የፌዴራሊዝም ፈተናዎች Featured

ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት የተከተለችው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ብዙ ፈተናዎች ተደቅነውባታል፡፡
ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በመተግበር ያልተማከለ አስተዳደርን ብትዘረጋም፤ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥታት መካከል ያለመመጣጠን ችግር መኖሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ይናገራሉ፡፡
ክልሎች በአዲስ መልክ ስለተቋቋሙ አንዳንዶቹ የተሻለ የተማረ የሰው ኃይልና መሰረተ ልማት ቢኖራቸውም፤ የተወሰኑት በዚህ በኩል ክፍተት አለባቸው፡፡ እነዚህ ተረስተው የቆዩ በመሆናቸው ክልልን ያህል ትልቅ ተቋም ማስተዳደር፣ ማደራጀትና የሰው ኃይል ማሟላት ይቸግራቸዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኢትዮ ሶማሌና አፋር ክልሎች ይታይ የነበረው ጉድለትም ከዚህ የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡
ሌሎቹ ክልሎች በአንጻራዊነት የተማረ የሰው ኃይል ስለነበራቸው ክልሎችን አደራጅተውና ባለሙያ ማስማራታቸው በቂ ባይባልም፤ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን መቻላቸውን ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል፡፡ ይህን የፌዴራልና የክልል መንግሥታትን አቅም ማመጣጠን የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተግዳሮት መሆኑን ያነሳሉ፡፡
የክልሎች የገንዘብ ምንጭ ውስን መሆን ሁለተኛው የሥርዓቱ ፈተና እንደሆነ ዶክተር ሲሳይ ይገልፃሉ፡፡ ክልሎች የሚያከና ውኗቸው በርካታ ሥራዎች በራሳቸው ገቢ ሳይሆን ከፌዴራል መንግሥት በሚገኝ ድጎማ ወይም ድጋፍ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ላይ በተሻለ መልኩ የራሳቸውን ገቢ ሸፍኑ የሚባሉት ክልሎች ከጠቅላላ ዓመታዊ ወጪያቸው ውስጥ 28ና 29 በመቶውን ብቻ ነው የሚሸፍኑት፡፡ ይህም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪ ከፌዴራል መንግሥት እንደሚጠብቁ ያሳያል›› ብለዋል፡፡
በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለመናበብና ተግባብቶ በመሥራት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸው ሌላው ፈተና እንደሆነ ዶክተር ሲሳይ ያስረዳሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን እጁን አስረዝሞ በክልሎች ሥልጣንና ተግባር ውስጥ እንዳይገባ የሚያርም የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲና መዋቅር የለም ይላሉ፡፡
‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ሳይገነባ የፌዴራል ሥርዓት ሥራ ላይ ማዋል አይቻልም›› የሚሉት ዶክተር ሲሳይ ክልሎች የጋራ አመራርና ራስን በራስ ማስተዳደርን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የዴሞክራሲ መርሆዎች ምሉዕ ሆነው ሥራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ሆኖም ወደ ሥልጣን የሚመጡ አካላት በውስጣቸው የዴሞክራሲ ባህል ባለመኖሩ ዴሞክራሲን በመርህ ደረጃ ቢያምኑበትም ተግባራዊ አለማድረጋቸው የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ፈተና ነው ብለዋል፡፡
አንድ አይነት ቋንቋ፣ ባህልና ተቀራራቢ የሆነ ሥነ ልቦና ያላቸው ህዝቦች ለአስተዳደራዊ አመቺነት ብለው በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ሊዋቅሩ ይችላሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ህብረ ብሄራዊ የሆነ የህዝብ ስብጥር ያላቸውና የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ያላቸው አገሮች ደግሞ እነዚህን በአግባቡ ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ የፌዴራል ሥርዓታቸውን ሊያደራጁ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የተከተለችው ህብረ ብሄራዊ መልክ ያለውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው፡፡
ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በምትከተለው ህብረ ብሄራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ክልሎች በአብዛኛው ቋንቋን፣ ባህልና መልክዓ ምድራዊ መቀራረብንም ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም በተለይ በክልሎች ወሰን አካባቢዎች የተሟላ ጥናት ተካሂዶ፣ ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተውበት፣ወደ ህዝቡ ወርዶ ውይይት ተደርጎበት፤ የህዝቦችን ሥነ ልቦናዊ ስሜትና ፈቃደኝነትና ይሁንታ አግኝቶ የተደራጀ ባለመሆኑ ለሥርዓቱ ተግዳሮት መሆኑ አልቀረም፡፡
