ድርጅቶቹን ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች Featured

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ የተወሰኑ ድርጅቶችን ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ በመንግሥት እንደሚያዝ ቀሪው ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እንደሚተላለፍ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ባለሙያዎች የተለያየ መንገድ ቢተገበር የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ካፒታሉን፣እውቀቱንና ክህሎቱን አስተባብሮ ድርጅቶቹን የመግዛት አቅም ይኖረዋል ይላሉ፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚሉት፤ አብላጫው አክሲዮን በመንግሥት ይዞታ ስር ሆኖ ከፊሉ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ይሸጣል ሲባል፤ አክሲዮኑን የሚገዙት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ ተራው ህዝብም እንደሚሆን መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ድርጅቶቹ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ እንደመሆናቸው የግሉ ዘርፍ ብቻውን የሚገዛቸው አይደሉም፡፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ድርጅቶቹን እንደተባለው በከፊል ለመግዛት እንዲቻል የአክሲዮን ገበያ መቋቋም ይኖርበታል፡፡ አገሪቱ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ባለቤት እንደመሆኗ ዜጎችን አስተባብሮ የሚዋጣው ትንንሽ ብር የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ሊውል ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ የአክሲዮን ገበያ ተቋቁሞ ቀልጣፋ በሆነ አሰራር ዜጎችን በማሳተፍ ባለሀብቱም ሆነ ሌላው ህዝብ አክሲዮን እየገዛ የድርጅቱ ባለቤት መሆን ይችላል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ሲባል አርሶ አደሩን ጨምሮ ሁሉንም ዜጋ የሚያካትት ነው፡፡ በመሆኑም ባለሀብት ሲባል ጠበብ ያለ ብያኔ ባንሰጠው መልካም ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም ሁሉም እንደየዓቅሙና ፍላጎቱ የአክሲዮን ድርሻ መግዛት ይችላል፡፡ ሰው በየቦታው ያስቀመጠውን ገንዘብ ሁሉ ቢያወጣ የሁሉም ተደማምሮ ከፍተኛ ገንዘብ መሆን ይችላል፡፡ ቀደም ሲል አማራጭ ስለሌለ ሰው በግማሹ ፎቅ ሰርቶ ግማሹን ያስቀምጠዋል፡፡ አማራጭ ከተሰጠው ግን ብዙ መስራት ይችላል፡፡ ለምሳሌ አየር መንገዱን ኢትዮጵያውን ሁሉ ሊገዙት ይችላሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን የአክሲዮን ገበያ መኖር አለበት›› ሲሉ ነው የሚያስረዱት፡፡ መንግሥት ያቀደውንና የወሰነውን ለመተግበር ደግሞ በተለይ ሽያጩን በተመለከተ ዋጋው ምን ያህል ያወጣል ለሚለው ጥናቶች እንደሚያስፈልጉም ይናገራሉ፡፡
የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ በበኩላቸው፤አትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ለግዥው መጋበዝ ካፒታልን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ለአብነት የኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎች ድርጅቶችን ለመግዛት አንድ መስፈርት ቢቀመጥና ከአንድ ሺ ብር በላይ ያለው ኢንቨስት ማድረግ ይችላል ቢባል፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስት ሊያደርጉ ነው ማለት ነው፡፡ የአገሬው ህዝብም ‹‹ይህ እኮ የኔ ንብረት ነው›› እንዲል ያደርጋል፡፡ በአንድ ሺ ብር የገዛውም ሆነ በአስር ሚሊዮን ብር የገዛው ለድርጅቱ የእኔነት መንፈስ ስለሚፈጥር በዚህ መልኩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማሳተፍ ይገባል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ እንደሚናገሩት፤ የድርጅቶችን ድርሻ ለግሉ ዘርፍ መሸጥ ያለ ነው፡፡ ሊኬድበት የሚችልና የሚገባም ነው፡፡ እዚህ ላይ ምንም አይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ናቸው፡፡ መንግሥት ማለት ደግሞ የማህበረሰቡ ቁንጮ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ውጪ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ሲሸጡ ህዝቡ የኔ ነው ይላቸዋል፡፡ ስለሆነም ስለደህንነታቸውም ሆነ ምርታማነታቸው በያገባኛል መንፈስ ከማሰቡም በተጨማሪ ድጋፍም ነው የሚሰጠው፡፡
