ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ለደመቀ ኢትዮጵያዊነት Featured

በኢትዮጵያ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ጠባብ ብሔርተኝነት እየገነነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በመሆኑም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የገነባች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስና ስትራቴጂ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ ፀሐዬ እንደሚናገሩት፤ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቁ ጉዳይ ብሔር የሚበየንበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም ግለሰብ ላይ የተመሰረተ እኩልነት፣ ነጻነትና አንድነት በሚል ሲሆን፤ በሦስተኛው ዓለምና እንደሩሲያ ያሉት ደግሞ የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና መልክዓ ምድር ያላቸው መሆኑን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ብዝሃነትን የተቀበለና ያከበረ የኢትዮጵያዊነት ግንባታ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚም አሁን ያለችውና ብዝሃነት ጎልቶ የሚታይባት ኢትዮጵያ ተፈጥራለች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው፣ እንደሚናገሩት፤ ኢህአዴግ ሲመጣ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ የብሔር እኩልነትን ማረጋገጥ፤ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ ሆኖም አካሄዱ መልኩን በመሳቱ ክልሎች በአንድ አገር የሚኖሩ አልመስል ብለዋል፡፡ ክልሎች ራሳቸውን እንደ አገር የሚተያዩበት፣ እንደ ሁለት አገርም መሬትና ህዝብ የሚቀራመቱበት ሂደትም ተፈጥሯል፡፡
ይህ የተሳሳተ ብሔርተኝነት ነው፤ አካሄዱም ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ የህዝቦች አመለካከትን ጨምሮ በጥበት፣ ትምክህት፣ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂና ሌላም በማለት በተለያየ መልኩ እየፈረጁ መሄድ በምንም መልኩ ዴሞክራሲያዊ ባህሪና መገለጫ የሌለው ብሔርተኝነት ነው፡፡ አካሄዱም በህዝቦች መካከል ከአንድነት ይልቅ መለያየትና መራራቅን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ብሔርተኝነቱ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን፤ አንዱ ብሔር የሌላውን ማንነት ሊያከብርና እውቅና ሊሰጥ ያስፈልገዋል፡፡ የብሔር ማንነት እያደገና እየጠነከረ መሄዱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፤ ብሔርተኝነቱ ግን ዴሞክራሲያዊ ከሆነ፤ ብሔር ብሔረሰቦች በወንድማማችነት እየተያዩ ለመኖር፣ ቀደም ሲል የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረምና አንድነትንም ለመጠበቅ ያስችላል፡፡

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በኢትዮጵያ ችግር የሚሆነው የብሔርተኝነት መኖር ሳይሆን፤ ይሄንን የማስተዳደሩ ሂደት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የማንነት አስተዳደር ሂደቱ አንድም ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት እንዲፈጠር የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የጋራ ባህልና ታሪክን በአንድ ላይ በማምጣት፣ በሂደት እየተቀበሉ፣ በኢኮኖሚ ሽግግርም እያጠናከሩ በመሄድ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊነት ባለው ብዝሃነት መለካት፤ ብዝሃነትን የተቀበለ ብሔርተኝነትንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚተዳደርበት ሂደት መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ የተገነባው ብሔራዊ ማንነት በየቦታው ተበታትኖ ያለ፤ ወደ ማዕከል መምጣት ያልቻለ ነው፡፡ ሆኖም ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መልኩ ማስተዳደር ሲቻል ይህ ተበታትኖ ያለ ማንነት በኢኮኖሚ ትስስርም ሆነ በጋራ እሴት ግንባታዎች ወደ ማዕከል በማሰባሰብ የጋራ ማንነትን ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ህዝቦች ያገኙትን የህግና የፖለቲካ እውቅና ወደ ልማትና ማህበራዊ ፍትህ ለማምጣትም ያስችላል፡፡ ብሔርተኝነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትም ታላቅ መሆኑን ለመገንዘብ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ኢትዮጵያም የመጨረሻ ቅርጿን የያዘችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ የነበረው ኢትዮጵያዊነትን የመፍጠር ሥራ ስለነበር የተለያየ ቋንቋና አስተዳደር ያላቸው ሰዎች ወደ አንድ የመጡበት መሆኑን ነው ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሂደት ግን የታዩ ሁለት እውነታዎች አሉ፡፡ አንዱ እስከ 1960ዎቹ የተማሪዎች አመፅ ድረስ የነበረው ኢትዮጵያዊነት በአንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ማንነት እንዲገለጽ የተደረገበት ሲሆን፤ ዘመናትን ቢዘልቅም ብዝሃነትን ያላከበረና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የማይወክል በመሆኑ ተቀባይነት ሳያገኝ ተቀልብሷል፡፡ ይሄም ብዝሃነትን የተቀበለ ኢትዮጵያዊነትን ወደመገንባት እንዲኬድም ምክንያት ሆኗል፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለጋራ አገር ግንባታ ሂደት አስተዋጽዖ እንዲኖረው ካስፈለገ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ለራሱ የሚሰጠውን ትርጉምና ግምት ያክል ለሌላውም ማሳየት አለበት፡፡ አሁን የማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ የሚታዩ ጥቂት ግለሰቦች ከአንዱ ብሔር ተገን በመያዝ ሌላው ብሔር ላይ ስድብና ማጥላላት የመሰንዘር አዝማሚያዎች በጊዜ ሀይ ካልተባሉ ወደህዝቡ ሊወርዱና ህዝቡም ስሜቱን ሊጋራ የማይችልበት፣ ቁርሾም የማይፈጥርበት ዕድል አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያም ሌሎች አገራት ላይ የደረሰው ችግር አይደርስባትም፣ ወደቀውስና መበታተን አትሄድም ማለት አይቻልም፡፡
በዶክተር ሲሳይ ሃሳብ የሚስማሙት ረዳት ፕሮፌሰር መረሣ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁንም ብሔርተኝነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተዳደር ካልተቻለ፣ የህዝብ ጥያቄዎች ይበረክታሉ፤ መንግሥትም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይከብደዋል፡፡ ይህ ሲሆን ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ይደበቃሉ፤ ጽንፍ የወጡ የብሄርተኝነት አስተሳሰቦች ይወለዳሉ፤ የመገንጠል ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ አገርን የመበተን አዝማሚያዎችም ይመጣሉ፡፡

ዜና ትንታኔ

ወንድወሰን ሽመልስ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።