የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 100 ቀናት Featured

የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመቶ ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መንበረ ሥልጣኑን ተረከቡ። በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ዘልቀው ገቡ። “ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነትና ይቅርታ” የሚሉት መልዕክቶቻቸው የሕዝብን ልብ ገዝተው ላቸዋል።
“ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሃደ ነው። ኢትዮጵያ ከፖለቲካ አመለካከት በላይ ነች። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” በማለት ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነት ያነሷቸው ሀሳቦቻቸው ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከደጋፊ እስከ ተቃዋሚ ሁሉንም የገዙ መልዕክቶች ነበሩ። ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባለፉት መቶ ቀናት ያከናወኗቸው ሥራዎች በምሁራን እንዴት ይታያሉ? በቀጣይስ ምን መሥራት አለባቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በትረ ሥልጣኑን ሲረከቡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች ነበሩ። አገሪቱም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነበረች። የመጀመሪያ ሥራቸውም ያደረጉት መረጋጋት ማስፈን ነው። የችግሮች መፍቻ ስልታቸው ደግሞ ከወትሮው የተለየ ነበር። የፀጥታ ኃይል ከመላክ ይልቅ መቃቃር፣ መጠራጠርና ግጭቶችን ለማስወገድ በየክልሉ በመዞር ስለ አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርታና ሠላም መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌት ተቀን በሚባል ደረጃ በጅግጅጋ፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ባሌ፣ ደንቢዶሎ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤና አፋር ከተሞች ፀብ እንዲጠፋ ሠላም እንዲወርድ መተማመን እንዲፈጠር ሰብከዋል። በዚህም አሁንም ያልተጠናቀቁ የቤት ሥራዎች ቢኖሩም አገሪቱ ከነበረችበት የሠላም እጦት እያገገመች ነው። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ተላቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ለመፍታት ብዙ መልፋታቸውንና እንደተሳካላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለኃይማኖት፤ በአገሪቱ የነበረው ግጭት የአፈና ውጤት መሆኑን ያነሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት ዴሞክራሲን የማስፋት አካሄድ የሚቀጥል ከሆነና የሕግ የበላይነት እየሰፈነ ከሄደ ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል። ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ያለውን የሠላም ችግር በመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርከተዋል። ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሥራትም ችግሩን ሙሉ በሙሉ መፍታት እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ።
ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትኩረት የተሰጠው የኢኮኖሚው ጉዳይ ነው። የመንግሥት ትላልቅ ድርጅቶችን በከፊልና በሙሉ ወደ ግል ማዘዋወር፣ የ2011 በጀት ዓመት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት ማድረጉ በጉልህ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ባልደረባ የሆኑት የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር አሰፋ አድማሴ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመንግሥት ግዙፍ ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ለማዘዋወር የተላለፈው ውሣኔ ትክክለኛ ነው ይላሉ።
ዶክተር አሰፋ እንደሚሉት፤ የ2011 በጀት ከሌሎች ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ዕድገቱ መጠነኛ ነው። ይህም ብድርን ለመቀነስ ያለመ ነው። የተመደበው በጀት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ላይ ማተኮሩ ገንዘብና ጊዜ እየበሉና በኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳደሩትን ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ያግዘዋል።
