በሥራ ባህል መዳከም እና በድንጋይ ከሰል እጥረት የተፈተነ ዘርፍ Featured

በአገሪቷ የሚገነቡ ፋብሪካዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ጠንካራ የሥራ ባህልን የተላበሰ ሠራተኛ ያስፈልጋቸዋል። በአብዛኛው ፋብሪካዎች ውስጥ ግን ከሥራ የሚቀሩ፣ የሚያረፍዱ እና ሥራ ይዘው የሚያዘገዩ ሠራተኞች እንደሚገኙ ከድርጅቶቹ እንደቅሬታ ይነሳል። ይህም በምርት መቀነስ እና በትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ ደግሞ የጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ከደካማ የሥራ ባህል በተጨማሪ የግብዓት እጥረት ያጋጥማቸዋል።
በተለይ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ወጪ ንግድ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ በሚገኘው አይካ አዲስ ቴክስታይል ፋብሪካ ላይ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ የድንጋይ ከሰል ግብዓት እጥረት እየፈተነው መሆኑን የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል። ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ግብዓት ጋር ተያይዞ እጥረት በማጋጠሙም የገበያ ትዕዛዞቹን በወቅቱ ማድረስ አለመቻሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የዘርፉን የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ላይ ጥሎታል። ያሳደረው ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑ ድርጅቱ ይገልፃል።
የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ገቢና ወጪ ንግድ ሎጂስቲክ ማናጀር አቶ ቢንያም አብረሃም እንደሚናገሩት፤ ፋብሪካው ባለፉት ስድስት ወራት ከተቀባዮቹ ፍላጎት ጋር የተጣጣም ምርት ማቅረብ አልቻለም። ችግሮቹ አንድም ከግብዓት በሌላም በኩል ከሥራ ባህል ጋር የተያያዙ ናቸው።
ፋብሪካው የሀገሪቷን የዘርፉን ወጪ ንግድ ከግማሽ በላይ ድርሻ የሚይዝ ነው። ነገር ግን የሥራ ባህላቸው ያደገና በሰዓቱ ምርት ለማድረስ የሚያስችሉ ሠራተኞችን ከገበያው ማግኘት አዳግቶታል። የሠራተኞቹ የሥራ ተነሳሽነት ከዚህ ቀደም ካለው የተሻለ ቢሆንም በወጪ ንግዱ ላይ በስፋት ለመሳተፍ ቢፈልግም አሁንም ደካማ አሰራር ይታይበታል። በቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመው አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አገር ውስጥ እስከተገነባ ድረስ የኢትዮጵያውያንም ሃብት በመሆኑ ውጤታማ እንዲሆን የሠራተኞችን የሥራ ባህል ለማዳበር ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አቶ ቢንያም ይናገራሉ።
አይካ አዲስ ለሚያመርታቸው ጨርቃጨርቅ ማቅለሚያ ግብዓትነት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል እጥረት ማጋጠሙ ባለፉት ስድስት ወራት የምርት መቀነስ እንዲገጥመው ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። በግብዓት እጥረቱ ምክንያትም በውጭ አገራት ለሚገኙ ደንበኞቹ ማድረስ የነበረበትን ምርት በሚፈለገው ደረጃ ማቅረብ አልተቻለም። አይካ አዲስ በቀን 80 ቶን የድንጋይ ከሰል ምርት ያስፈልገዋል። የድንጋይ ከሰል ምርቱን ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚረከብ ቢሆንም፤ የምርት እጥረት በመፈጠሩ በቂ ማቅለሚያ ማግኘት አልቻለም። ከክር ጀምሮ እስከ መጨረሻው የጨርቃጨርቅ ምርት ድረስ የተለያዩ ህብረ ቀለማትን ለመፍጠር የድንጋይ ከሰል እና ጨው አስፈላጊነታቸው ከፍተኛ ቢሆንም በቂ ግብዓት በወቅቱና በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን አቶ ቢንያም ይገልጻሉ።