ተንታኙ ኢትዮጵያውያን መግዛት የሚችሉት በጣም ትንሹን ድርሻ ነው ይላሉ ፡፡ ለምሳሌ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ አሴት ነው ከተባለ እና 70 በመቶውን መንግሥት ይይዛል የሚባል ከሆነ 30 በመቶውን ኢትዮጵያውያን የመግዛት አቅም አላቸው ብለው አያምኑም፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ያለው ሀብት በሙሉ ተሸጦ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ 30 ቢሊዮን ዶላር ያለው ባለሀብት ላይኖር ይችላል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ለአክሲዮን መነሻ የሚሆን ዋጋ መኖር አለበት፡፡ ለምሳሌ ትንሹ መነሻ አንድ ሚሊዮን ብር ነው ከተባለ በሼር አስር በመቶ እንኳ ቢገዛ በጣም ትልቅ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹በመሆኑም አክሲዮኑ ሊገዛ የሚችለው በጥቂት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆን በበርካታ ኢትዮጵያውያን ነው መሆን የሚችለው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፤ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እንዲሁ ቅድሚያ ይሠጣቸዋል፡፡ ከዛ በኋላ ነው ወደ ውጭ የሚወጣው የተባለው›› ይላሉ፡፡
አክሲዮኑ በአግባቡ እንዲሸጥና ውጤታማ መሆን እንዲቻል ከመንግሥት የሚጠበቀው ግልጽ የሆነ አሠራርን መከተል ነው የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ መንግሥት ራሱ እንደ ሼር ሆልደር እንጂ በብቸኝነት እንደባለቤት መሆን የለብትም፡፡ ሼሩ ከተሸጠ በኋላ የአስተዳደር ቦርዱ ከመንግሥትም ከእነሱም ስለሚቋቋም ያ አሠራርና መመሪያ ወጥቶለትና ተጠንቶ መሆን አለበት እንጂ ዝም ብሎ በግርድፍ መሆን የለበትም ይላሉ ፡፡
አቶ ካህሳይ እንደሚያብራሩት፤ አፈጻጸሙ የልማታዊ መንግሥት ባህሪያት በሚያስጠበቅ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ ሊመራ ይገባል፡፡ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቱ ተሽሎ እንዲገኝ የተመቻቸ ሁኔታን መፍጠር አለበት፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርክ ወደማኑፋክቸሪንግ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን መንግሥት ድጋፍ ማድረጉ ባለሀብቱ አቅም እንዲያገኝ ማስቻሉንና ወደኢንቨስትመንቱ እንዲሳብ ማድረጉን ይገልጻሉ ፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ መጠናከር አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አገሪቱ በምትከተለው የልማታዊ መንግሥት አካሄድ መነሻነት የአገር ውስጥ ተቋማት አቅም እስኪጠናከር የተወሰኑ ዘርፎች በመንግሥት እጅ እንዲቆዩ የሚያደርግ አቅጣጫ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በእዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት በመንግሥት ይዞታ ስር ይገኛሉ፡፡
የድርጅቶቹን ድርሻ ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ የማስተተላለፉ ሥራ ከተጠናከረ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ ያለሥራ የተከማቸ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ገብቶ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ዜጎች ስለሚበራከቱ የእኔነት ስሜት በማሳደግ ጠንካራ የሥራ ባህል ይፈጠራል፤ ድርጅቶቹም ከሌሎች አገራት የሚፎካከሩ እዲሆኑ በር ይከፍታል፡፡  

 

ዜና ትንታኔ
አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።