የተዘረፉ ቅርሶቻችንን እናስመልስ

የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች በመንግሥታትና በግለሰቦች ተዘርፈው በተለያዩ አገራት ይገኛሉ። እነዚህን ቅርሶች የተደራጀ አሠራር በመዘርጋት ማስመለስ ይገባል፡፡
በቅርስ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ቅርሶቹን ለማስመለስ ያገባናል የሚሉ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ከቅርስ ጋር የሚሠሩ ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ የቅርስ ባለቤቶች እና የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በብዙ አገሮች የዚህ አይነት ሕዝባዊ ተቋማት ቅርሶችን ለማስመለስ አስችለዋል። ኢትዮጵያም ይህን መንገድ ብትከተል በመንግሥታት ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ዕጅ ያሉ ቅርሶች ለማስመለስ ያስችላል። በዚህ መልኩ ተደራጅቶ መሥራት ከታቻለ ቅርሶችን ይዘው የሚገኙ አገራትንም ሆነ ግለሰቦችን ለማሳመንና ጫና ለማድረግ ያስችላል፤ ዓለም አቅፍ ሕግና ዲፕሎማሲ ለመጠቀምም አቅም ይፈጥራል፡፡
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አብርሃም ኪሮስም የዲያቆን ዳንኤልን ሀሳብ ይጋራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ከሠሩ ቅርሶችን ለማስመለስ ይቻላል። በተለይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤምባሲዎች፣ ቆንስላዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅተው ቅርሶችን ለማስመለስ መታተር አለባቸው። የቅርስ ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በዚህ ላይ የሚሰሩ ማህበራትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ከሰሩ ቅርሶችን ለማስመለስ እንደሚቻል ይናገራሉ።
የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃ ቁጥጥርና ደረጃ ምደባ ባለሙያ አቶ አበራ ኢንጭሎ፤ የዓለም የባህል፣ የሳይንስና የትምህርት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1970 የአንድ አገር ቅርስ  ወደሌላ እንዳይወሰድና እንዳይዘዋወር ስምምንት ቢደረገም ከዚህ ስምምንት በፊት የተወሰዱ ቅርሶችን በሕግ ለማስመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ቅርሶቹን ማስመለስ የሚቻለው በዲፕሎማሲና በድርድር ብቻ ነው። ይህን ለማድረግም በመጀመሪያ በተለያዩ አገራት ያሉንን ቅርሶች ማጥናት ያስፈልጋል። እስካሁን ግን መንግሥት ይህን ለማድረግ የሰራው ሥራ የለም። በመሆኑም ከግለሰቦችና ከድርጅቶች በላይ መንግሥት ዋና ተዋናይ በመሆን ከማጥናት እስከ ማስመለስ መሥራት አለበት። ቅርስ በማስመለስ እስካሁን ምንም ያልሰሩት የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንባር ቀደም ሆነው ቅርሶቻችን ተዘርፍው ከሚገኙበት አገራት ለማስመለስ መደራደር አለባቸው። ከመንግሥት ጎንም በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ሁሉም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጫና ማድረግ አለባቸው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና የቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር ተክሌ ሀጎስ በበኩላቸው፤ ቅርሶችን ለማስመለስ ያሉበትን ቦታ መለየትና አዋጭ የሆነ የዲፕሎማሲ ስልት በመንደፍ መሠራት አለበት። የዓለም የባህል፣ የሳይንስና ትምህርት ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንም የሥራው አጋር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለማጥናትም ሆነ ለማስመለስ ሁሉም ዜጋና ድርጅቶች ባለቤትና ተዋናይ መሆን አለባቸው። መንግሥትም የአንባሳውን ድርሻ ስለሚወስድ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ነገር ግን እስካሁን አብሮ የመሥራት ችግር ስላለ በቀጣይ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።
