዳል -‹‹ህዝባዊ ባህሪችንን እያጎለበትን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን በመጠበቅ የሀገራችን ህዳሴ ዋስትና ሆነን እንቆማለን›› የሚለው 6ኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን መሪ ሃሳብ፡፡ 

ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመከላከያ ቀን በዓል እየተከበረ ሲሆን፣የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በትናንትናው ዕለትም የሠራዊቱ አባላት በአዲስ አበባ ከተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጃን ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የመከላከያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከክፍለ ከተማው ከመጡ የህዝብ ተወካዮች ጋር በተካሄደው የፓናል ውይይት፣ የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት ብርጋዴር ጀኔራል ይልማ መኳንንት እንደተናገሩት፤ ከህዝብ ጋር መወያየት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱም ዓላማ ሰላምንና የህዳሴ ጉዞን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው፡፡
ብርጋዴር ጀኔራሉ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የሠራዊት አመሰራረትንና ዘመናዊነትን አስመልክተው ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ ኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረስ ያለውን ሂደት አብራርተዋል፡፡ ሁሉም የየራሱ ጥንካሬ እንዳለው ሁሉ ድክመት ያለበት ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በህዝብ ብሶት የተወለደ ሠራዊት ነው፡፡ ተልዕኮውም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከውጭ ወራሪ ኃይሎችንና ልማቱ በሰላም እንዳይካሄድ የሚያደርጉ እንቅፋቶችን መከላከል ነው፡፡ ሠራዊቱ ከሙያ አኳያም ሲታይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም በሚችል የሰው ኃይል ተገንብቷል፡፡
ሠራዊቱ የተጎዱ እና አቅም ያጡ ወገኖችን በመርዳት ግንባር ቀደም መሆኑን የሚገልጹት ብርጋዴር ጀኔራሉ፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎች በመሳተፍ ወገኑን የሚያገለግል እንደሆነም ይናገራሉ፡፡በእንቅስቃሴዎቹና በውጤታማነቱም በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ከማትረፉም በተጨማሪ ከውጭ አገራትም ሽልማቶችን ማግኘት መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡
ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ህዝብን ወክለው በመጡ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ሠራዊቱ የእናት ልጅ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፤ የአገር የልብ ትርታ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ተልዕኮዎችም ድልን የተቀዳጀ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ለዚህም የህዝብ አጋርነት ሚናው ጎልህ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፤ የቀድሞው ሠራዊት አገሪቱን በጦር፣ በጋሻና በመሳሰሉት በመጠቀም ከውጭ ወራሪ ኃይሎች በመጠበቅ ለዛሬ አብቅቷታል ያሉት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የመጡት ነዋሪ አቶ እሸቱ ማሞ ፣ትናንት ጀግና ከነበረው የተወለደው መከላከያ ሠራዊትም አሁን እያደረገ ያለው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ እቴነሽ ቀጄላ እና ወጣት ቤተልሄም ከተማ በየበኩላቸው፤ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚችሉት አግርን የሚጠብቅ መከላከያ ሠራዊት በመኖሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከውይይቱ ሰፊ ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፤ በውጭ የሚወራውና አሁን የተረዱት ሰፊ ልዩነት እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በሠራዊቱ ላይ የሚሰነዘረው ትችት ሠራዊቱን የማይወክለው መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡
ተሳታፊዎቹ ጥያቄዎችንም አንስተዋል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች አካባቢ የሚታዩ ግጭቶች ስጋት ላይ ከመጣላቸውም በተጨማሪ ገዳይና ሟችም ባለመታወቁ ምን መደረግ ይኖርበታል? የመከላከያ ሠራዊቱ በጀት እጅግ ያነሰ ነውና ስለምን አይጨመርም ? መከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ ቦታዎች በኮንትሮባንድ ሥራ ውስጥ ተዘፍቋል ይባላል በዚህ ላይ ምን ትላላችሁ ? ሠራዊቱ የአንድ ፓርቲ ጠባቂ ነው ይባላልና ይህስ እንዴት ይታያል? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የዕለቱ አወያይና ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ሜጀር ጀኔራል ሀለፎም እጅጉ እንደተናገሩት፤ጥያቄዎቹም ሆኑ የተሰጡት አስተያየቶች ገነቢ ናቸው፡፡ ካለፈው ሠራዊት በርካታ ትምህርት የሚገኝበት ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ሕዝብን ማስከበር የሚያስችል ባህሪው የሚወሰድለት ጉዳይ ነው፡፡
ሠራዊቱ የህዝብን ጥቅም የሚያስከበር እንጂ የማንም ፓርቲ ጥገኛ አለመሆኑን ሜጀር ጀኔራሉ ይናገራሉ፡፡ በህዝብ አመኔታ እንዳይኖረው ጥቂቶች እንደሚናገሩ ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ ግን ከህዝብ አብራክ የተወለደና ህዝብን የሚያገለግል እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ የውትድርና ሙያ የሚለካው በህይወት እንጂ በገንዘብ እንዳልሆነም ይገልጻሉ፡፡
ሜጀር ጀኔራል ሀለፎም እንዳሉት፤ የጸጥታ መደፍረስን ማረጋጋት የሠራዊቱ ሚና ነው፤ ይሁንና የደፈረሰን ሰላም ለመመለስ ሲባል በሚደረገው እንቅስቃሴ አላስፈላጊ እርምጃ ደግሞ መወሰድ የለበትም፡፡ አንዳንዶች ግን ለሠራዊቱ ያልተገባ ምስል ለመስጠት ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ ህዝብ ደግሞ ቅሬታ ካለው ህገ መንግሥታዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ የሚችል ሲሆን፣መፍትሄም የማግኘት መብት አለው፡
‹‹እኛ የእናንተው ልጆች ነን፤ የምንጠብቀው ሰላማችሁን ነው፡፡ በመሆኑም የእናንተ ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ስናጠፋ ልታርሙን ይገባል›› ያሉት ሜጀር ጀኔራሉ፣ የሠራዊት በጀት ለተባለው ደግሞ አገር ስታድግ የሚያድግ በመሆኑ በአገሪቱ ዕድገት ላይ የሚወሰን መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የበዓሉ ባለቤትና የዕለቱ ውይይት ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት ሌተናል ኮረኔል ሮማን ገብረክርስቶስ በዓሉ የሠራዊት በዓል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ሠራዊቱ ህዝቡ፣ ህዝቡም የሠራዊቱ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹ሠራዊቱ የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው፡፡ ህዝብም እንዲሁ ነው፡፡ ሠራዊት ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሁሉ ለአገሪቱም ህዳሴም ከህዝቡ ጋር ሆኖ የበኩሉን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ዜና ሐተታ
አስቴር ኤልያስ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።