አለመናበብና የጋራ ትርጓሜ አለመያዝ ከቱሪዝም ለሚገኘው ጥቅም እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ:- የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለቱሪዝም ዘርፍ ተመሳሳይ ትርጉም አለመያዛቸውና አለመናበባቸው አገሪቱና ዜጎች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ። 

በክልልና በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት መካከል በቱሪዝም ዘርፍ ያለመናበብና የጋራ ትርጓሜ የመስጠት ችግር መኖሩ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታጣ ማድረጉን የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበራትና ባለድርሻ አካላት ገልጸዋል፡፡
ማህበራቱ በዘርፉ በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ሲወያዩ እንደገለፁት፤ መንግሥት ለአስጎብኚዎች ከቀረጽ ነፃ ተሽከርካሪ እንዲያስገቡ ቢፈቅድም ተሽከርካሪዎቹ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉበት አግባብ ላይ የጋራ ትርጓሜ ባለመሰጡት ለሥራ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ንግድ ባንክ ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት ህንፃ ካልተገነባ ብድር ስለማይሰጥ የመዳረሻ ቦታዎችን ለማልማት አልተቻለም ብለዋል፡፡ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎቶች ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ አጥጋቢ ባለመሆናቸው ለሥራው እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ወጥ የሆነ አሰራር ስለሌላቸው ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፉ ከህጋዊነት ይልቅ ህግ ወጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ማህበራቱ ጠቁመው፣ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ ከውጭ አገር ጎብኚዎችን ይዞ በመምጣት ያለምንም ከልካይ አስጎብኝቶ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡ በዚህም አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እያጣች ነው ተብሏል፡፡ በዘርፉ ሊፈጠር የሚችለው የሥራ ዕድል ለውጭ ዜጎች እየተሰጠ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ማዕዛ ሀይሉ፤ ችግሮችን ለመፍታት ተመሳሳይ ትርጓሚ ለመስጠት ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና ከሌሎቹ ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረ ዋል፡፡ ያለመናበብ ችግርን ለመፍታ ትና ወጥ አሰራር ለመዘርጋት ጥናት ተካሂዶ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመን ግሥት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ጥናት ላይ ውይይት በማድረግና የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ቶሎ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ የሚታዩ የአሰራር ግድፈቶች እና የህግ ክፍተቶች እንዲታ ረሙም አሳስበዋል።

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።