ገበያውን ለማረጋጋት የሚጥሩ ማህበራት Featured

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ሮሮ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ነጋዴዎች በሸማቹ ላይ ዋጋ ጨመሩ እንጂ ቀነሱ ሲባል መስማት ብርቅ ሆኗል።በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኑሮ ውድነት የህዝቡን ወገብ አጉብጧል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መንግስት በሸማቾች ሥራ ማህበራት አማካኝነት መሰረታዊ ሸቀጦችን በሚዛናዊ ዋጋ ለማቅረብ ቢሞክርም የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም፡፡

ሸማቹ የዋጋ ንረትን ሽሽት ከሸማቾች ማህበራት ደጅ ቢጠናም ሸቀጦችን በሚፈልገው መጠንና ጊዜ አለማግኘቱ ለድካምና እንግልት ዳርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከሚታዩት የታክሲ ሰልፎች ቀጥሎ፤ በሸማች ማህበራት አካባቢ የሚታየው ሰልፍ በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀሳል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ሸማች ማህበራት ለጤናማ ግብይት መፈጠር የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው አይካድም፡፡ የህብረተሰቡን ችግር እያስታገሱ ካሉት ሸማች ማህበራት ጀርባ ገበሬውን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በሉሜ አዳማ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን ቅጥር ግቢ ውስጥ ያገኘኋቸው እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ብርሃንና መርካቶ ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይላይ ለማ ይሄንኑ እውነታ ነው ያረጋገጡልኝ። የሸማች ማህበራት ህብረተሰቡ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ነው። የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ለሸማች ማህበራቱ የዋጋ ድጎማ በማድረግ ምርቶችን ማቅረባቸው ሸማቹ ዋጋ ለመግዛት አስችሎታል ይላሉ፡፡
ብርሃንና መርካቶ ዩኒየንን ጨምሮ በአዲስ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ዩኒየኖች ከሉሜ አዳማ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የስንዴ ዱቄት፣ስንዴ ፣ጤፍ፣የቁም ከብት የመሳሰሉትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚወስዱ አቶ ኃይላይ ይገልጻሉ። «ያለፈውን የፋሲካ በዓል መሰረት በማድረግ 180 በሬዎችን በመውሰድ ለሸማቹ ስጋን በተመጣጣኝ ዋጋ ማዳረሳቸውን ለማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
የሉሜ አዳማ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብዲ በበኩላቸው ዩኒየኑ የአገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ «በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የሸማች ማህበራት ለሁሉም በሚባል ደረጃ አስር የተለያዩ የምርት አይነቶችን በማቅረብ ላይ ነን። ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አንደኛ ደረጃ ዱቄት በሳምንት አራት ጊዜ እናቀርባለን፣ ለስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ጤፍ እያቀረብን ነው» በማለት ዩኒየኑ ለገበያ መረጋጋት ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በየዓመቱም 43 ሺ ኩንታል የተለያዩ ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመረከብ ለገበያ በማቅረብ ዋጋን እያረጋጋ ነው ብለዋል፡፡
ከአርሶ አደሩ በሚረከቡት ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ አቶ ታደለ ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም በስምንት ሚሊዮን ብር የዱቄት ፋብሪካ በመገንባት በቀን ሶስት መቶ ኩንታል አንደኛ ደረጃ ስንዴ ዱቄት በማምረት ለሸማቹና ለተቋማት እያቀረቡ ይገኛል፡፡ በየዓመቱም እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያከናውናሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቀን 20 ሺ ዳቦ የማም ረት አቅም ያለው ፋብሪካ በመትከል ለሞጆና አካባ ቢዋ ገበያን የማረጋጋት ስራን እየሰራ እንደሚገኝም ነው አቶ ታደለ የገለፁት፡፡ በኢንዱስት ሪው ላይ የተሻለ ተሳትፎ ለማድረግ የማካሮኒና ፓስታ ፋብሪካ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መጣሉን ገልጸው ፤ወደ ተግባር ለመግባትም ሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡
የጨርጨር ኦዳ ቡልቱም የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ ለገሰ ዩኒየናቸው በወተት ተዋጽኦ ዘርፍ ገበያ የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ ነው ይላሉ፡፡ ዩኒየኑ የቡና ምርትን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፤ የቀንድ ከብቶች ፣የወተት ላሞች፣ የስጋና የወተት ምርቶችን ከህብረተሰቡ በተጨማሪ ለኦዳቡልቱና ለሃሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ነው የገለፁት፡፡ ዩኒየኑ የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ለጭሮና አካባቢዋ ነዋሪዎች የወተት ምርትን እያቀረበ ነው፡፡
የህብረት ስራ ማህበራት ለአባላት ከሚሰጡት ጠቀሜታ በሻገር ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ የሸማቾች የዩኒየን ማህበራ ትስስር መፍጠር የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር ህብረተሰቡ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ረድተዋል፡፡
ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የህብረት ስራ ማህበራትን አደረጃጀት በማጠናከር በተለይም መሰረታዊ ሸቀጦችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ መስራትና መደገፍ ይገባል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ 19 ሚሊዮን 464ሺ 336 አባላትን ያቀፉ 84ሺ 727 መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት፤382 የህብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ሶስት የህብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዜና ሐተታ
ዳንኤል ዘነበ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።