የመሬት አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መሻሻሉ ተጠቆመ Featured

አዲስ አበባ፡- ቀድሞ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭነትና የተገልጋዮች መጉላላት ይስተዋልበት የነበረው የመሬት አስተዳደር ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መሻሻል ማሳየቱን ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡
በዘርፉ የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምን ያህል ለውጥ አመጣ? ሲል አዲስ ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል ዘርፉ ሰፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ነበረበት፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት አመርቂ ነው ባይባልም መሻሻል አሳይቷል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ያገኘናቸው አቶ ወርቄ ቸርነት፣ ቀደም ሲል አገልግሎት ለማግኘት ለስድስት ጊዜያት ያህል እንደተመላለሱ አስታውሰው፤ ይህ አሰራር አሁን ላይ ለውጥ ማሳየቱን ገለጸዋል፡፡ ጉዳያቸውም ያለምንም እንግልት እንደተፈጸመላቸው ተናግረ ዋል፡፡ ይህም በቅርብ ጊዜያት መንግስት ራሱን እንደፈተሸ ማሳያው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለውጥ እንደሚመጣ ያስቀመጠው አቅጣጫ ለተገኘው ለውጥ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ወርቄ ገለፃ፤ መንግሥት ችግሮችን ለማቃለል እየወሰደ ያለውን እርምጃ መነሻ በማድረግ በክፍለ ከተማው እየተፈጠረ ያለው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ችግሮችን እያቃለለ ነው፡፡ በመሆኑም የተጀመረው አሳታፊነትና ግልፅነት የተሞላበት አሠራር ቀጣይነት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ አሁን ችግሮችን እየለዩ በሚወሰዱ እርምጃዎች የታየው ለውጥ የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ አሁንም የመሬት ጉዳይ በባህሪው እጅግ ውስብስብና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ በመሆኑ ትኩረት ሊነፈገው አይገባም፡፡
በክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግደይ ዓለምሰገድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአሰራር የተገኙ ለውጦች ቢኖሩም በዘርፉ ላይ የሚስተዋለው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ሙሉ በሙሉ ተቃሏል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ተገልጋዩ ፈጣን አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር በመዘርጋቱ የችግሩን ምንጭ ለመድፈን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አግዞታል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ተገልጋዮች ጉዳያቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልፅ እንዲያውቁ መጨናነቅን በመቀነስ ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖርም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በጽህፈት ቤቱ መጀመሩ ለለውጡ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ በቀጣይም በአሁኑ ወቅት የመጣውን ለውጥ በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ትግሉን ማገዝ አለበት፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።