‹‹የአዋጁ መጽደቅ የአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቀመናብርት የጋራ ውሳኔ ነው››- አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ Featured

አዲስ አበባ፡- ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኢህአዴግ አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቀመናብርት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተውና ተስማምተው የጋራ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ጸድቋል›› ሲሉ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገለጹ፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከትናንት በስቲያ በጽህፈት ቤታቸው ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ የአዋጁ መጽደቅ የአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የጋራ አቋም ነው፡፡ በተጨማሪም እንደግንባሩ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔና አቋምም ነው፡፡
በአዋጁ መጽደቅ ላይ ምንም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ሽፈራው፣ አዋጁ ከመጽደቁ አስቀድሞ ገና በመጀመሪያው ላይ አፈ ጉባኤው ከ547ቱ የምክር ቤት አባላት መካከል አራት ሰዎች በህይወት አለመኖራቸውን፤ አራቱ ደግሞ በተለያየ ምክንያት በአገር አለመገኘታቸውንና በዕለቱ 490 ሰዎች መገኘታቸውን በመግለጽ ስብሰባውን ያስጀመሩት ይሄዳሉ:: ምልዓተ ጉባኤው መሟላቱን አረጋግጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህንንም በዕለቱ የተገኙት የመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው፣ በየትኛውም ስሌት ለአዋጁ መጽደቅ በቂ ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ድምፅ ሲቆጠር ግን ቆጣሪዎች የፈጠሩት ስህተት መኖሩን አልሸሸጉም፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ዛሬ እንደሚጀምር የተናገሩት አቶ ሽፈራው፤ ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል በዋናነት ከአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የሚቀርቡትን ሪፖርቶች የሚመለከተው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሟት እንደመሆኑ ለዚህም መነሻው ምንድነው በማለት ፍተሻ ተደርጎ መፍትሔ እንደሚቀመጥም አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፉት ወራት ይህን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፡፡ ድርጅቱ ጊዜ ወስዶ ከታኅሣሥ 3 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ታሪካዊ የሚባል ውይይት አድርጓል፡፡ መርህ አልባ ጉድኝት መስፈኑ፤ አድርባይነት መንገሡ ተገምግሟል፡፡ ይህም በትግል ይፈታ ነበር ሲል አምኗል፡፡
በተለያየ መንገድ ህግ የተላለፉ አካላትን በይቅርታ በመልቀቅ ዴሞክራሲውን ለማስፋት ጥረት መደረጉን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህ ሲደረግ ግን በማንም ጫናና ግፊት ሳይሆን ለዓላማችንና ለመርሐግብራችን ስኬት ስንል ነው›› በማለትም አስረድተዋል፡፡
ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በነገው ዕትማችን ፖለቲካ ገጽ እናቀርባለን፡፡

አስቴር ኤልያስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።