«ፋብሪካው አምርቶ ገዢዎችን በማፈላለግ የሚሸጥ ሳይሆን በትዕዛዝ የቀረቡለትን የሚያመርት ነው» የሚሉት አቶ ቢንያም፤ በግብዓት እጥረት ምርት በወቅቱ ያልደረሰላቸው ደምበኞች በተለይም የጀርመን መዳረሻዎች በቀጣይ ትዕዛዝ ለመስጠት ያላቸው ፍላጎት ይቀንሳል። በመሆኑም ድርጅቱ ወደኪሳራ እንዳያመራ አቅርቦቱን መንግሥት እንዲያሟላ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባው ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባንቲሁን ገሰሰ እንደገለጹት፤ የውጭ ድርጅቶች የእራሳቸውን እውቀት እና ልምድ ይዘው ይመጣሉ። በቂ አቅምም አላቸው። ነገር ግን አገር ውስጥ ጨርቃጨርቅ በሚያመርቱበት ወቅት የሚፈልጉትን ያህል ባለሙያ ላያገኙ ይችላሉ። የሰው ኃይሉን ለሥራ ያለው አመለካከት እና በቂ እውቀት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ሳይሆን በሂደት የሚዳብር ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ክህሎት በሂደት እየተሻሻለ የሚመጣ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ምርት ማዘጋጀት የሚችል የሰው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ አጫጭር ስልጠናዎች አማካኝነትም ቀደም ካሉ ዓመታትም የተሻለ የሥራ ዕውቀትና የሥራ ባህል እየዳበረ መምጣቱን መመልከት ይቻላል። ችግሩ ግን የሰለጠኑ ባለሙያዎች የደመወዝ እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ፍለጋ ከአንዱ ፋብሪካ ወደሌላው የሚያደርጉት ፍልሰት ነው። በመሆኑም ባለሙያዎቹን ጠብቆ ምርታማነቱን ለማስቀጠል ድርጅቶቹ በየጊዜው የእራሳቸውን የማትጊያ መንገዶች መጠቀም እንደሚኖርባቸው አቶ ባንቲሁን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ባንቲሁን ማብራሪያ ከሆነ፤ አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በሌላ በኩል ያሉበት የግብዓት እጥረት የተፈጠረው በትስስር ክፍተት ምክንያት ነው። በተለይ በድንጋይ ከሰል ምርት አቅርቦት ከባለሃብቶች ወደ ሥራ አጥ ወጣቶች በመሸጋገሩ ከፋብሪካው ጋር በቂ ግንኙነት አልተደረገበትም። የግብዓት ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ አምራች የሆኑት ወጣቶችን ከፋብሪካዎች ጋር በማስተሳሰር ምርት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል። የግብዓቱ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ በመከናወኑ የአምራቾች የማቅለሚያ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታ ይጠበቃል። በየዕለቱ በአምራቾች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን እየመዘገቡ መረጃ የሚያቀርቡ ባለሙያዎችም በመመደባቸው ከሥር ከሥሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የጥናትና ክትትል ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አበበ በበኩላቸው፤ የአይካ አዲስ ዋነኛው ችግር የግብዓት እጥረት በተለይም የድንጋይ ከሰል ግብዓት ነው። ፋብሪካው ከኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የያዮ ማዳበሪያ ድንጋይ ከሰል ልማት ፕሮጀክት የድንጋይ ከሰሉን ይረከብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከያዮ ማምረቻ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲያለሙ በመፈቀዱ ምርቱን ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ጌዶ አካባቢ ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው 100 ቶን ድንጋይ ከሰል ለማምረት በሂደት ላይ በመሆናቸው ለተለያዩ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ግብዓቱም ማቅረብ የሚያስችል ዕድል እየሰፋ መሄዱን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፤ አይካ አዲስ ነባር ፋብሪካ በመሆኑ የልምድ ማነስ እና ደካማ የሥራ ባህል ያላቸው ሠራተኞች በብዛት የሉትም። እንደውም ችግሩ በአዳዲስ ፋብሪካዎች ላይ የጎላ በመሆኑ የተለያዩ የማበረታቻ መንገዶችን በሠራተኞች ላይ መጠቀም ያስፈልጋል። ማትጊያዎች በብዙ ቁጥርም የኢንዱስትሪውን የሥራ ባህል ማሳደግ ይቻላል።

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።