የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሥራ ላይ አደጋ Featured

 

ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፊት ለፊት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ፐሬስ ድርጀት መዝናኛ ክበብ ቁርስ አዘናል፡፡ቁርሱ እስከሚደርስ እንደወትሮው ጨዋታችንን ቀጥለናል፡፡
ከፊት ለፊታችን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የሚያስገነባው አዲስ ህንፃ የግንባታ ባለሙያዎችም የዘወትር ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ይታያሉ። በዚህ የሥራ ውጥረት ትዕይንት ላይ ድንገት አንድ ግኡዝ አካል በግምት ከስድስተኛ ፎቅ እየተምዘገዘገ ወረደ፡፡ ያረፈበት አካባቢ አቧራ ተቀሰቀሰ፡፡ ወዲያው ጩኸት ተሰማ። ሁሉም ይህ ግኡዝ አካል ወደ ወደቀበት ስፍራ በረረ፡፡ ከየአቅጣጫው ሰዎች ወደ ሥፍራው በተጠጉ ቁጥር ጩኸቱ እየበረከተና እየመረረ መጣ፡፡
እኔና ጓደኛዬም ግራና ቀኝ ሳንመለከት መኪና መንገዱን አቋርጠን በድርጅቱ አጥር ላይ ሆነን እየተመለከትን የሆነውን ሁሉ ለማረጋገጥ ሞከርን። የተመለከትነውን ማመን አቃተን። አንድ ሰው መሬት ተዘርሯል። ከሠራተኞቹ አንዱ ስለመሆኑ በቀላሉ ይታወቃል። ሁኔታው በእጅጉ ልብ ይነካል፡፡ አምቡላንስ ቀርቦም ተጎጂውን ይዞ በረረ ፡፡
ክስተቱን በሚመለከት በወቅቱ በቅርበት ከነበሩት ውጪ መላ ምት ከመስጠት በዘለለ እውነቱን መናገር የሚችል አልነበረም ። አብዛኞቹ ግን ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለ አንሸራቶት እንደወደቀ ተናገሩ። ወዲያው ግን ህይወቱ የማለፉ ዜና ተሰማ፡፡ለሦስት ቀናትም አንድም ሠራተኛ በግንባታው ላይ አልታየም፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ለሠራተኞች ደህንነት ጥንቃቄ ካለመደረጉ ጋር በተያያዘ በዓለም በየዓመቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።
በኢትዮጵያም በተለይ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በዚህ ችግር ስሙ ይነሳል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለስልጣን የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤በግንባታ ወቅት በ 2008 ዓ.ም 8 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፤ 24 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም በ53 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል። በ 2010 ዓ.ም እስከ ቅርብ ጊዜ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ 1 የሞትና 14 ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል ።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ብርሃኑ ድሪባ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያለው የሙያ ደህንነት አጠባበቅ ደረጃ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው ይላሉ። በተለይም የአሰሪዎች (ኮንትራክተሮች) በመንግሥት የወጡ መመሪያዎችን ተፈጻሚ ያለማድረግ ደግሞ ለችግሩ መስፋፋት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ብርሃኑ በቅርቡ በባህርዳር ከተማ በህንጻ ግንባታ ላይ የነበሩ 20 ሰዎች መወጣጫው በመደርመሱ ህይወታቸውን ማጣታቸውን በመጥቀስም የጉዳዩን አሳሳቢነት ያመለክታሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንና ተቆጣጣሪ አካላም እንደሌለ ነው» ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፍ አደጋ ሰለባዎች አምራች ወጣቶች መሆናቸውን በመጥቀስም እነርሱን ማጣት በቤተሰብ ፣በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ፣ከአደጋው የተረፉትንም ለማሳከም በርካታ የአገር ሀብት ወጪ እንደሚደረግ ሌሎች ወገኖችን ማገልገል የሚችሉ የሆስፒታል አልጋዎች በእነዚህ ወገኖች እንደሚያዙ በመጠቆም አሳሳቢነቱን ያመለክታሉ ፡፡ ይህም የአገርን የማደግ ተስፋ ያቀጭጨዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አበባ እሸቴ የአቶ ብርሃኑን ሃሳብ ተጋርተው፣ ለአደጋው መከሰት ዋናው ምክንያት አሰሪው የጥንቃቄ መሳሪያዎችን አለማቅረቡ መሆኑን ያስረዳሉ።
አሰሪው ሠራተኛ ቀጥሮ ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት የጥንቃቄ ቁሳቁስን ማሟላት አለበት የሚል ህግ አለ የሚሉት ወይዘር አበባ፣ይህ ግን ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም ይላሉ፡፡ ሠራተኞችም ሥራውን ለምደነዋል በሚል ቁሳቁስ ሲቀረብላቸው «ምንም አልሆንም» በሚል እንደማይጠቀሙም ይጠቁማሉ፡፡
