ኢትዮ-ቴሌኮም በአክሲዮን ወደ ግል የመዛወሩ ፋይዳ Featured

መንግስት በእጁ ስር ያለውን ኢትዮ-ቴሌኮምን ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ ራሱ ይዞ ቀሪውን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች ለማስተላለፍ ወስኗል፡፡ ኩባንያው በተወሰነ የአክሲዮን ድርሻ ወደ ግል መተላለፉ ብዙ ጥቅም እንዳለው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ ወደ ግል መተላለፉ የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ይበልጥ ለማፋጠን እንደሚረዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህርና በአክሲዮን ላይ ጥናት ያካሄዱት ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጴጥሮስ ይናገራሉ፡፡ ዕውቀትና ገንዘብ ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች በዕድገቱ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ያስችላል፡፡ ብቃት ያለው የሰው ሀይል ለመገንባት፣ የተቋሙን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የሚገልፁት፡፡ የንግድ ውድድርን በመፍጠር፣ ጥራት ያለው አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጴጥሮስ እንደሚሉት፤ መንግስት ቀደም ሲል ጀምሮ መንግስታዊ ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ቢያዞርም ለመንግስት በጣም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘውን ኢትዮ- ቴሌኮምን ለማዞር ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ተቋሙን በብቸኝነት ይዞ የአገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ አይቻልም፡፡ የአሁኑ ውሳኔ ታዲያ መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተደራሽነት ላይ ውጤታማ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
ኢትዮ- ቴሌኮም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ቢያስገኝም የብር ዶላርን የመግዛት ዋጋ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ገቢው ልማቱን በሚፈለገው መልኩ ሊያግዝ አለመቻሉን ምሁሩ ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም የተቋሙ አክሲዮን መሸጥ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይረዳል፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ ተቋሙ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ጋር እኩል ለመሆን፤ ከተቻለም ለመብለጥ ለመስራት ያነሳሳዋል፡፡ በፋይናንስ፣ በእውቀት፣ በአስተዳደርና በቴክኖሎጂ አቅም ልቆ በመገኘት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ይረዳዋል፡፡ በተለይ የውጭ ባለሀብቶች ከገቡ ኩባንያው በውጭ ኩባንያዎች ደረጃ እንዲሰራ ይገደዳል፤ባለአክሲዮኖቹ ከኢትዮጵያ ውጭም ቅርንጫፍ የመክፈት ድፍረቱና አቅሙ ስለሚኖራቸው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ይጨምራል፡፡
በመንግስት እጅ ያሉት ትላልቅ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ቢዛወሩ የተሻለ ውጤት እንደሚኖር ረዳት ፕሮፌሰሩ ጠቁመው፤ ኢትዮ-ቴሌኮምም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ቢዞር የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ረገድ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያመጣ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
እነ ኬንያ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋናና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ቴሌን የመሳሰሉ ተቋማትን ወደ ግል በማዞራቸው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ችለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም አያጋጥማቸ ውም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ነጋዴዎች መድኃኒት ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወረፋ ጠብቀው ሲወስዱ፣ በኬንያ ማንኛውም ዜጋ የሚፈልገውን ያህል ዶላር በኢቲኤም ካርድ ነው የሚቀበለው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ዶክተር ገብረህይወት ተስፋይ በበኩላቸው ግዙፍና ረጅም ታሪክ ያለው ቴሌ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ማገልገሉን በማስታወስ፤ የተወሰነ ድርሻው ወደ ግል መዛወሩ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡ በተለይም በአገር ውስጥ ላሉትና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ በትርፍና በግብር የሚገኘው ከፍተኛ ገንዘብም የአገሪቱን ልማት ለማገዝ ይረዳል፡፡
በተለይም ዳያስፖራዎች ዶላርና እውቀት ይዘው ስለሚመጡ የሚያገኙትን ትርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ስለሚያደርጉበት ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ነው የሚሆነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከመፍታትና በተጨማሪ ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት በተጨማሪ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ይላሉ-ዶክተር ገብረ ህይወት፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ድርሻውን የሚገዙ ከሆነ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ስለሚገኝ መንግስት ያለበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል ይረዳዋል፡፡
‹‹ኢትዮ-ቴሌኮም በአክሲዮን ድርሻ ወደ ግል መዛወሩ ለውጤታማነት ያግዘዋል፡፡ ኩባንያው በማትረፉ የሚጠቀሙት፤ በመክሰሩ ደግሞ የሚጎዱት ባለአክሲዮኖቹ በመሆናቸው ስራውን በብቃት በመምራት፣ ሀብትን በመቆጠብና ከብክነት በማስወገድ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይሰራሉ›› የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አጥላው አለሙ ናቸው፡፡
እንደ ቴሌ ያሉ በሞኖፖል የተያዙ ድርጅቶች ካፒታላቸው ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ወጪያቸው ስለሚቀንስ፤ አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ስለሚያቀርቡ በመንግስት መያዛቸው የተሻለ እንደሆነ የሚገልፁ አካላት መኖራቸውን ዶክተር አጥላው ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህ አካሄድ የመንግስትን ስልጣን ተገን አድርገው የሚጠቀሙ ቡድኖች እጅ ላይ የሚወድቅበት ዕድሉ ስላለ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመፍጠሩም በላይ የተቋሙ ገቢ ወደ ሙሰኞች ጎተራ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡
ለምሳሌ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ለኩባንያው ለግብዓትነት የሚውሉ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ መሳሪያዎችን መርጦ በመግዛት የመጠቀም ነገር አይኖርም፡፡ ይህም በአገልግሎት ጥራቱ ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የተቋሙ አመራሮቹ በፓርቲው ጣልቃ ገብነት ስለሚሾሙ የአመራር ብቃት የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ ላጠፉት ጥፋትም አይጠየቁም፡፡ ይህም ለተቋሙ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ፈተና ይሆናል፡፡ ስለሆነም ወደ ግል መዛወሩ እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን እንደሚረዳ ነው ዶክተር አጥላው የሚናገሩት፡፡
መንግስት ቀደም ሲል እንደ ቴሌ ያሉ ትላልቅ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ የሰሞኑን የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ በአፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ግዙፍ የሆኑት ቮዳኮምና ኤምቲኤን የተባሉት ኩባንያዎች የኢትዮ- ቴሌኮምን ባለቤትነት ከፊል ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግስት እጅ ሥር የነበሩ ከ300 በላይ የልማት ድርጅቶች ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲዛወሩ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በመንግስት እጅ በሞኖፖል ከቆየ የአገር ውስጥ አንበሳ ብቻ ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ውጤታማነቱና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደርስም፡፡ የምዝበራና የመልካም አስተዳደር የችግር ምንጭ ሆኖ ይቀጥላሉ፡፡ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች እንዳይኖሩ፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋና ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ተገድቦ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

ዜና ትንታኔ
ጌትነት ምህረቴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።