በምክር ቤቱ ስብሰባዎች በአማካይ 218 አባላት አይገኙም Featured


አዲስ አበባ፦ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረጉ 78 መደበኛ፣ አስቸኳይ እና ልዩ ስብሰባዎች ላይ በአማካይ በየስብሰባው 218 አባላት እንዳልተገኙ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ልዩ ዘገባ አረጋግጧል።
የጋዜጣው ሪፖርተር የአምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛና ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመንን ቃለ ጉባኤዎችን ከመረመረ በኋላ ባገኘው መረጃ መሰረት በምክር ቤቱ ውስጥ በሁለት ዓመታት በተደረጉ መደበኛ፣ አስቸኳይ እና ልዩ ስብሰባዎች ከ547 የምክር ቤቱ አባላት መካከል በአማካኝ በየስብሰባው 218ቱ አልተገኙም።
ለዚሁ ዘገባ ሲባልም አዲስ ዘመን በሁለት ዓመት የተካሄዱ 78 ስብሰባዎችን ቃለ ጉባኤ የተመለከተ ሲሆን፤ በ68 ስብሰባዎች የተገኙት አባላት ከ350 በታች ነው። ከ350 በላይ አባላት የተገኙባቸው ስብሰባዎች 10 ብቻ ናቸው።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ላምሴ ያልቃ በሰጡት ምላሽ፤ አባላቱ የህዝባቸውንና የድርጅታቸውን ጥቅም ለማስከበር በየስብሰባዎቹ መገኘት ቢኖርባቸውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙባቸው ስብሰባዎች ከ400 በላይ አባላት የሚገኙ ሲሆን፤ በሌሎቹ ስብሰባዎች ግን ከ280 እስከ 350 አባላት ብቻ ስብሰባዎችን ይካፈላሉ።
እንደ አቶ ላምሴ ገለጻ፤ የምክር ቤቱ አባላት የማይገኙት በመንግሥትና በየድርጅቶቻቸው በክልልና በፌዴራል ደረጃ ኃላፊነት ስለተሰጣቸው፣ በሞትና በተለያየ ምክንያት ምክር ቤቱን የተለዩ አባላት በመኖራቸው ነው። አባላቱ የመስክ ምልከታ ሲኖርባቸውና በሌሎች ተያያዥ የሥራ ምክንያቶች የተነሳ በስብሰባዎቹ ላይ የማይገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡
ይህንን የቀሪ ብዛት ለመከላከል በሚል ምክር ቤቱ ትምህርት ይማሩ የነበሩ አባላትን በማነጋገር ከሚማሩበት ተቋም ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ትምህርቱን ስብሰባ በማይኖርበት ጊዜ እንዲማሩ መደረጉን አቶ ላምሴ አስታውሰዋል።
አባላቱ ለመረጣቸው ህዝብና ፓርቲ ትክክለኛ ህግ እንዲወጣ በየስብሰባዎቹ በመገኘት ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ከፍተኛ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ የወከላቸው ፓርቲም አባላቱ ሲቀሩ መከታተልና ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት ብለዋል፡፡ ከስብሰባ የሚቀሩት አባላት እንደሚታወቁ ጠቁመው፤ እስከ አሁን በመቅሩቱ ዕርምጃ የተወሰደበት አባል እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ ሁለት መሰረት የምክር ቤቱ አባላት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም በሚመለከተው አካል ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም የምክር ቤቱ ስብሰባዎች መገኘት አለባቸው፡፡
በአንቀጽ 162 ንዑስ አንቀጽ 6 የምክር ቤት አባል ያለበቂ ምክንያት ኮሦስት ተከታታይ ስብሰባዎች በላይ የቀረ እንደሆነ በሚመለከተው ኮሚቴ በሚቀርብ ሞሽን ምክር ቤቱ ከኮሚቴ አባልነት እንዲነሳ ሊወስን እንደሚችልም ያስቀምጣል። በአንቀጽ 175 ንዑስ አንቀጽ 1 የቋሚ ኮሚቴ ስነ ምግባር ዝርዝር የሥራ ስዓት ማክብር እንዳለበት ይደነግጋል። 

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።