የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኪራይ ዋጋ ሊያሻሽል ነው • በሶስት ዓመት ከ16ሺ 200 በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅዷል

አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በ2011 በጀት ዓመት በሚያከራያቸው 18ሺ645 ቤቶች ላይ የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታወቀ። በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከ16ሺ 200 በላይ ቤቶችን እንደሚገነባም ገልጿል።

በኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን፤ የኪራይ ዋጋ ማሻሻያውን ለማድረግ የሚያስችል ጥናት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ በሚቀጥለው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከ30 ብር እስከ 1000 ብር እንደየቤቶቹ ዓይነት እያከራየ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች በዶላር የሚያከራይ ቢሆንም የኪራይ ዋጋው ካለው የገበያ ዋጋ አንጻር ፍጹም የማይጣጣም ነው ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ ገቢውን ለማሳደግ በኪራይ ላይ ማሻሻያ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ ቤቶችን በራሱ ይዞታው እና ከአዲስ አበባ መስተዳድር በትብብር በሚያገኘው መሬት ላይ ለመገንባት ማቀዱን አቶ ክብሮም ገልፀዋል፡፡
የሚገነቡትን ቤቶች ለፌዴራል መንግስት ሀላፊዎችና ሰራተኞች፣ ለአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ዲፕሎማቶች ፤እንዲሁም በህንፃው ወለል ላይ ያሉትን ቤቶች ለንግድ እንደሚያከራይ ተናግረዋል፡፡ እየጨመረ የመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያግዝም ነው የገለፁት፡፡
አቶ ክብሮም እንዳሉት፤ በ2011 በጀት ዓመት 3ሺ 200 ቤቶችን ግንባታ ለማከናወን የራሱ ይዞታ በሆኑ ስድስት ቦታዎች ላይ 12 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል፡፡ የህንፃዎቹ የዲዛይን ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ህንፃዎቹ የከተማዋን መሪ እቅድ መሰረት ተደርጎ ከዘጠኝ እስከ 21 ወለል ያላቸው ናቸው። የግንባታው ጨረታ በቅርብ ጊዜ ወጥቶ በመጪው በጀት ዓመት ወደ ስራ ይገባል። ዘጠኝ ወለል ያላቸው ህንፃዎች 22 ወራት ከፍተኛ ወለል ያላቸው ህንፃዎች ደግሞ በ30 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ።
በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከ16ሺ200 በላይ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ ግንባታዎቹን በራሱ ይዞታዎች ከማካሄድ በተጨማሪ ለግንባታ አመቺ ያልሆኑትን ትናንሽ ቦታዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀየር ለግንባታ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በመረከብ የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል። የግንባታው ወጪ በኮርፖሬሽኑና በብድር እንደሚሸፈን አስረድተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል መንግስት ቤቶችን ለማስተዳደር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፤ አጠቃላይ ሀብቱም ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።