የራዕይ ቀበኛው

 የብዙዎችን ተስፋ ያጨለመ፤ ሩቅ ዓላሚዎችን በቅርብ ያሳደረ፡፡ ጠዋት ቤተሰባቸውን ተሰናብተው ማታ ሊገናኙ በተስፋ የተለያዩትን በወጡበት ያስቀረ፡፡ አረጋውያንን ያለጧሪና ቀባሪ፤ ህፃናትን ያለአሳዳጊና ተንከባካቢ ያስቀረ መጥፎ ክስተት፡፡ ከዕውቀት ገበያ የሸመቱትን በተግባር መንዝረው ራሳቸውን ሊለውጡ፣ ቤተሰባቸውን ሊረዱ፣ አገርን ሊጠቅሙና ህዝብን ሊያገለግሉ የተዘጋጁ ዕጩ ምሩቃንን ጋወን ወደ ማቅ ልብስ የቀየረ ነው-የትራፊክ አደጋ፡፡  የትራፊክ አደጋ ህፃን አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ደሃ ሀብታም፣ የተማረ ያልተማረ፣ ሃይማኖተኛ ፖለቲከኛ ሳይል የሁሉንም ቤት አንኳኩቷል፤ እያንኳኳም ይገኛል፡፡ የብዙዎችን ራዕይ በአጭሩ ቀጭቷል፡፡ ወላጅ የአብራኩን ክፋይ ተነጥቋል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን ተቀምተዋል፡፡ በደስታ ቀናቸው እስከ ዘላለሙ ያንቀላፉ ጥንዶችም ጥቂት አይደሉም፡፡
የትራፊክ አደጋ የአገርን ኢኮኖሚ በማሽመድመ ድም አቻ አልተገኘለትም፡፡ በተለይም በማደግ ላይ ላሉና ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አገራት ችግሩ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ለለውጥ የሚደረገውን ሩጫ የኋሊት ይጎትታል፤ ዕድገትን ያቀጭጫል፡፡ በአጠቃላይ ጨካኙ ድንገቴ የአገርና የህዝብን ራዕይ በአጭሩ ቀጭቷል፡፡
ክፉው ቀን ከገጠማቸው መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ሰለሞን በልሁ፤ ከስድስት ዓመት በፊት በትራፊክ አደጋ ታናሽ ወንድሙን አጥቷል፡፡ ወንድሙ ከሱቅ ዕቃ ለመግዛት ወጥቶ ሳይመለስ የቀረበትን ያቺን አጋጣሚ ሲያስታውስ ዓይኖቹ በእንባ ይሞላሉ፡፡ መንገድ የሳተ ተሽከርካሪ በወንድሙና በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የሞት አደጋ አደረሰ፡፡ በወቅቱ አሽከርካሪው ህይወቱ ባታልፍም ከሦስት ቀን የሐኪም ቤት ቆይታ አልተሻገረችም፡፡
የእነ ሰለሞን ቤት አስከፊ ገጠመኝ የብዙዎችን ቤት ማንኳኳቱን በመጠቆም ችግሩ ከመሻሻል ይልቅ፤ መባባሱን ይገልፃል፡፡ በትራፊክ አደጋ ብዙ ሰዎች ለሞትና ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውንም ይጠቁማል፡፡ በሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የአገር ሀብትም ወድሟል፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ ለአደጋው የተለያዩ መንስዔዎች ቢዘረዘሩም ዋናው ምክንያት ግን የአሽከርካሪ ጥፋት ነው፡፡
በታክሲ አሽከርካሪነት ለስምንት ዓመት መስራቱን የሚገልፀው እስክንድር ሳምሶን፤ እየተባባሰ ለመጣው የትራፊክ አደጋ የአሽከርካሪ ጥፋት በቀዳሚነት ቢጠቀስም መንገድና እግረኞችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው ባይ ነው፡፡ አሽከርካሪው የተፈቀደለትን ፍጥነት ጠብቆና ህጉን አክብሮ በማሽከርከር ረገድ ክፍተት እንዳለበት ያምናል፡፡ መንገዶቹ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተናገድ አለመቻላቸው፣ መበላሸታቸው፣ በቂ የእግረኛ ማቋረጫዎች አለመኖሩ ተሽከርካሪና እግረኛ እየተገፋፉ ለመሄድ መገደዳቸውን ይናገራል፡፡
እግረኞች የእግረኛ ማቋረጫን ጠብቀው አለመሻገራቸው፤ በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚደፉ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ የመንገድ ላይ ንግድ፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር፣ የእግረኞች ስህተትና ሌሎች ምክንያቶች ቢጠቀሱም የአሽከርካሪዎች ስህተት ቀዳሚውን የመንስዔ ድርሻ ይወስዳል፡፡ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ በማሽከርከር እንዲሁም ጠጥተው በማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት በሚፈፅሙት ስህተት የትራፊክ አደጋ ያደርሳሉ፡፡
ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የተገኘው መረጃም ይህንኑ ዕውነታ ያረጋግጣል፡፡ ባለስልጣኑ ባደረገው ጥናት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው በአሽከርካሪዎች ስህተት ነው፡፡ አሽከርካሪዎች የሙያውን ስነ ምግባርና ህጉን አክብረው ባለማሽከርከራቸው የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትን ያደርሳሉ፡፡
በተሽከርካሪና በመንገድ ችግር የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የአሽከርካሪ ብቃት አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ለፌቦ ይናገራሉ፡፡ ዋናው የችግሩ መንስዔ የአሽከርካሪ ስህተት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም አዲስ የወጣው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ደንብ ችግሩን ለመቀነስና ለመከላከል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል ይላሉ፡፡
አዲሱ ደንብ የአሽከርካሪዎችን ዕድሜ፣ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ደንቡ አሽከርካሪዎች በየደረጃው የተቀመጠውን የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ጊዜና ልምድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚፈልጉትን መንጃ ፍቃድ ለማግኘት በየምድቡ የተቀመጠውን የመጀመሪያ ደረጃ መንጃ ፍቃድ መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀጣዩን ደረጃ ለማግኘትም ሁለት ዓመት ማሽከርከራቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ደረቅ አንድ የያዘ ደረቅ ሁለት ለማግኘት ሁለት ዓመት ማሽከርከር ይኖርበታል፡፡
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይግዛው ዳኘው፤ በ2007 ዓ.ም በ10ሺ ተሽከርካሪዎች የሚደርሰውን 65 የሞት አደጋ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ 27 ለማድረስ ግብ መቀመጡን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ አንድ ሺ895 ሰው ላይ የሞት አደጋ ደርሷል፡፡ ይህም በ10ሺ ተሽከርካሪ 51 ሰው መሞቱን እንደሚያሳይ በመጠቆም ችግሩን ለመቀነስ የሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል ብለዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም አንድ ሺ852 የነበረው በትራፊክ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት እጥፍ ሊባል በሚችል መልኩ ጨምሯል፡፡ ይሄም የችግሩ አሳሳቢነት ከፍ ማለቱን ያሳያል፡፡ የትራፊክ አደጋ የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ ችግር ነውና ለመፍትሔው ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት የትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በተመሳሳይ አደጋ ሕይወታቸው ያልፋል፡፡

ዜና ሐተታ
ዳንኤል ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።