የስርዓተ-ፆታ እኩልነት መሰናክል የሆኑት ማህበራዊ ተለምዶዎች Featured

ማህበራዊ ተለምዶዎች የአንድ ሕብረተሰብ መገለጫ ባህሪያት መሆናቸውንና የአሳሪነት ኃይል እንዳላቸው የስርዓተ ፆታ እኩልነት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ተለምዶዎች የፆታዊ ጥቃትና፣ የስርዓተ - ፆታ እኩልነት አለማደግ ምክንያት መሆናቸውንም ያስገነዝባሉ።
የሕግ ባለሙያና የሴቶች መብት ተሟጋች ብሌን ሳህሉ እንደምትለው፤ ማሕበራዊ ተለምዶዎች በአንድ ሕብረተሰብ አነጋገር፣ አኗኗር፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ታትመው በሚወጡ ጽሑፎችና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጭምር ይንጸባረቃሉ፡፡ ሰዎች የሚኖሩበትን መንገድ የሚገልፁ የባህል አካል በመሆናቸው ባህሪን የመቅረጽ ኃይል አላቸው፡፡ ተለምዶዎቹ የሴቶች እኩልነት ማነቆም ናቸው፡፡
«የወንድነትና የሴትነት መለኪያ ብለን ያስቀመጥናቸው ሚዛናቸው የተዛባ ተለምዶዎች አሉን። እነዚህ ተለምዶዎች የሴቶች እኩልነትን ዕድገት የሚገቱ እንዲሁም የፆታዊ ጥቃት ምቹ ሁኔታዎች ናቸው›› ስትል የሕግ ባለሙያዋ ታመለክታለች።
እንደ እርሷ ገለጻ፤ ማህበራዊ ተለምዶ ወንድና ሴት እኩል አይደሉም የሚል አመለካከት በኀብረተሰቡ እንዲሰርፅ ምክንያት ሆኗል። የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችም ወንዶች ሴት ልጆች ላይ ጉልበት አለን ብለው የማመናቸው ውጤት ናቸው። ሴቶች ራሳቸውን እንዳይከላከሉ፣ እንዲፈሩ፣ ትምህርት እንዳያገኙና ተለምዶውን አምነው እንዲቀበሉ ይገደዳሉ። መሰል የሴቶች አቅምና ሚና ከወንዶች የሚያሳንሱ አስተሳሰቦች እንደ ሕግ ኃይል ያገኙት ማሕበራዊ ተለምዶ በመሆናቸው ነው። በዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጭምር አብዛኛውን ጊዜ ወንድ ጥቃት አድራሽ ሴት ደግሞ ተጎጂ እንድትሆን አድርጓል።
«ሴት ልጅ ፆታዊ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ ምን ለብሳ ነበር? በዛ ሰዓት ማን ውጪ አላት፤ ለምንስ እንዲህ አደረገች? በማለት እሷ ላይ ነው ጣታችንን የምንቀስረው» የምትለው ባለሙያዋ፤ «ጥቃት አድራሾቹን ለማረቅ እንደማንችል ወስነን ተቀምጠናል፤ እናም እንደ ሕብረተሰብ የመሸነፍ ስሜት ውስጥ ገብተናል» ትላለች።
‹‹ወንዶች በተፈጥሯቸው ጥቃት ፈፃሚ ናቸው›› የሚል እምነት እንደሌላት ይልቁን ኀብረተሰቡ ወንዶችን የሚያስተምርበት መንገድ እና ጥቃት ሲያደርሱ እንደ ትክክል መቆጠሩ የችግሩ መንስኤ እንደሆነ ትጠቁማለች። «እንደ ሕብረተሰብ ወንዶች በሴቶች ላይ ለሚያደርሱት ፆታዊ ጥቃት ተጠያቂነት ስለማናስተምራቸው በጥቃት አድራሽነታቸው እንዲቀጥሉ መንስኤ ሆኗል» የሚል አስተያየትም ትሰጣለች።
የሴታዊት የጾታ እኩልነት እንቅስቃሴ መስራች አባል ዶክተር ስሂን ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማሕበራዊ ተለምዶ በትምህርት ሳይሆን በመኖር ብቻ የሚታወቁ ልማዶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከባህል አንደኛውና ትልቁ አካል ነው፡፡ በቋንቋ የሚቀረፅም ነው፡፡
ዶክተሯ‹‹ ሰዎች የሚጠቀሟቸው ቃላትና በአንድ ማሕበረሰብ ለሴቶችና ለወንዶች ተለይቶ የሚሠጣቸው ሚና በሙሉ በማሕበራዊ ተለምዶ ይካተታል›› ይላሉ፡፡ ሰው ሰራሽ የስርዓተ ፆታ ኢ-ፍትሐዊነትም ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በመሆኑም ለፆታዊ ጥቃት መብዛት ድርሻቸው የጎላ ነው ይላሉ፡፡