ከጎረቤት አገራት ጋር የተጀመሩ ጠንካራ ግንኙነቶችም በወደብ፣ በአየርና በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች በጋራ ለማደግና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ይረዳሉ። ከዚህ ባለፈም ለፀጥታ የሚወጣውን ወጪ በመቀነስ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ወራት ከአንድ መሪ የሚጠበቅ በቂ የኢኮኖሚ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ያስቀመጡትን አቅጣጫ የመፈፀም ኃላፊነት የዜጎችና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶች ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ መቶ ቀናት እስረኞችን በይቅርታ መፍታት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያከናወኑ ኃላፊዎችን በሌላ መተካት፣ የምህረት አዋጁ እንዲወጣና ሌሎች ሕጎችን ለማሻሻል ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ ማቋቋም በጉልህነት የሚጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍስሃ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ በተለያየ ምክንያት የታሰሩ ዜጎችን በመፍታት እንዲሁም በውጭ ታስረው የነበሩ ዜጎችን በማስፈታት ባለፉት ሦስት ወራት የለውጥ ኃይል መሆናቸውን አሳይተዋል። ችግር ያለበትን የፍትህ ሥርዓት መስመር ለማስያዝም እንደሞከሩ በማንሳት ጥሩ የለውጥ ጅምሮች መደረጋቸውን ይናገራሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን፤ ሆኖም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሰዱ እርምጃዎች አብዛኞቹ ትክክል ቢሆኑም፤ በሽብር፣ በሰው መግደልና በሙስና የተጠረጠሩና የተፈረደባቸው ሰዎቸ መፈታታቸው ተገቢ አልነበረም። የሚወሰኑ አንዳንድ ውሣኔዎች ግልፅነት ይጎላቸው ነበር። እንደ ሰንደቅ ዓለማ ያሉና ሌሎች ሕጎች አልተከበሩም። አንዳንድ ውሣኔዎችም የሕግ መሰረት ሳይኖራቸው ተወስነዋል። ከመስቀለኛ መንግድ ወደ ሌላ መስቀኛል መንገድ እንዳንገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥንቃቄና በትብብር መሥራት እንዳለባቸው በማንሳት ጅምሩን ከዳር ማድረስ እንደሚገባቸው ሃሳብ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመቶ ቀናት ውስጥ ትኩረት ሰጥተው ካከናወኗቸው ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሦስት ወራት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳና ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ሳኡዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኢሜሬቶችን ጎብኝተዋል። ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት መሥራታቸው ሌላው ስኬት ነበር።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሲሳይ አስምሬ፤ ዶክተር አብይ በዲፕሎማሲው መስክ ባለፉት ሦስት ወራት በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት አምጥተዋል። ለዓመታት በጦርነት ተፋጠው የኖሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራንም ወደ ሠላምና አንድነት በማምጣት ስኬታማ ሆነዋል። በዲፕሎማሲ ሥራቸው በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ተቀባይነት እያገኙ ነው። የጀመሩትን የዲፕሎማሲ ሥራ ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የቀጣናውን አገራት በኢኮኖሚ አንድ ከማድረግ ባለፈ ፖለቲካዊ ውህደትን ዕውን ለማድረግ መንገድ ይጠርጋሉ። እስካሁን ባለው የዲፕሎማሲ ሥራቸው ይህን ያስተካክሉ የሚባል ነገር የለም፤ የጀመሩትን ከፍፃሜ ለማድረስ መሥራት ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ወራት ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁት አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ እና ኦብነግ ከአሸባሪነት መሰረዛቸው በበጎ የሚታይ ተግባር ነው። በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መጥተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ አድርገዋል። እንደ ኢሳትና የኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ መገናኛ ብዙሃንና የሚዲያ መሪዎቹ ላይ የነበረውን የፍርድ ቤት ክስም እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህን ተከትሎ ወደ አገር ቤት የገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ለመግባትም የተዘጋጁ አሉ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲው መምህር ሲሳይ፤ በአሸባሪነት የተፈረጁ ከሽብር መሰረዛቸው፣ በተለያየ ምክንያት የታሰሩት መፈታታቸው፣ መገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዲዘግቡ መደረጉ፣ ዜጎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃ መግለፃቸው፣ ሕጎችን ለማስተካከል ሥራዎች መጀመራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሦስት ወራት ያከናወኗቸው ስኬታማ ሥራዎች ናቸው። የተጀመሩት ሥራዎች መልካም የሚባሉ ሲሆን፤ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን አክብረው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ፣ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል የማዳበርና ጠንካራ ተቋማትን የመፍጠር ጉዳይ በቀጣይ ትልቅ የቤት ሥራቸው ማድረግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

ዜና ሐተታ
አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።