አገራቱ የሰላምና ልማት ስምምነት ተፈራረሙ Featured

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለያዩ መስኮች አብሮ መሥራት ከሚያስችል ስምምነት ደርሰዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተለያዩ መስኮች አብሮ መሥራት ከሚያስችል ስምምነት ደርሰዋል፤

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛነት መመለስ የሚያስችል የሰላምና የልማት ስምምነት ፈፀሙ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ባካሄዱት የሁለት ቀናት ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት በሚቀጥልበት መንገድ ላይ መክረዋል።
ከውይይቱ በኋላም፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ መስኮች ተባብሮ ለመሥራት ለሰላምና ልማት ከስምምነት ደርሰዋል። አገራቱም በመካከላቸው የነበረው ጦርነት በይፋ ማብቃቱን በማስታወቅ፤ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ተባብረው ለመሥራትና በዲፕሎማሲ፣ በፀጥታ፣ በንግድ፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በቴሌኮሙዩኒኬሽን መስኮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
አገራቱ በስምምነቱ የጦርነት በርን በመዝጋት በልማት ለመተባበር፣ ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን እድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወደብ መጠቀምን ጨምሮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር የተስማሙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና አስመራ ኤምባሲዎቻቸውንም ለመክፈት ስምምነት ፈፅመዋል።
ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ አገልግሎት ለማስጀመር እንዲሁም የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች ወደ አገራቱ መደበኛ በረራ እንዲያካሂዱና የአልጀርሱም ስምምነት ሆነ የድንበር ስምምነቶች ገቢራዊ እንዲሆኑ ከመስማማት ደርሰዋል።
የሁለቱ አገራት ዳግም ግንኙነት አስመልክቶም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ፣ «በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በፍቅር ፈርሷል» ብለዋል።ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ጥሪና አጋርነትን በእጅጉ አድንቀዋል። ሁለቱ መሪዎች አገራቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን አብስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ ታሪካዊ የተባለለትን ጉብኝት በማድረግ አስመራ ሲገቡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ይታወሳል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በኤርትራ የነበራቸውን ቆይታ በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡ 

ታምራት ተስፋዬ 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።