የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ከመጋቢት 10 እስከ 17 ይካሄዳል Featured

የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ከመጋቢት 10 እስከ 17 ይካሄዳል ፎቶ - በሐዱሽ አብርሃ

አዲስ አበባ፡- ከመጋቢት 10 እስከ 17 ቀን 2010 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት እንደሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የህዳሴ ግድቡ መሰረት የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት በማስመልከት የተለያዩ ሁነቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በጽህፈት ቤቱ በህዝብ ግንኙነት ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ከመጋቢት 10 እስከ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ያለው ጊዜ የቦንድ ሳምንት ሲሆን፣ በእነዚህ ቀናት በመላ አገሪቱ ቦንድ የሚሸጥበት ጊዜ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ሚያዚያ 21 ቀን 2010 ዓ.ም በመላ አገሪቱ እስከ 500 ሺ ሰዎችን ለማሳተፍ የታቀደበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሩጫ ይከናወናል፡፡
አቶ ኃይሉ እንደገለጹት፤ መጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ኪነ ጥበባት ምሽት በአዲስ አበባ ብሄራዊ ቴአትር እንዲሁም መጋቢት 16 መቀሌ ላይ የሙዚቃ ኮንሰርት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከመጋቢት 19 እስከ 24 ቀን የሚቆይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፎቶ እና የስዕል አውድ ርዕይ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ባህል አዳራሽ ይኖራል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግድቡን የጎበኙ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር ወደ 260 ሺ እንደሚጠጋ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ወደ 400 የሚጠጉ የአገር ውስጥና የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃንም እንደተመለከቱት አብራርተዋል፡፡ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆነ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የተለያዩ ልዑካን ቡድንም በስፍራው ተገኝተው መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከውጭ አገር ጎብኚዎች የሚያገኙት ግብረ መልስ፣ ግድቡ በትክክለኛው መንገድ እየተሰራ እና በኢትዮጵያውን አቅም እየተገነባ ስለመሆኑ ያላቸውን አድናቆት የሚያመለክት ነው፡፡ በተጨማሪም አገሪቱ በፈጣን ዕድገት ላይ ስለመሆኗ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የአገር ውስጥ ጉብኚዎች ደግሞ ቦታው ከደረሱ በኋላ የሚሰጡት አስተያየት በአንድም ሆነ በሌላ ያበረከቱት ገንዘብ በትክክልና በአግባቡ ውጤት እያሳየ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለበለጠ ድጋፍ የተነቃቁ ስለመሆ ናቸው ያመለክታሉ፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑም ግድቡን አስመልክተው የሚያሰራጯቸው አዎንታዊ ዘገባዎች መሆናቸውን ማስተዋል ተችሏል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከህዝቡ ቃል ከተገባው 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መካከል እስከ ታኀሣሥ ወር 2010 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የተሰበሰበው 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ግድቡ በአሁኑ ወቅት 64 በመቶ ላይ መድረሱን አመልክተዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡ መሰረት የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት በማስመልከት እስካሁን የተለያዩ ሁነቶች በመከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከተከናወኑትም መካከል ዋና ዋናዎቹ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን አስመልክቶ የተዘጋጀ ውይይት፣ የፎቶ አውደ ርዕይ፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አምባሳደር 2010 የቁንጅና ውድድር እና የመሳሰሉ ይገኙባቸዋል፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ሰባተኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ግድቡ እየተገነባ ባለበት በጉባ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል፡፡  


አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።