የወጡትን ቅርሶች ማስመለስ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት የቅርስ ሽያጭ በሰፊው ይታያል የሚሉት መምህር ተክሌ ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ከመንግሥት አመራር እስክ ሕብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ነው ይላሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ፤ በአገራችን ያሉት ቅርሶች ዓለም አቅፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ አልተመዘገቡም። አገር አቅፍ የመረጃ ሥርዓት አልተዘረጋም። ይህ ባለመሆኑ ሲሰረቁ በሕግ ለማስመለስና ከአገር እንዳይወጡ ለመከላከል አልተቻለም። ቀደም ሲል ለወጡት ቅርሶች ብቻ ሳይሆን አሁን ከዕጃችን እያመለጡ ያሉትን ቅርሶቻችንንም ትኩረት መስጠት ይገባል።
ዲያቆን ዳንኤል፤ ከውጭ ያሉትን ማስመጣት ብቻ ሳይሆን ከተመለሱ በኋላ የትና እነዴት ነው የሚቀመጠው የሚለው አንገብጋቢ መሆኑን ያብራራሉ። ቅርሶችን ለማስመለስ ብቻ ሳይሆን ያሉትንና የሚመጡትም ዳግም እንዳይሰረቁ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው። አምጥተን ድጋሚ የሚወጡ ከሆነ ታጥቦ ጭቃ ነው። የቅርስ ጉዳይ የሁሉም ዜጋ በመሆኑ በማስመለስና በመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። መንግሥትም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ይላሉ።
አቶ አብርሃም በበኩላቸው እንደሚሉት፣ ቅርስ ከማስመለስ ጎን ለጎን ስለቅርስ ለህዝቡ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል። የተዘረፉብንን ቅርስ ብናመጣም ተመልስው መሄዳቸው አይቀረም። መንግሥትም ዜጎች ለቅርስ ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ ማስተማር አለበት። ለቅርሶቻችን ማስቀመጫና ማሳያ ሙዜየሞችም ለመገንባት ትኩረት መደረግ አለበት። ዜጎችንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድርግ ያስፈልጋል። ለዘራፊዎች ሸጠው ከሚያገኙት በላይ ቅርሶቹ በአገራቸው መኖሩ ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው መሥራት እንዳለበት ይመክራሉ።
አቶ አበራ በበኩላቸው በአገር ውስጥ ያለው ቅንጅት ዝቅተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ በክልሎች በትንሽ ገንዘብ ቅርሶችን አሳልፈው እየሸጡ ነው። ቅርስን ከአገር የሚያወጣ ከፍተኛ የሆነ የደላላ ሰንሰለት አለ። ተዘርፈው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እየወጡ ነው ያሉት። ይህን ማስቆም ይገባል። ቅርሶቻችን ለማስመለስ እስካሁን መንግሥትም ሆነ ዜጎች ተደራጅተው አልሰሩም። ከዚህ በኋላ መንግሥት በመደበኛነት ቅርስ የማስመለስ ሥራውን ከዜጎች ጋር በመተባበር መሥራት ይጠበቅበታል።
ከኢትዮጵያ ተዘርፍው በሌላ አገራት ያሉ ቅርሶች ከ50 በላይ በሚሆኑ አገራት እንደሚገኙና ቁጥራቸውም ከ15ሺ በላይ እንደሚሆኑ ዲያቆን ዳንኤል ይጠቅሳሉ። አቶ አብርሃም ኪሮስ በበኩላቸው የተዘረፉ ቅርሶቻችን ከ30 እስከ 40ሺ እንደሚደርሱ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርሶች በተለያዩ አገራት መገኘታቸው ገሃድ ነው። እነዚህ ቅርሶች የሳይንስ፣ የዕምነት፣ የፖለቲካ፣ የጦርነት፣ የኪነጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የህክምና ሌሎች መገለጫዎቻችን ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ቅርሶች በሚፈለገው መጠን ካለተመለሱ አገራችን በቀጣይ በተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ተገቢውን መረጃ እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡ የቀደመውን ታሪካችንንም ቀስ በቀስ እንድናጣ በማድረግ ታሪኮቻችን እየተረሱ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡

ዜና ትንታኔ
አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።