ደም ልገሳውና ህክምናው - በሴቶች ብቻ

የዘንድሮው የሴቶች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ42ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በመንግሥትና በግል መስሪያ ቤቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ የአለርት ማዕከልም ቀኑን በተለያዩ መርሐግብሮች ትናንት ያከበረ ሲሆን፣ የተቋሙ ሠራተኞችና የህክምና ባለሙያዎች ደም ለግሰዋል፡፡ በሴቶች ብቻ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎትም ተከናውኗል፡፡
በማዕከል ድንገተኛ ክፍል በፕሮፌሽናል ነርስነት የሚያገለግለው አዳነ ቦጋለ፣ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ደም ከለገሱ የተቋሙ የህክምና ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ በደም እጥረት ምክንያት በርካታ እናቶች፣ አደጋ የደረሰባቸው ህፃናትና ሴቶች እየሞቱ ነው፡፡ ይህን የደም እጥረት ለማቃለል የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የማዕከሉ የሕክምና ባለሙያዎችና ሠራተኞች የጀመሩት ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ደም የመለገሱ ልምድ በቋሚነት በየሦስት ወሩ ተግባራዊ ቢሆን የሰውን ህይወት መታደግ ይቻላል፡፡
ፕሮፌሽናል ነርስ አዳነ፣ ደም ሲለግስ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ጠቅሶ፤ ከአሁን ቀደምም ሦስት ጊዜ እንደለገሰና በቀጣይም በየሦስት ወሩ ደም ለመለገስ ፍላጎት እንዳለው አስረድቷል፡፡ እርሱ በሚሰራበት የሥራ ክፍል በርካታዎች በአደጋ ምክንያት ደም ሲፈሳቸው ስለሚያይና የደም እጥረት አጋጥሟቸው ሲቸገሩ በማየቱ እርሱና በድንገተኛ ክፍል የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ደም ለመለገስ መወሰናቸውን ይገልፃል፡፡ ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም በተመሳሳይ ምንም ሳይሰስቱ ደምን በፍቃደኝነት ቢለግሱ የሰውን ህይወት ከማዳን ባሻገር የአዕምሮ እርካታ እንደሚያገኙም ይናገራል፡፡
ዶክተር ስመኝ አሰፋ በአለርት ማዕከል የጥርስ ሐኪም ስትሆን፣ ማዕከሉ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ባዘጋጀው ሴቶች ብቻ በሚሳተፉበት የህክምና አገልግሎት ለታካሚዎች ከሰጡት ውስጥ አንዷ ናት፡፡ የሴቶች ቀንን ታሳቢ በማድረግ ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የህክምና አገልግሎት በማዕከሉ መዘጋጀቱ መልካም ጅማሬ መሆኑንም ጠቅሳ፤ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በተለይ ሴቶች የጥርስ  ህክምናን ጨምሮ ሁሉንም ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ስትል ትናግራለች፡፡ በጥርስ ህክምና ክፍል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች በመሆናቸውና ለታካሚው የሚሰጡትም አገልግሎት ጥሩ የሚባል በመሆኑ እስካሁን ምንም ዓይነት ቅሬታዎች ከታካሚዎች አልመጡም፡፡ ይህም ሴቶች በጥራትና ታካሚን በሚያረካ መልኩ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ የሚያሳይ መሆኑንም ታመለክታለች፡፡
እንደ ዶክተር ስመኝ ገለፃ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በሴቶች ብቻ የተካሄደው እንዲህ ዓይነቱ የህክምና አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሴቶችም ከወንዶች እኩል የመስራት አቅሙ እስካላቸው ድረስ ወደኋላ ማፈግፈግ የለባቸውም፡፡ የ‹‹ይቻላል››ን መንፈስ በውስጣቸው ከሰነቁ ሁሉንም ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሴት በመሆናቸው ብቻ በጾታቸው ምክንያት ተብሎ ሊያግዳቸው የሚችል ነገር አይኖርም፡፡ ሴቶች በሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ላይ ታካሚዎች የሚሰጧቸው ገንቢ አስተያየቶችም በቀጣይ ሴቶችን የሚያበረታቱና ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ስንቅ የሚሆኑ ናቸው፡፡
በአለርት ማዕከል የህክምና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ኃይሉ ታምሩ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በማዕከሉ ሰፊ የጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የጤና አገልግሎቶችም በሴቶች የሚሰጡ ናቸው፡፡ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግም ሴቶችን ብቻ አሳታፊ የሆነ የህክምና አገልግሎት ተካሂዷል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ አላማ ሴቶች በህክምና አገልግሎት ዙሪያ ያላቸውን ሚና አጉልቶ ለማሳየት ነው፡፡ የህክምና አገልግሎት ሙያዊ ዲስፕሊን የሚጠይቅና ውስብስብ በመሆኑ ሴቶች በየትኛውም የህክምና ደረጃ ላይ መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት በማሰብም ጭምር ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሴቶች ሁሉንም የህክምና አገልግሎት በሚሰጡ ቦታዎች ላይ በተሻለ መልኩ መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት ተፈልጎ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ኃይሉ ገለፃ፤ ሙሉ በሙሉ የወንዶች ተሳትፎ ሳይኖርበት ሴቶች ብቻ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ሴቶች በቀጣይ በየትኞቹም የጤና አገልግሎት መስኮች ላይ በብቃት መፈጸም እንደሚችሉ ለማበረታታት ነው፡፡ ሴቶች ብቻ ከሚሳተፉበት የህክምና አገልግሎት ጎን ለጎን የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የደም ልገሳ በማዕከሉ በህክምና ባለሙያዎችና ሠራተኞች መደረጉንም ጠቅሰው፤ ይህም የተደረገበት ዋነኛ አላማ በማዕከሉ የድንገተኛ ክፍል ደም በየጊዜው ስለሚያስፈልግ የህክምና ባለሙያው ደም በመስጠት ሌላውም ህብረተሰብ እንዲለግስ ለማስተማር ነው፡፡ በቀጣይም የተለያዩ በአላት ታስበው የሚውሉ ቀናትን በመጠቀም እንዲህ ዓይነቱን መልካም ጅምር ለማስቀጥል ማዕከሉ ይሰራል፡፡

ዜና ሐተታ
አስናቀ ፀጋዬ

 

 

 

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።