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ በክልሎች ውስጥ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል ማቋቋም ወይም ወደ የትኛውም ክልል ሊሄዱ ከፈለጉ ሊስተናገዱ እንደሚችል ቢገለፅም፤ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወይም መሪው ፓርቲ ይህን ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በአግባቡ እየሠራበት አለመሆኑን ዶክተር ሲሳይ ይጠቁማሉ፡፡ የማንነትና የወሰን ማካለል ጥያቄዎች ሲቀርቡ ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ከመፍታት ይልቅ፤ እዚያው ለማፈን ጥረት ሲደረግና በዝምታ ለማለፍ ሲሞከር፤ ችግሮቹ እየተጠናከሩ ሄደው አመፅና ያልተገባ ግጭት ማስከተላቸውን ገልጸዋል፡፡ በትግራይ ውስጥ የተነሳው የወልቃይት ህዝብ የአማራ የማንነት ጥያቄና አማራ ክልል የተነሳው የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የአንድ ብሔር ቋንቋ ተናጋሪ ወደ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ክልል ሲሄድ እሱን እንደ ዜጋ ለመቀበል ብዙም ፈቃደኛ ያለመሆን ሁኔታ ይታያል፡፡ ክልሉን የመሰረቱት የህብረተሰብ ክፍሎች ‹ክልሉ የእኛ ነው› የሚል የባለቤትነት ስሜት ሲያጸባርቁ ይታያል፡፡ ይህም የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ፈተና መሆኑ አይቀርም›› ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ይህ አካሄድ ዜጎች በየትኛውም ሥፍራ በነጻነት ተዘዋውረው የመሥራት፣ የመኖርና የመንቀሳቀስ ህገ መንግሥታዊ መብትን ይጋፋል፡፡ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ህገ መንግሥቶችን የመሳሰሉ የክልል ህገ መንግሥታት ‹‹ይህ ክልል የእነዚህ ክልል ህዝቦች ነው›› እንደሚል አስታውሰዋል፡፡ ይህ አገላለጽ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተዋላጆች ባለቤት አይደሉም እንደማለት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ፌዴራሊዝም መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ የጋራና የራስ አስተዳደርን በማማከል ተመራጭ የሆነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት በትክክል ካልተያዘ ብዙ ፈተናዎች አሉበት ብለዋል፡፡
ሥርዓቱን በአግባቡ አለመተግበር፣ ሥራ ላይ የሚያውሉት የመንግሥትና የህብረተሰብ ክፍሎች ተዓማኒነትና ብቃት አለመኖር፣ የፌዴራል ሥርዓቱን መሬት ለማስያዝ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አለማሟላት፣ በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መንግሥታት መካከል ተናቦ አለመሥራት፣ የፌዴራሊዝምን ፅንሰ ሀሳብና አተገባበር በትክክል አለመረዳት፣ በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል ያለውን ሚዛን አለመጠበቅ፤ የፌዴራል መንግሥት አላግባብ ጣልቃ ገብነት፣ የክልል መንግሥታት የጋራ የሆነውን አስተዳደር የሚያናጉ ተግባራትን መፈጸም እና የግንዛቤ ችግሮች የፌዴራሊዝም ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የክልልና የፌዴራል ሥልጣንና ኃላፊነቶች ሚዛናቸውን ጠብቀው መሄድ ባለመቻላቸው ዩጎዝላቪያ ለረጅም ጊዜ የእርስ በእርስ ግጭት መዳረጓንና መበታተኗን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ አሀዳዊ የአስተዳደር ሥርዓትን ስትከተል ነበር፤ በዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት አልተረጋገጠም በሚል በእነ ዋለልኝ መኮንን የተመራ የተማሪዎች ንቅናቄ ተነስቷል፡፡ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በሽግግር መንግሥት ስትመራ ቆይታ፤ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የፌዴራሊዝም ሥርዓትን እውን ያደረገውን የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አፅድቃለች።
የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ፈተናዎች ከወዲሁ በብስለት ካልተፈቱ፣ ሥርዓቱ በአግባቡ ካልተተገበረ፣ ካልተያዘና ሚዛኑን ካልጠበቀ አገሪቱን ወደ ግጭት ያመራታል፡፡ አመፅና ሁከት ተከስቶ፣ ሠላምና መረጋጋት ይጠፋል፡፡ በእርስ በርስ ግጭት የዜጎች ህይወት ይጠፋል፤ ንብረት ይወድማል፡፡ የዜጎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ ይገታል፣ ኢንቨስትመንት ይዳከማል፡፡ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

ዜና ትንታኔ
ጌትነት ምህረቴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።