የኢንዱስትሪ ማዕከላቱን ለኮርፖሬሽኑ የማስተላለፉ ሥራ አልተሰራም ተባለ

አዲስ አበባ፡- ለሥራ ዕድል ፈጠራ በማለት ለተለያዩ አካላት የተሰጡ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን (ሼዶችና ህንጻዎች) ለኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የማስረከቡ ሥራ እንዳልተሰራ የፌዴራል የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የማኑፋክቸሪንግ ፋሲሊቴሽንና ትራንስፎር ሜሽን ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ገብረማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ19/97እና 98 ዓ.ም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተብለው ለተለያዩ ግለሰቦችና ማህበራት የተሰጡ የማምረቻ ቦታዎችን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ለተሰጠው የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን አልተላለፉም።
በደቡብና ትግራይ ክልሎች ማዕከላቱን ለኮርፖሬሽኑ ማስረከብ መቻሉን አቶ ደጀኔ ጠቅሰው፣አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ግን ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከላት በብዛት መገኘት ብሎም የተለያዩ አካላት ባለቤት ነን ማለታቸው ሥራውን እንዳጓተተው ገልጸው፣ ይህንን ለማስተካከል በመንግሥት በኩል በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በሌላም በኩል አዲስ አበባ የማምረቻ ቦታዎቹን የያዙትን አምራች ኢንዱስትሪዎች እናንተ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋግራችኋልና ማዕከላቱን ለሌሎች ልቀቁ በማለት የማስለቀቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ደጀኔ ጠቅሰው፣ይህ ድርጊት ፍጹም ስህተት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉ የአመራር አባላት እና በየደረጃው ያሉ ሠራተኞች ከፍተኛ የግንዛቤ ክፍተት እንደሚስተዋልባቸውም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ደጀኔ ማብራሪያ፤ ይህንንም ለማስታረቅ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ሥራውን የሚያውቀውንና በርካታ የሰው ኃይል ወደ ሥራ ያስገባውን እንዲሁም ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ወጪን በመቀነስ ላይ የተሰማራውን መደገፍ ያስፈልጋል።
አገሪቱ የምትከተለው ሥርዓት ባለሀብቱ በልማቱ ሥራ ከመንግሥት በላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያበረታታ ሲሆን፣አምራቹ በዚህ መልኩ መሳተፉ ሥራ አጡን በመቅጠር ልምድ እንዲያገኝ በማድረግና በረጅም ጊዜም ራሱን እንዲችል በማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡
መንግሥት ሥራ አጦችን ወደ ሥራ ለማስገባት በብዙ ሚሊዮን ብር በማውጣት የተለያዩ የማምረቻ ማሽኖችን ማቅረቡን ተናግረው፣ ገንዘቡን ማስመለስ ግን ሳይቻል መቅረቱን አቶ ደጀኔ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ልምድ በመቅሰም ከአሁን በኋላ በጀማሪነት ወደ ሥራ ገብቶ ለውጥ ያመጣል በማለት በሥራው ብዙ ልምድ ያላቸውንና ለብዙዎችም የሥራ ዕድል የፈጠሩትን ማባረር ተገቢነት እንደሌለው አስገንዝበዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው በተጨባጭ አሁን ወደ ገበያ የሚቀርብና የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀር በአንጻሩ ገቢን የሚያመጣ ፣ በእጅ ያለ እና በተለይም አሁን ያለብንን የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚቀርፍ ሆኖ ሳለ የሥራ ዕድል ፈጥረናል ለማለት ብቻ ይህንን አካል መግፋቱ ተገቢነት አይኖረውም ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የወጪ ምርት አምራች ኢንዱስትሪ ከተገኘ የማምረቻ ቦታ በቅድሚያ ሊያገኝ እንደሚገባው ኃላፊው ጠቁመው፤ በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን የሚተካ ምርት የሚያመርት ኢንዱስትሪ ከሆነ ቀጥሎ ቅድሚያ እንደሚያገኝም አስታውቀዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ እንደ ምርታቸው አስፈላጊነት ዕድሉን ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
‹‹የማምረቻ ቦታ ወስዶ አከራይቶ የሚጠቀም አልያም የሌላን ሰው ምርት ሸጦ ለሚጠቀም ቦታዎቹን መስጠት ግን ብክነት ነው›› ያሉት አቶ ደጀኔ፤ ይህ አካሄድ ግለሰቡንም አገርንም እንደማይጠቅም ተናግረዋል፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለም አምራች ኢንዱስትሪው እንደሚቀጭ ጭና ይህንን የአስተሳሰብ ዝንፈት ማስተካከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
እነዚህን ነባሮቹን በተለይም ተዘግተው እንዲሁም ለሁለተኛ ወገን ተላለፈው ያሉትን ማዕከላት ከፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ወደ ኮርፖሬሽኑ ማዘዋወር የግድ መሆኑንም ተናግረዋል።
ነባሮቹ የማምረቻ ማዕከላት በንግድና አገልግሎት ላይ በተሰማሩ ፣ለሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል የሌሎችን ምርቶች በመሸጥ ላይ በሚገኙ ሰዎች የተያዙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ ተዘግተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እጸገነት አክሊሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።