‹‹የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ላላት መልካም ግንኙነት አብነት ነው›› ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ያለበትን መልካም ደረጃ ዋነኛ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሸመ አስታወቁ

ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ ለአንድ አመት ተኩል የሱዳን አምባሳደር ሆነው ሲሰሩ ከቆዩት ገማል ሼህ አህመድ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

‹‹በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ስትራቴጂካዊ እና የተረጋጋ መሆኑን በመግለጽ የሀገራቱ ግንኙነት ኢትዮጵያ በተይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት የደረሰበትን ደረጃ ዋነኛ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው›› ሲሉ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቃባይ አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል፡፡

ይህ ስትራቴጂያዊ እና የተረጋጋ  ግንኙነት ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቱ መናጋገራቸውን የገለጹት አቶ አሸብር፤ ይህንን መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል መከናወን ስላለባቸው ተግባራት ዙሪያም ውይይት አምባሳደሩ እና ፕሬዝደንቱ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር አከባቢዎች በሚደረጉ ልማቶች እና በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በየጊዜው እየተደረገ ያለው ግንኙነት ኢትዮጵያ ለጎረቤቶች ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ፤  ለጎረቤቶች ሰላምና ልማት እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ሀገራት ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ አብዛኛውን በመቀበል ሱዳን ሁለተኛዋ መሆኑዋን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ፤ በቀጣይም ከሱዳን ጋር በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለው ግንኙነት ሊሰፋ እና ሊጠናከር እንደሚገባም መናገራቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እና ለማስፋት የኢትዮጵያ መንግስት ማድረግ ያለበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት ፕሬዝደንቱ፤ አዲስ የሚሾም በኢትዮጵ የሱዳን አምባሳደርም ይህን ያከናውናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ገማል ሼህ አህመድ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው፤ ይህንን እውን ለማድረግም የተጀመሩ ግንኙነቶችን ሊያሰፋ እና ሊያጠናክር የሚችል ተግባራትን ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ትስስሮችን ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታዎች ዙሪያ ከፕሬዝደንቱ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

 

እንደ አምባሳደር ገማል ማብራሪያ፤ ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ባሻገር በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት ያደረጉ ሲሆን የተደረጉ ውይይቶችም በኢትዮጵያ እና በሱዳን የሚገኙትን የወንድማማች ህዞቦች ጥቅም ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ አንድ አመት ከተኩል ባሳለፉበት ወቅት መልካም ጊዜ ማሳለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።