የነዋሪዎቹን የውሃ ጥም የቆረጠ ፕሮጀክት Featured

የከተማዋ ነዋሪዎች የሚገለገሉበት የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ አቅም ውስን እየሆነ መምጣት የውሃ ፍላጎታቸውን ማርካት ተስኖት በመቆየቱ ሳቢያ በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ለዓመታት ተፈትነዋል፡፡ነዋሪዎቹም ውሃ ለመቅዳት ረጅም መንገድ መጓዝ ከዚያም ወረፋ መጠበቅ የግድ ሆኖባቸው ኖሯል ፡፡

ወይዘሮ መስታወት አህመድ የዚህች የደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ ለሚ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ገፈት ቀማሽ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ መስታወት ፣የከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አነስተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ውሃ ለመቅዳት ሌሊት መነሳት እና ወረፋ መያዝ የግድ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ መስታወት ፣ወረፋው አንዳንዴ እስከ ማግስቱ ከቀኑ አስር ሰዓት ይዘልቅ እንደነበር በትዝታ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ እንግልቱ ከፍተኛ እንደነበር ይገልጻሉ ፡፡
ወይዘሮ መስታወት አሁን ከዚህ አስከፊ ችግር ተላቀዋል፡፡ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት ድጋፍ በከተማው በተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ትልቅ እፎይታ አግኝተዋል፡፡ የውሃ ጥማቸውን ከማርካታቸውና ምግብ ከማብሰል ባሻገርም ልብስ ለማጠብ አይቸገሩም፡፡ ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት በመጓዝ ጉልበታቸውን አያባክኑም፤ ጊዜም አያጠፉም፡፡ ተማሪ ልጆቻቸውም ውሃ ለመቅዳት ሲያጠፉ የነበረውን ጊዜ በትምህርትና ጥናታቸው ላይ አውለዋል፡፡፡
ወይዘሮ ሸዋዬ ሃይሉም የለሚ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማነስ ምክንያት ሲቸገሩ ኖረዋል፡፡ እሳቸውም እንደሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ውሃ ለመቅዳት ረጅም ርቀት ይጓዙ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ የወንዝ ውሃ ጭምሮ ቀድቶ እስከ መጠቀም ደርሰውም ነበር፡፡ የወንዝ ውሃ መጠቀማቸው እርሳቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ለበሽታ እንዲጋለጡ አርጓቸዋል፡፡ በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለረጅም ጊዜ ተፈትነዋል፡፡፡
ወይዘሮ ሸዋዬም ይህ ችግራቸው በሰዎች ለሰዎች ድርጅት አማካኝነት በተገነባው የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መወገዱን ይገልጻሉ፡፡ በፕሮጀክቱ በየደጃፋቸው የቦኖ ውሃ መሰራቱን ገልጸው፣ ያለድካም ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
የወግዲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንድሪስ ይማም እንደሚገልፁት፤የለሚ ሮቢት ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንደ ልብ የማይገኝባት ከተማ ሆና ቆይታለች ፡፡ ከተማዋ ከታዳጊ ወደ ንኡስ ከተማ እያደገች መምጣቷን ተከትሎ የከተማው ነዋሪ በመጨመሩ በከተማዋ የነበረው መካከለኛ የጉድጓድ ውሃ ለነዋሪው በቂ ሊሆን አልቻለም፡፡
ከአገልግሎት ብዛትም የውሃ መቆራረጥ በተደጋጋሚ ያጋጥም ነበር፤በዚህ የተነሳም ነዋሪው እስከ ስምንት ወር ውሃ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር የሚሉት አቶ እንድሪስ፣ የሌሎች አጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎችም እስከ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓዝ ውሃ ለመቅዳት ተገደው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የነዋሪውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በወረዳው በመገኘት መመልከቱን የወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታትም ከወረዳው ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ጋር ጥናት እንዲካሄድ ማድረጉን ፣ እስከ 2009 ዓ.ም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅም ወደ ግንባታ መገባቱን ይናገራሉ፡፡
በግንባታው ሂደት የአካባቢው ነዋሪ በጉልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቅሰው፣ አስር ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ መስመር መዘርጊያ ቁፋሮ ማካሄዱን ያብራራሉ፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ይላሉ፡፡
በፕሮጀክቱ የህብረተሰቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መልስ ማግኘቱን የሚናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ፣በቀጣይም የውሃው አቅም እየታየ እያንዳንዱ ነዋሪ በየቤቱ ውሃ የሚያገኝበት ሁኔታ የሚመቻች ይሆናል ብለዋል፡፡
በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የቦረናና ወግዲ ወረዳ የተቀናጁ የገጠር ልማት ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳነ ንጉስ እንደሚገልፁት፤ ድርጅቱ በግብርና ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በአካባቢ ንፅህናና ትምህርት ዙሪያ የተቀናጁ የገጠር ልማት ፕሮጀክቶችን ያከናውናል፡፡ በቦረናና ወግዲ ወረዳዎች ከተከናወኑ የገጠር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የለሚ ሮቢት ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ነው፡፡ የለሚ ሮቢት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2015 ተጀምሮ በ2018 ተጠናቋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 14 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡
ከ6ሺ200 በላይ የሚሆኑ የከተማዋንና የአጎራባች የቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት አቶ አዳነ፣ ለሰላሳ ዓመታትም አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ መሰራቱንም ይገልጻሉ፡፡
የከተማው ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ከሦስት እስከ አራት ሰዓት በመጓዝ ከወንዝ ውሃ ይቀዱ እንደነበር አቶ አዳነ አስታውሰው፣ በዚህም ምክንያት ጉልበታቸውና ጊዜያቸው ሲባክን መቆየቱን ያብራራሉ፡፡ በተለይም ሴቶች ትምህርታቸውን እስከ ማቋረጥ ይደርሱ እንደነበር አስታውሰው፣ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን መሰረታዊ ችግር መፍታቱን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በእነዚሁ ወረዳዎች ሌሎች የተቀናጁ የገጠር ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው፣ በወግዲ ወረዳ የማካፍታ የንፅህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ ይህም ፕሮጀክት መሰረታዊ ችግር ያለበትን አካባቢ በመለየት በተካሄደ ጥናት ላይ ተመስርቶ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅትም የጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቆ የመስመር ዝርጋታ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ዜና ሐተታ
አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።