«የስርዓተ - ፆታ ለውጥ ማምጣት ሲቻል የወንድና የሴት ግንኙነት በእኩልነት የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ እኩልነት ያለው ግንኙነት አለ ማለት አይቻልም» በማለት የሚናገሩት ዶክተር ስሂን፤ ከቤት ውጭ ሥራ፣ መሪነትና አስተዳዳሪነት ለወንዶች የሚሰጥ ሚና መሆኑ የዚህ አንድ ማሳያ በማድረግም ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ ዶክተር ስሂን ማብራሪያ፤ በተለይ በገጠር ሴት ልጆች የወንዶችን ያህል የመማር ዕድል አያገኙም።በገንዘብ ሲታይም በኢኮኖሚ የጠነከሩ ወንዶች ናቸው። ግማሽ ያህል የአገሪቱ አዋቂ ሴቶች ሥራ መስራት ቢችሉም፤ ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን የሚሰሩት ቤት ውስጥ ነው፤ይህም ሴቶችን የኢኮኖሚ ጥገኛ መሆናቸውን ያመላክታል።
«ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር የመሪነት ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥ የወንዶች ቦታ ነው» ሲሉ ጠቅሰው፤ ጥቂት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሴቶች መመራታቸው፣ ካሉት የግል ባንኮች ውስጥ በሴት የሚመራ ባንክ አለመኖሩ፣ በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የፕሬዚዳንትነት ቦታ በወንዶች መያዛቸውን ለአብነት በመጥቀስ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
የስርዓተ-ፆታ መዛባት፣ፆታዊ ጥቃትና ከዕድሜ በታች ሴት ልጆችን መዳር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚያጋጥሙ አይደሉም፤ በዚህም የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ዓለም-አቀፋዊ ጥረትን ይሻል ትላለች። የሴቶች ቀንን ከማክበር ባሻገር እና ከሚደረጉ ጥረቶች በተጨማሪ ለወንድና ለሴት የሚሠጠውን ሚና መፈተሽና መለወጥ እንደሚገባም ይጠቁማሉ። የስርዓተ-ፆታ እኩልነት መረጋገጥ የጥቂት ሰዎች የቤት ሥራ አለመሆኑን በማስገንዘብም ሁሉም የሕብረተሰብ አካል ሥራ መሆኑን ያመለክታሉ። በተለይ ወላጆችና መምህራን በስርዓተ-ፆታ ረገድ የልጆችና የተማሪዎችን አስተሳሰብ በመቅረፅ ከሌላው የበለጠ ሚና እንዳላቸውም ያስገነዝባሉ፡፡
የሕግ ባለሙያዋ ብሌን በበኩሏ፤የስርዓተ-ፆታ ኢ-ፍትሓዊነትና ፆታዊ ጥቃቶች አሁን ካለው የሰፋ እንዲሁም የተደራጀ ምላሽ ያስፈልገዋል ባይ ነች።
ማንኛውም ሥራ ሀብት ይፈልጋል፤የስርዓተ-ፆታ ማስፈንና ፆታዊ-ጥቃት ቅነሳ ተግባራትም ረጅም ጊዜ፣ጉልበትና ገንዘብ ይፈልጋሉ፡፡አሁን ያሉት የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅቶችም በመላ አገሪቱ ተደራሽ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ፣ በጉዳዩ አመላካች ጥናቶች እንዲሠሩና እንዲሁም ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ሃብት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናም ድርጅቶቹን መደገፍ አንዱ የመፍትሔ አካል ነው።

ዜና ሐተታ
በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።