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትር ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ገብሩ እንደሚሉት ደህንነትን እንደ ሥራቸው አካል ቆጥረው በማያሰሩ አሰሪዎች ምክንያት የሚጠፋው የሰው ህይወት እና የሚወድመው ንብረት እየጨመረ መሆኑን ይጠቅሱና ፣ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደህንነትን ባለመጠበቅ ብቻ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እስከ 4 በመቶ እንደሚወድም ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ይጠቁማሉ ፡፡ አቶ ፍቃዱ የወይዘሮ አበባን ሃሳብ በማጠናከር የኮንስትራክሽን ዘርፉ ጥራት ያላቸውን የግንባታ ግብዓቶች ተጠቅሞ ደረጃውን በጠበቀና ህግ በሚፈቅደው መሰረት መወጣጫዎቹን ከብረት አዘጋጅቶ ሌሎች ለደህንነት የሚረዱ የጥንቃቄ አልባሳትን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ባለመገባቱ በሚደርሰው አደጋ አሰሪው ብቻ በዓመት የገቢውን 4 በመቶ ያጣል ወይም ኪሳራ ይገጥመዋል ይላሉ። ይህ ኪሳራ በደረሰው አደጋ ልክ የሚያሳክመውንና የሚክሰውን እንደማ ይጨምር ጠቅሰው፣ይህ ሁሉ ወጪ ሲደመር ኪሳራው ድርብ ድርብርብ መሆኑን ያመለክታሉ።
አቶ ፍቃዱ አደጋውን ዜሮ ማድረስ ባይቻልም የተለያዩ የግንዛቤና የቁጥጥር ሥራዎችን በመስራት መጠኑን መቀነስ ግን ይቻላል ይላሉ።
የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህዝብ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ደርቤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ በዋናነት ትኩረቱን በደህንነትና ጤንነት ላይ ያደረገ አዋጅ ቁጥር 724/2001 መኖሩን ይጠቅሳ ፡፡
« አሁን የከፋ የአካል መጉደል የህይወት መጥፋት እያየንና እየሰማን ነው፤ የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ የዚህ ችግር ዋና መንስኤ የአስፈጻሚው የቁጥጥርና የክትትል ማነስ፣ ህጎቹን ተግባራዊ የማድረግ ውስንነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሎች ጋር በየስድስት ወሩ በመገናኘት ይወያያል፤ በሌላ በኩልም አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ምክር ቤት ዘንድሮ በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት እየሰራም ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር፣ ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የግንባታ ግብዓቶች መጠቀምም ሌላው የሥራ ላይ አደጋ እንዲጨምር ያደረገ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ በግንባታ ላይ ያሉና የተጠናቀቁ ህንጻዎች እንደሚፈርሱና በሠራተኛው ላይ ጉዳትና ሞት እንደሚያስከትሉም ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ታደለ ማብራሪያ፤የሙያ ደህንነትና ጤንነት መጠበቅ ፋይዳው ብዙ እንደመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ ለማኖር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፤ ስልጠናዎችን በመስጠት ግንዛቤን በማሳደግ አደጋዎቹ እንዲቀንሱ ማድረግ ካልተቻለ አደጋው አምራቹን ኃይል መግደሉን አካል ማጉደሉን ይቀጥላል፤ አምስት ስድስት ሰዎች የሞቱበት ኮንትራክተር ሰርቶ ተወዳዳሪ መሆን አይችልም፤የተጠያቂነትም ጉዳይ አለበት፤ የአገርም ኢኮኖሚ በዛው ልክ ጫና ላይ ይወድቃል።
የእንጨት መወጣጫ የአደጋ ተጋላጭነቱ እንደሚሰፋ ያመለክታሉ። መወጣጫው በብረት የመለወጥ፣ ከዚህ አልፎም ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አስፈላጊነትን አቶ ታደለ ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ብርሃኑ «ችግሩ በዚሁ ይቀጥላል የሚል እምነት የለኝም በማለት መፍትሄውን ይጠቁማሉ፡፡ የግንዛቤ ሥራው ተጠናክሮ ከተካሄደ ችግሩን ዜሮ ማድረግ ባይቻል እንኳን እየቀነሰ እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል ይላሉ፣አሰሪው ሠራተኞችን ወደ ሥራ ከማስገባቱ በፊት ለግንባታ ሥራ የሚያስፈልጉ የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስን ማሟላት፣ ሠራተኛውም ቁሳቁሱ ባልተሟሉበት ሁኔታ አልሰራም ማለት ሲሟሉም በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ያስገነዝባሉ። 

ዜና ሀተታ
እፀገነት አክሊሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።