ድንበር ተሻጋሪ ፋይዳው Featured

ኬንያዊው ዳን ካን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የባቡር ትራንስፖርት የድህረ-ምረቃ ተማሪ ነው። «ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሰማሁት ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡» ይላል:: ግድቡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የተገነዘበው ዳን ካን .አህጉራዊ ፋይዳ እንዳለውም ይናገራል።

«ግድቡ ለምሥራቅ አፍሪካ መለወጥ የሚያበረክተው ድርሻ እንዳለ ሆኖ በተለይ አገሬ ኬንያ ኤሌክትሪክ የማግኘት ዕድሏ እንዲሰፋ ያደርጋል» ያለው ዳን ካን፣ የሁለቱ አገራት የንግድ ትስስር እየጠናከረ እንዲሄድ ግድቡ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም ይናገራል።
«የተፋሰሱ አገራት ህዝቦች የግድቡን አህጉራዊ ጠቀሜታ እንዲረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት ይገባቸዋል፤ መገናኛ ብዙኃንም ዘጋቢ ፊልሞችና ዘገባዎች መሥራት ይጠበቅባቸዋል» ይላል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የድህረ-ምረቃ ትምህርቱን በባቡር ምህንድስና እየተከታተለ የሚገኘው የውሃ ሀብት መሀንዲሱ ኡጋንዳዊው ካጁቢ ኢኖክ አባይን የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ለተፋሰሱ አገራት የውዝግብ ምክንያት ሆነው መቆየታውን ያስታውሳል፡፡ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በማህበራዊ ሚዲያ የሚመለከታቸው መረጃዎች ስለ ግድቡ የማወቅ ፍላጎት እንዳሳደሩበት ይናገራል።
«ግድቡ ሲነሳ ስለተፋሰሱ አገራት ህዝቦች በተለይም የታችኞቹ ጉዳይ ያስጨንቀኝ ነበር» ያለው ካጁቢ ኢኖክ፣ በግድቡ ምክንያት በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሱዳንን ጨምሮ በሦስቱ አገራት መካከል እየተካሄዱ የሚገኙት ውይይቶች ይፈቱታል የሚል እምነት እንዳደረበትም ያብራራል።
ኡጋንዳዊው ግድቡ የሚያመነጨውን ከፍተኛ የኃይል መጠን ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለውስጥ ፍጆታዋ ታውለዋለች ብሎ እንደማያስብ ተናግሮ፤ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም ጭምር የኃይሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እምነቱ እንዳለው ይገልጻል፡፡ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ያሉት ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ በማድረግ ተጨማሪ አህጉራዊ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁሟል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምህንድስና መምህሩ ዶክተር ይልማ ስለሺ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግድቡ የኃይል አቅርቦት አቅሟን ማሳደግ ብሎም ምጣኔ ሀብቷን ማሻሻል ትሻለች። ለሱዳንም ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይሏን ያሳድግላታል፣ የጎርፍ አደጋና ደለልም ይቀንስላቸዋል፤ በግብፅ በኩል ደግሞ የአስዋን ግድብን በደለል ከመሞላት ይታደጋል ይላሉ።
«የደለል ስጋት መቀነስ የግድቦችን ዕድሜ በ 100 ዓመት መጨመር ነው።›› የሚሉት ዶክተር ይልማ፣ ይህ ደግሞ ሌላ ግድብ ገንብቶ እንደመስጠት ይቆጠራል ይላሉ፡፡ አገራቱ ከተስማሙ ግድቡ የድርቅ ስጋታቸውንም የመቀነስ አቅም እንደሚኖረው ይጠቁማሉ።
የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፊቅ አሕመድ ነጋሽ «ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ከውጥኑ እስከ ትግበራው ያደረገቻቸው ጥንቃቄዎች ወሰን ተሻጋሪ በሆኑ ወንዞች ላይ መደረግ የሚገባቸው መሆናቸውን ይገልጸሉ፡፡ የግድቡ ግንባታ በዓለም-አቀፍ የውሃ ሕግ ላይ የተጠቀሱ ድንጋጌዎችን ሙሉ በሙሉ የተንተራሰ መሆኑንም ያመለክታሉ።
የግድቡ ግንባታ ወንዙን በመጠቀም ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ጠቅሰው፣ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ድጋፍ የተቸረው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ አገራቱ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ መኖሩንም ይገልጻሉ። ሁሉም የኃይል እጥረት ያለባቸው ከመሆኑ አንጻር ደግሞ ችግራንንም ያቃልልናል ብለው ተስፋ መጣላቸውን ያብራራሉ።
የቀድሞ የታንዛንያ የውሃ ሀብት ሚኒስትር እ.አ.አ 2015 ግድቡን ጎብኝተውት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ፊቅ አሕመድ፤ በወቅቱም «የግድቡ ስያሜ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚሆን ይልቅ ታላቁ የአፍሪካ ህዳሴ ግድብ መባል ነበረበት» በማለት ድጋፋቸውን መግለጻቸውንም ይናገራሉ።
የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ሱዳንና ግብፅ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ስጋት እንደነበራቸው የተናገሩት አቶ ፊቅ አሕመድ፤ ሱዳን በቂ መረጃ ስታገኝ ግንባታውን መደገፍ መጀመሯን በግብፅ በኩልም በጊዜ ሂደት መጠነኛ የአቋም ለውጥ እየታየ መምጣቱንም ይናገራሉ።
«ግድቡ አሁን ያለው የኢትዮጵያን ኃይል የማመንጨት አቅም በ150 በመቶ ያሳድገዋል፣ የቱሪዝም ፍሰትን ያበረታታል፣ የዓሣ ምርትንም ይጨምራል» የሚሉት አቶ ፊቅ አሕመድ፣ ቀጣናዊ ትስስርንና ትብብርን እንደሚያጎለብትም ነው ያመለከቱት፡፡ በተለይ ሱዳን በተደጋጋሚ የሚያጋጥማትን የጎርፍ አደጋ የሚያስቀር መሆኑንም ያመለክታሉ።
«የሱዳን ግድቦች አነስተኛ በመሆናቸው ለመስኖ ልማት በቂ አይደሉም ግድቡ ሲጠናቀቅ ችግሩም አብሮ ይፈታል፤ የኃይል ማመንጫ ግድቦቿም ዓመቱን ሙሉ ውሃ በመያዝ ከ 2 ሺ እስከ 3 ሺ ጊጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ያመነጫሉ» ይላሉ።
በግብፅ በኩልም በተመሳሳይ የአስዋን ግድብን የሚሞላ ደለልን በማስቀረት ዕድሜው እንዲረዝም ማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመው፣ በናይል ወንዝ ምክንያት የሚደርሰውን አደገኛ ጎርፍ በመከላከል ሊደርስ የሚችለውን የመፍረስ አደጋ እንደ ሚያስቀርም ይጠቁማሉ።

ዜና ሐተታ
በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።