ምክር ቤቱ የ702 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጸደቀ

አዲስ አበባ ᎓- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም የልማት ማህበር ጋር ያደረገውን የ702 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጸደቀ።

ምክር ቤት 24 ኛውን መደበኛ ጉባዔውን ትናንት ሲያካሂድ፤ ለኤሌክትሪፊኬሽን እና ለከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የተደረገውን የብድር ስምምነት መርምሮ አፅድቋል፡፡ ከጸደቀው የ702 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ውስጥ 327 ሚሊዮን ዶላር ለከተሞች የተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም፤ ቀሪው 375 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም እንደሚውል ተመልክቷል፡፡
ከብድር ስምምነቱ በተጨማሪ የዓለም ባንክ 273 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ የተለገሰ ሲሆን፤ ይህም ለኤሌክትሪፊኬሽን ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡ በብድርና በልገሳ ለኤሌክትሪክ ማስፋፊያ የተገኘው ገንዘብ ፕሮግራሙን ተግባራዊ በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም የልማት ማህበር ጋር ለሁለቱ ፕሮጀክቶች ያገኘው ብድር ስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ የክፍያው ሥርዓት ከወለድ ነጻ እንደሚፈፀምም ታውቋል።
የከተሞች የተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም፤ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሙ ደግሞ እ.ኤ.አ ማርች 20 ቀን 2018 የተፈረመ ነው።

ዳንኤል ዘነበ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።